Monday, January 15, 2024

ስልጣን በቃኝ

 

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ


መሰረታቸው ከወላይታ ንገስታት የሚመዘዘው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፡ በዘመናዊው የኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ፡ እስከማውቀው ድረስም፡ስልጣን በቃኝ ብለው ስልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ የለቀቁ፡ከቀዳሚዎቻቸው ሁሉ የተማሩ አንጋፋ ትሁት ፓለቲከኛ የነበሩ፡ ሰው ናቸው፡፡ ህሊናቸውና እውቀታቸው በሚፈቀድላቸው መጠን ሀገራቸውን በሙያቸው፤ ከዩኒቨርስቲ፡መምህርነት አንስቶ እስከ ሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ማዕረግ ድረስ የደረሱ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት እርሳቸው ሲናገሩ፡ በአአዩ፤ ሲመረቁ፡ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው አአዩ መቅረት ሲገባቸው ወደ አርባምንጭ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፡ የሄዱበትን አጋጣሚና በዚያም ከመምህርነት አንስቶ እስከ ኃላፊነት በርካታ ስራቸውን እንደሰሩ ሲናገሩ በኩራት ነበር፡፡ አርባምንጭ እያሉ፡ ደቡብ ክልል ውስጥ በተነሳ፡ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ  ወደ ፓለቲካው ተስበው፡ በክልል ደረጃ እስከ ርዕሰ መስተዳደርነት ከዚያም ወደ ፊደራል መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት ብሎም ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ቢያድጉም፡ ለተወለዱበት አካባቢና ህዝብ፡ ያገኙትን ስልጣን መከታ አድርገው አንድም ስራ አለመስራታቸው፤ ማንም ያውቀዋል፡፡ መስራትና ማድረግ ቢፈልጉ ግን ያሉበት ስልጣን ለማድረግ የሚገድባቸው አይደለም፡፡ እርሳቸው ግን ታማኝና ኢፍትሀዊነትን የሚጸየፉ ስለሆነ ሊያደርጉት አልደፈሩም፡፡

ቀዳሚው ጠቅላይ ሚኒሰቴር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ፡ ባልተጠበቀ ወቅት ይህችን አለም በሞት ሲሰናበቱ፡ ትልቅ የስልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር፡ እርሳቸውን ተክተው፡ የተጀመረውን ነገር ለማስቀጠል የሞከሩ፡ በስልጣን ዘመናቸውም የልዕለ ኃያሏን ሀገር መሪ ባራክ ኦባማን ተቀብለው ያስተናገዱ፡ ትሁት መሪ ነበሩ፡፡ አሳምኖ መስራት የሚል መርህ የነበራቸው አቶ ኃይለማርያም አንድ ጊዜ የኢ.ኦ.ተ.ቤተክርስቲያን እጅግ ያማሩ ህንጻ ቤተክርስቲያንን የምታሳንጸው ተከታዮችን አሳምና ነው፡ ፓለቲካውም /ካድሬውም/ አሳምኖ ነው መስራት ያለበት የሚል ይዘት ያለው ንግግሩ ሲያደርጉ አስታውሳለሁ፡፡

ሰውየው፡ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት፤ መልካም ሆነ መልካም ያልሆነ ነገር ሊፈጽሙ እንደሚገባ ይታመናል፡፡ ነገር ግን ማንም ስልጣን ለመያዝ በጎሳ፤ በቡድን፤ ሲደራጅና ገድሎም ወደ ስልጣን ለመምጣት በሚሰራበት አፍሪካ ስልጣን በቃኝ ያሉ በመሆናቸው ብቻ ትልቅ ትምህርት አስተምረዋል፡፡ ስልጣናቸውን እንደለቀቁም ሀገር ጥለው አልጠፉም ከቦታ ቦታ እየተተዘዋወሩ  በአየር ንብረትና አረንጓዴ ልማት ላይ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እና እንዴት ነው እኝህን ሰው የኢትዮጲያ ዲፕሎማሲ ሲነገር መዝለል የሚቻለው፡፡ ለእኔ እስከሚገባኝ ይህ ማለት በእርሳቸው ዘመን ኢትዮጲያ ምንም አይነት የዲፕሎማሲ ስራ አልሰራችም፤ ማለት ሲሆን፡ ኢትዮጲያ የምትባል ሀገር የለችም ነበር ማለት ነው፡፡

 

እያለህ የለህም፤ ደግሞ ግራ ያጋባል፡፡

No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...