Thursday, April 30, 2026

የሰፈራችን ትልቁ ሰው


የሰፈራችን ትልቁ ሰው የአባባ ጋሼ

ተወልጄ ባደኩባት የገጠር መንደር ውስጥ ሰፈራችን በርካታ ሰዎች በአስተዳደጋችን ውስጥ ብዙ አስተዋጽኦ አላቸው። ልጅነታችን የጋራ ነው። በወላጆቻችን ስም እንጠራለን፤ወላጆቻችን ቤት እናድራለን እንጂ፤ ምግባችን፤አገልግሎታችን፤ስናጠፋ የሚገርፉን፤ጥሩ ስንሰራም የሚያመሰግኑን፤ ለወደፊት ማንነታችን ትልቅ አስተዋጾኦ ያላቸው በርካታ ሰዎች አሉ።ከእነዚያ ዘመን ካፈራቸው ሰዎች መካከል አባባ ጋሼ አንዱ ነበሩ። አባባ ጋሼን ወላጆቻችንን፤ ታላላቆቻችንን ሁሉም አባባ ጋሼ ነው የሚላቸው። ሙሉ ስማቸው ጋሸ ታፈሰ ይባላሉ። አባባ ጋሼ በስማቸው የውሃ ምንጭ አላቸው፤ሱልላ ወይንም አባባ ጋሼ ምንጭ ሄዳችሁ ውሃ ቅዱ ይባላል። ምንጩ ጥልቅ ሲሆን፡ በበጋ እንኳን የማይቀርቅ በክረምት ጎርፍ ገብቶበት የማይደፈርስ ነው። ምንጩ መቼና በማንም እንደተቆፈረ ጥርት ያለ መረጃ ባይኖረኝም፤እርሳቸው ስለቆፈሩት ይመስለኛል፤ በስማቸው የሚጠራው። በበጋ ወራት፡ በተለይም የእህል ውቃ በሚከናወንበት ወቅት፡የውሃ ወረፋ ካለ ከእርሳቸው ቤት የሚመጣ ልጅ ወረፋ አይጠብቅም፡ ቅድሚያ ይሰጠዋል።ባለቤታቸው ወ/ሮ ዘነበወርቅ ከመጡ ደግሞ እዚያ ያለ ሰው ቀድቶ እቤታቸው ያደርሳል። እማማ ዘነበወርቅ፤ ህጻን እንኳን ቢሆን ዝም ብለው አያልፍም፡ የማይሆን ቦታ ከሆነ የተገኘው፤ ተቆጥተው፤ ቤት ድረስ ሄደው እንዴት በዚህ ሰአት እዚህ ቦታ ትለቁታላችሁ፡ ብለው የተሰብን ሁሉ፤ የሚቆጡ ደርባባ እናት ነበሩ። ለእማማ፤ ዘነበወርቅ ምንጭ ሲመጡ ይህ የሚደረግላቸው፤ እርሳቸው ፈልገውት ሳይሆን ፍቅራቸውና እናትነታቸው፤ስለሚያስገድድ ነው። አንዳንድ ጊዜ እርሳቸው እዚያ፤ካገኙት ሰው ጋር ሲጫወቱ ልጆችን ሲመክሩ ውሃ ተቀድቶ ቤታቸው መድረሱን እንኳ ላያውቁ ይችላሉ። ቤታቸው ድግስ አይጠፋም፤በቅርበት ልጅ ካዩ ቤት ገብተው ያላቸውን አውጥተው የሚሰጡ ደገኛ የዚያ ዘመን እናት ነበሩ። አይ ሞት ግን ስንቱን ደግ ሰው ወስዶ ደሃ አደረገን።አባቴ የአባባ ጋሸንና የወ/ሮ ዘነበወርቅን ሴት ልጅ፡ለማግባት አጭቶ፤ ነገር ግን ጋብቻው አልተፈጸመም። ምክንያቱን እኔ አላውቅም። ይሁን እንጂ አባቴን ልክ እንደልጃቸው፤እርሱም እንደወላጆቹ ነው የሚተያዩት፡ በሚገርም ሁኔታ አባቴ ሊያገባት የነበረችው ልጃቸው የጓደኛዬና አብሮ አደግ ወንድሜ አደፍርስ ከፈለው  እናት ናት። ባትወልደኝም እናቴ ናት። አባባ ጋሼ ያላቸው ቅርበት በተወሰኑ ጉዳዮች ከወላጅ አባቴ  ጋር ላቅ ይላል እንጂ ለአባቴ ወንድሞችና ለሌላው ሰው ሁሉ ያላቸው ቅርበት አንድ ነው። አባባ ጋሼ ብልህ፤ ወጌሻና ብዙ ጥበብ አላቸው። ለበርካታ ሰው መፍትሔ የሚሰጡ፤የተጣላን የሚያስታርቁ ነበሩ። ልጅ ሳለሁ እግሬን አልቤን ማጭድ ቆርጦኝ ሽባ ይሆናል መራመድ አይችልም ሲባል፤ ጨው በብረት ምጣድ እያቀለጡ፤ በየሶስት ቀን እያጠቡና በንጹህ ጨርቅ እየሸፈኑ፤ በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ ጤነኛ ያረጉኝ ትልቅ አባት ናቸው። ዛሬ ጫማዩን ባሰርኩና በፈታሁ ቁጥር ጎንበስ ስል፤ ያኔ በጨው ሲያጥቡኝ ፤ሳለቅስ፤አይዞህ እያሉ ያባብሉኝ የነበረው አንደበታቸውና አባታዊ የፊታቸው ጭንቀት ድቅን ይልብኛል። አባባ ጋሼ ከከተማ ስንመጣ፤ ስለኑሮው ስለከተማ ደህንነት ይጠይቁኛል።

አባባን ከውስጤ እንዳልረሳቸው የሚያደርገኝ ግን አንድ ነገር ነው። ማትሪክ አልፌ፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመማር በዘመኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር በነበረው ባህርዳር መምህራን ኮሌጂ ደርሶኝ የመጀመሪያ አመት ትምህርቴን ጨርሼ፡ ስመለስ፤ በተደጋጋሚ ይጠይቁኝ የነበረው ስለሀገሩ ርቀት ለምን ባህርዳር እንደተባለ ነበር። ትልቅ ባህር አለ፤ እያልኩ የጣናን ግዘፈት ያክል ሳይሆን እርሳቸው በሚገባቸው ልክ ነገርኳቸው፡ በጣም ተገረሙ። በውይይታችን መጨረሻ፡ አደራ ወደዚያ ባህር አጠገብ እንዳትሄድ እያሉ ሲያስጠንቅቁኝ፤ በጣና ሃይቅ ላይ በጀልባ እንደሄድኩ፡ አባይን በእግሬ ለመሻገር ሙከራ እንዳደረግሁ ብነግራቸው እንዳይደነግጡ በማሰብ ተውኩት። ከዚያ በሁዋላ ላገኙት ሰው ሁሉ የሚያወሩት የእኔ ትምህርት በጣም ለየት ያለ ባህር አለበት ሀገር እንደምማር ነው። እኛም ቤት መጥተው የሚያወሩት ይህንኑ ነው። በአባባ አረዳድ የትምህርት ክብደትና ቅለት የሚለካው ከአካባቢ ርቆ በማማር ስለሆነ። ተመርቄ ለስራ ደቡብ ክልል ደረሰኝ፤ ያኔ የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሀዋሳ ናት። ሀዋሳ ደርሼ እጣ አውጥቼ  ወደ ቤት ሄድኩኝ፤ ስራ የት ደረሰህ ሲሉኝ ለገጠር ሰው ደቡብ ክልል ማለት ቶሎ ላይገባቸው ይችላል ብዬ በማሰብ ሀዋሳ ነበር የምለው። ብዙ ሰው የሀገሩን ርቀት፤እንጀራ አለ፤ሰላም ነው፤ እንደው የምታውቀው ሰው ይኖራል ብለው ነው የሚጠይቀኝ። አባባ ግን ስለአየሩ፤ስለሚመረተው ምርት፤ሰው ስለሚናገረው ቋንቋ፤ ነው። ያኔም በጣም አስፍቼ የነገርኩዋቸው ስለ ሀዋሳ ሀይቅ ነው። በጣም የሚገርመው፤ ድጋሚ ለዞን እጣ ሳወጣ የደረሰኝ፤የቀድሞው፡ ሰሜን ኦሞ ዞን ሲሆን ዋና ከተማው አርባምንጭ ነው። ለአባባ ስለአርባምንጭ ስለሁለቱ የጫሞና አባያ ሃይቆች አንስቼ ስለነገርኳቸው፡ውስጣቸው የደረሰበት ድምዳሜ እኔ የተማርኩት ትምህርት ከሁሉም የላቀ እኔ ከሁሉም በጣም ጎበዝ የሆንኩ፤ ወደፊትም በቃ ስራዬ ሁሉ ውጭ እንደሆነ  ነበር። ከዚያ በሁዋላ ለእረፍት ስሄድ በጣም እንደትልቅ ሰው አውርተውኝ፤ሸኝተውኝ፤መክረውኝ ፤ እቤት ሄጄ ጋብዘውኝ ነበር የምንለያየው። አባባ ሰፈራችን ሰው ሲሞት አስከሬን አጥበው፤የሚገንዙ ሰው አጥብቆ ሲያዝን የሚቆጡ፡ነበሩ። አባቴም ከልቡ ነበር የሚወዳቸው፤አማካሪያቸው፤ የሚላክላቸው፡ ነበር። የሚገርመው የአባባ ሁሉም ልጆቻቸው፡ በሚባል ደረጃ ቁምነገረኛ፤ ሰው የሚወዱ፤ ለሰው ፈጥነው የሚደርሱ ናቸው። እትዬ እትሜ፤እትዬ ትርንፍስ በብዙዎቻችን የማይረሱ የአባባ ፍሬዎች ናቸው። አሁን ቤታቸውን ይዞ ያለው ልጃቸው በእርሳቸው ቦታ የተተካና ለሰፈሩ ሰው ሁሉ ፈጥኖ ደራሽ ነው። ከእርሳቸው አንጻር ልጅ አልኩት እንጂ ጋሽ ንጉሴ( ብዙ ሰው አንች ነው የሚለው) ወልዶ የዳረ ትልቅ ሰው ነው።

አባባ ጋሼ ነብስዎት በቅዱሳን እቅፍ ያኑረልኝ።

የአባባ ጋሼና  ያደኩባት መንደሬ የወላጆቼ መንደር


No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...