Monday, May 25, 2026

 

                                    የኦሞዋ በሌ ሐዋሳ

                                ውስጤ ገብታለች ሆና እንዳትረሳ


                  ወደ ስራ ከመግባቴ 2 ወር በፊት የነበረኝ ገጽታ

ገና ከማለዳው በዳመና የተጀቦነው የዳሞታ ተራራ በእድሜ ብዛት ነጭ ጸጉር የለበሱ አዛውንት መስሎ የሶዶ ከተማን ቁልቁል ይመለከታታል። ከመኝታዋ ብዙም ያልነቃችው የሶዶ ከተማ ፡ ገና በመንጠራራት ላይ ብትሆንም ጥቂት ነዋሪዎቿ፡ ግን ወደ እለት ስራቸው ተሰማርተዋል። በዘልማድ አሮጌ አራዳ ከሚባለው የከተማ ከፍል በጋሪ ተጭነው ወደ መናሐሪያ የሚመጡ ሰዎች ቁጥራቸው በርከት ይላል። ጤና ጣቢያና አጂፕ አካባቢ የቀን እንጀራ ፈላጊዎችና ኑሮዋቸውን መንገድ ዳር ያደረጉ ታዳጊ ህጻናት ላይ ታች ይላሉ። ከታች ከማርያም ቤተክርስቲያን አቅጣጫ እንደዚሁ ወደ ላይ እና ወደታች የሚሉ የማለዳ ሰዎች ይታያሉ። ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ወደ አርባምንጭ አቅጣጫ ረጂም ጡረንባቸውን እያሰሙ ከተማዋን በጭስ እያጠኑ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎችም ይታያሉ። ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ነጠላቸውን መስቀልያ ለብሰው ወደ ቤተክርስቲያንና ወደ ቤታቸው ይተማሉ። እኔ በዚያን ቀን ጠዋት አዲስ ለስራ ተመድቦ ከመጣ አንድ አይነስውር መ/ር ጋር ትንሿ ሆቴል አብረን አድረን እርሱን ወደ አረካ አሳፍሬ፡ወደ ተመደብኩበት ወረዳ ለመሳፈር መኪና ለማግኘት ላይታች እላለሁ። እንደአለመታደል ሆኖ እኔ የተመደብኩበት ወረዳ ተሳፋሪዎችን ከመደበኛው መናሐሪያ ሳይሆን የሚያሳፍረው ውጭ ነው። መንገዱ፤ጥርጊያ መንገድ እንጂ በስርአት ተሰርቶ ስላልተጠናቀቀ፤ መንገድ ትራንስፖርት ስለማያወቀው፡ የግለሰብ ፒክ አፕ፤ላንድሮበር አንዳንድ ጊዜም መለስተኛ የዕቃ መጫኛ መኪናዎች ጤና ጣቢያው ፊት ለፊት፤ትንሿ ሆቴል ግቢ ወይንም አቶ ደባራ ደጅ፡ያሳፈራሉ እንጂ፤ ከመደበኛው መናሀሪያ አይገኙም ነበር። አብዛኛውም ሰውም በእንደዚህ አይነት መኪናዎች መሄድን ይመርጥ እንደነበር እንደቀልድ ጣል የሚደረግ አንድ አባባል ነበር፤ መንገዱ ተከፍቶ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎንችናዎች ሲመደቡ "ሰው መኪና አጥቼ በሎንችና (በሽፍን) መኪና መጣሁ" ይላል እየተባለ ይነገር ነበር። ሳስበው ይህ ለቀልድ የሚባል እንጂ እውነተኛው ተሳፋሪ ይህንን ይላል ብዬ አልገምትም። አጋጣሚ የዚያን ቀን ወደ ምሄድበት የሚያሳፍረው ተሽከርካሪ ላድሮቨር መኪና ሆኖ የሚጭነው ጤና ጣቢያው ፊት ለፊት ነበር። እንግዳ እንደሆንኩ ብዙ ማስረጃዎች ስላሉብኝ ይመስላል የተሰጠኝ ቦታ እንደ እንግዳነቴን ያከበረና ጋቢና ሹፌሩ አጠገብ ነበር። የልብስ ሻንጣዬን ጉልበቴ ላይ አድርጌያለሁ። መኪናዋ መጫን ከሚገባት ሁለት እጥፍ ጭናለች። ይህ በመሆኑ፡ማንም ቅር የተሰኘ የለም። ወንበር ላይ የተቀመጠ ሌላ አንድ ሰው በላዩ ላይ ሰው ማስቀመጥ ግዴታው ነው ተብሎ የተደነገገ ይመስል፤ ማንምሰው እላዩ ሲቀመጥ እንቢ አይልም፤ነውርም አይመስልም። መኪናዋ ውስጥ ዘፈን ወይንም መዝሙር እስከመጨረሻው ተከፍቷል። ቋንቋው ምን እንደሆነ ባላውቅም ወላይትኛ ግን እንደሚሆነ ገምቻለሁ። ከአፍ እስከገዳፉዋ ሰው የጫነቸው መኪና እንቅስቃሴ ስትጀምር ወሬው ደራ። በዚህ ወከባና የደራ ወሬ ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌለኝ እኔ ብቻ እመስላለሁ’ ሁሉም ያወራል። እንዴት መደማመጥ እንደሚቻል ግን ግራ ገብቶኝ ነበር። ሁሉም ያወራ ስለነበር። ይህ ዝምተኛነቴና ምናልባትም ፊቴ ላይ የሚነበብ ጭንቀት ሹፌሩ እይታ ውስጥ እንድገባ ሳያደርገኝ አልቀረም፡ በየመካከሉ አይዞህ ይለኛል። የተሳፈርንባት መኪና፤ብዙም ሳንጉዋዝ፡ ጭቃ ያዛት ተባለና በርከት ያለ ሰው ወርዶ መግፋት ጀመረ፤ ይህንን መሰል ተግባር ከ 5-8 ጊዜ ያክል የተደረገ ይመስለኛል 37 ኪሜ መንገድ ለመድረስ። የውጭው አየር አሁንም በዳመና እንደተሸፈነ ቢመስልም የጸሐይ ጨረር አርፍዳም ቢሆን፤ለመውጣት ሙከራ እያደረገች ነው። ብርሃንዋ ግን ጥቅጥቁን ደመና በፍጹም ሊደፍረው አልቻለም። መኪና ውስጥ ያለው ሙቀት ከፍተኛ ነው። በተለይም ሜዳማውንና ደጋማውን ቦታ እንዲሁም የጉንኖን ከተማ እንዳለፍን የኦሞ በርሃ ክልል ውስጥ ስለገባን ሙቀቱ በጣም ከፍተኛ ነው። አይኔ ማየት እስከሚችለው ድረስ ሳይ በአረንጓዴ የተሸፈነ የበረሃነት ባህሪ ያለው መሬት ነው የሚታየኝ። ወደ ከተማዋ እየቀረብን ስንመጣ በርካታ የመንገድ ስራ የሚያከናውኑ መኪናዎች ከእኛ  ብዙም ባልራቀ እይታ አዲስ መንገድ በመቀየስ  ላይ ሲረባረቡ ይታያል። በሁዋላ ባገኘሁት መረጃ ሳሊኒ የሚባለው የመንገድ ተቋራጭ ከሶዶ ጭዳ መንገድ ለመስራት ግንቦት ወር ላይ ስለገባ መኪናዎቹና መንገድ ቀያሾቹ የጣሊያናዊው የሳሊኒ መንገድ ስራ ድርጅት ንብረቶች መሆናቸውን ተረዳሁ። ሳሊኒ መንገድ ስራ ተቋራጭ በአራት አመት የበሌ ቆይታዬ፤ በርካታ ወንድምና እህቶችን እንዳውቅ ረድቶኛል። ተጋብተው ልጆች እናት የሆኑትን የአርባምንጬን ኤዶም ታፈስንና የፍልቅልቅዋ፤ ከተማ ልጅ የሆነችውን ስንታየሁን፤ ዮናስ ዳኛቸውንና የጓደኛዬ ባለቤት የሆነችውን እህቱ አለምጸሐይ ዳኛቸውን፤እናም ሌሎችን. 

ለስራ የተመደብኩባትን በቀድሞው ሰሜን ኦሞ ዞን ውስጥ የምትገኘውን የበሌ ከተማን በዚህ መንገድ ረቡዕ ነሐሴ 24 አየሁዋት። ላንድሮበሩዋ መኪና ከተማ ደርሳ ሁሉም ሰው ሲወርድ እኔ ብቻ ቁጭ ብያለሁ፤ ሁሉም ተሳፋሪ ወርዶ ሲያበቃ ሹፌሩ ሲገባ እኔ ቁጭ ብያለሁ፤ውረድ እንጂ ሲለኝ፤እኔ እዚህ አልወርድም አልደረስኩም አልኩት፤ ፈገግ እያለ ይህ እኮ የመጨረሻው ነው፤ አለኝ፡ የቆምንበት ሰፊ የመገበያያ ቦታን እያሳየኝ። ግራ በመጋባት ምንም ሳልመልስለት ስቀር ረዳቱን መጣሁ አለና መኪናውን አስነስቶ በከተማ ካለ ትልቁ ሆቴል ወሰደና አንድ ልጅ ጠርቶ አልጋ አስይዘው ብሎኝ ተመለሰ። ትልቅ ሆቴል ስል አንጻራዊ እንደሆነ ይታሰብልኝ፤ ባለኮኮብ ሆቴል እንዳይመስል።

ይሁን እንጂ በዚያም ሆቴልም ሆነ በሌሎች ከተማ ውስጥ ባሉ ትናናሸ ቤቶች ጭምር አልጋ ፈጽሞ እንደማይገኝ መርዶ ተነገረኝ። ይህንን እንደሰማሁ በመጣሁበት መኪና ለመመለስ አይኔን ስወረውር የመጣሁባት መኪና በመጣችበት ሁኔታ ተሳፋሪ፤ጭና ከተማውን እየለቀቀች ከርቀት ተመለከትኩዋት። አሁን ፍርሃቴ በጣም ጨመረ፤ ዕለቱ ጾም ስለነበር፤ቁርስ አልባላሁም፤ ምሳ ሰአት እያለፈ ቢሆንም ረሃብ አይሰማኝም። በምትኩ የት እወድቅ ይሆን የሚል ሃሳብ ነው ውስጤን እያስጨነቀው ያለው። መጀመሪያ ውስጤ የመጣው ደጀ ሰላም ነው። በማላውቀው ሀገር ዘመዴ መጠጊያዬ ቤተክርስቲያናት ማን ከእርሷ ሊቀርበኝ፤አልኩኝ፤ ከግቢ ስንወጣ፡ ቤተክርስቲያና ቤታችሁ ናት ወደ እርስዋ ሂዱ ዘመድ ወላጅ እርሷናት እያሉኝ ያስተምሩን የነበሩ መ/ራን ቃል እያስታወስኩ። በሹፌሩ አማካኝት እያጋዘኝ ያለውን ልጅ እያዩ ሜንታ ይባላል፤ ስራ ስጀምር የ 9ኛ ከፍል ተማሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ቤተክርስቲያን የት ነው ያለው አልኩት? የማን አለኝ? ምን ማለት ፈልጎ ነው የግል ቤተክርስቲያን የለ? የማን እንድለው ነው ብዬ መልስ ሳልሰጠው ዝም ስል፤ ሙሉወንጌል፤ቃለህይት ሀዋርያት እያለ ደረደረና የኦርቶዶክሶችም መዳናለም እዚያ ጋ አለ አለኝ። መድሃኔአለም ቤተክርስቲያን ወዳለበት አቅጣጫ እየጠቆመኝ። በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፤ውጭ ቤተክርስቲያን ያላቸው እምነቶች እንዳሉ አወቅሁ። የ2ኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ደብረብርሃን ከተማ ውስጥ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በግለሰብ ቤት ጸሎት ያደርጋሉ፤ ሲባል እሰማ ነበር እንጂ ለእኔ እስከዚያ ቀን ድረስ ቤተክርስቲያን የኦርቶዶክስ ብቻ ነበር የሚመስለኝ። ይህ ሃሳብ የሌላው ሰው እምነት ካለማወቅና ካለማክበር የመጣ ሳይሆን፤ ለመረጃ ቅርበትና ርቀት አንጻር የመጣ ነበር። ፍርሃቴ በጣም እየበረታ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ምን ማድረግ እንዳለብኝ ሳስብ አንድ ሃሳብ ትውስ አለኝ፡ እጣ ሳወጣ ከበሌ ወደ ሌላ ቦታ ለመዛወር አርባምንጭ ያገኘሁት አንድ መ/ር ስለሁለት ሰዎች ነግሮች ነበር። አንዱ ስለ ት/ቤቱ ም/ር/መር እና ወረዳ ጽ/ቤት ውስጥ ደሞወዝ ስለምትከፍለው አንድ ሰራተኛ። አሁን በዚህ ከተማ በአካል ባይሆንም በስም የማውቃቸው እነርሱን ግን የማያውቁኝ ሁለት ሰዎችን ብቻ ነው አልኩ ለራሴ። አቶ ዶሎ ዶናና ወ/ሮ ወርቅነሽን። ሁለቱን ማነጻጸር ጀመርኩ ወ/ሮ ወርቅነሸ ለጊዜው ተውኩዋትና የአቶ ዶሎን ቤት እንዲያሳየኝ ልጁን ጠየቅሁት። ፈቃደኛ ሆኖ ወደ አቶ ዶሎ ቤት ሄድን አጋጣሚ አቶ ድሎ ከስራ ለምሳ ቤት ገብቶ ስለነበር አገኘነው። እዚያ መመደቤ ቀድሞ መረጃ ደርሶት ስለነበር በደስታ ተቀበለኝ፤ ሻንጣዬን አስቀመጥኩ፤ምን ተፍረቴን፤አልጋ እንደምፈልግ ስነግረው አልጋ አታገኝም እዚያ ታድራለህ ብሎ ከጭንቅ ገላገለኝ። በቃ ከተማውን ልይ ከሰአት ጽ/ቤት ሄጄም ሪፖርት ላድርግ ብየው ወጣሁ።

ወሩ ነሐሴ ቀኑ  24 ዕለቱ ረቡዕ  ነበር። ሰማይ ተከፍቶ በጣም ከፍተኛ የጸሐይ ዝናብ እወረደ ስለነበር መንቀሳቀስ በጣም ከባድ ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር ለእኔ አዲስ ስለነበር ያለመታከት ጽ/ቤት ከሰአት እስከሚከፈት ከተማዋን አየሁዋት። ምንም እንኳን ውስጤ የመከፋትም የመደሰትም ነገር ባይሰማውም፤የማስበው ተመልሼ እንዴት ወደ ቤት እሄዳለው የሚለውን ብቻ ነው። አመጣጤማ እስከ አዲሱ አመት ዋዜማ እዚህ ቆይቼ ለበአል ወደ ወላጆቼ ለመመለስ ነበር። ያለሁበት ሁኔታ ግን ለአንድም ቀን ማደሪያ ስለሌለ፤ መፍትሔው መመለስ ብቻ ነበር።

አይደርስ የለ 7፤30 ሲንቀረፍፍ ደረሰ፤ ጽ/ቤት ሄድኩ ከጥበቃው ውጭ ማንም ሰው የለ። ምናልባትም ከ 30 ደቂቃ በሁዋላ ሰራተኞች ቀስ እያሉ ወደ ቢሮ መምጣት ጀመሩ። ከሚመጡት ሰዎች መካከል ሃላፊ ሊሆን ይችላል ብዬ የገመትኩ ሰው ሲመጣ ተከትየው ቢሮው ገባሁና ሰላምታ አቅርቤ፡ አዲስ እንደተመደብኩ ስነግረው እጅግ በጣም ደስ በሚል አባታዊ ሰላምታ ሰላም አለኝ። ማስታወሻውን አወጣና በስሜ ሲጠራኝ በጣም ደስ አለኝ። እስከአሁን የነበረው፤ፍርሃቴ ሁሉ ጥሎኝ ጠፋ፤ነጻ ሆኜ አወራሁት። ትንሽ ካጨወተኝ በሁዋላ በየቢሮ እያዞረ ከጽ/ቤቱ ሰራተኞች ጋር አስተዋወቀኝ። አርባምንጭ፡ እያለሁ በዝውውር ሂደት ላይ ስለወርቅነሽ ተነግሮኝ የነበረውን በስም የማውቃትን ወርቅነሽንም ወርቄ በሚል ስም በአካል፡ተዋወቅሁዋት። ከትውውቅ በሁዋላ ስለቀጣይ እቅዶቼ ሲጠይቀኝ፤  አቶ ታደሰ "ሃሳቤ እዚህ ለመቆየት ነበር፤ አሁን ሳየው የሚመች ነገር ስለሌለ ወደ ወላጆቼ ተመልሼ መስከረም መጀመሪያ ሳምንት፡ እመጣለሁ፤ ድፍረት ካልሆነብኝ እስከ፤ ምመጣ ድረስ ቤት ብታፈላልግልኝ አልኩት፟፟።'' አቶ ታደሰ ግን ምንም አይነት የቅሬታ ስሜት ሳያሳይ እንዴ ይህ እኮ ግዴታችን ነው፡ እንፈልግልሃለኝ አለኝ። አስከትዮም ለዝግጅት ይረዳኝ ዘንድ  የሐምሌ ወር ደሞወዜ እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት። ብዙም አልገረመውም፤ "አሁን ብቻህን እዚህ ከምትሆን በአል ከቤተሰብ አሳልፍና ተመልሰህ ና፤ የሐምሌወር ደሞዝህ አሁን ይከፈልሀል" ብሉ ወዲያው ከነወርቄ ከፍል ካለችው፡የሂሳብ ክፍል ሃላፊዋ ተጠሩ። እጄ ላይ የያዝኩት በግል የተሰጠኝ የቅጥር ደብዳቤ፤’ለጽ/ቤቱ የተጻፈውን ደብዳቤ እንጂ የፋይናንስ ደብዳቤ ስላልመጣ ሙሉ ደሞወዙን መክፍል አንችልም ፋይናንስ ስለማይሰጠን።  ብድር ግን  ቢሰጠው የሚል ሃሳብ አቅረበች፡ ሃላፊው በጣም ተቆጣ፤ አሁን እኮ የነሐሴ ደሞወዝ መውጫ ቀን ነው፤ለምንድነው የሃምሌ ደሞወዙየማይሰጠው አለ፤ በቀናነት። ይህ ሃላፊ የእኔን መቸገር እንጂ የመንግስት አሰራር ስርአት ምኑም አልነበረም። እንደሰማሁት ወረዳው ውስጥ ባለው ብቸኛው፤ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ደረጃውን የጠበቁ መ/ራን ስለሌሉት የሚመጡ መ/ራን ተንከባክቦ መያዝ እንደ አቅጣጫ የወረደ ስለነበር ያንን ለመተግበር እየተጋ ነው። ሂሳብ ክፍልዋ ተረጋግታ አሰራሩ ስለማይፈቅድ ነው፤ ብለው አስረዱ፥ አሺ ወደ መፍትሔው እንምጣ፤ ተብሎ ሰከን ወደላዬ ውይይት ሲገቡ፤ በፍጹም ፈገግታ አንድ ጊዜ ጠብቀን ተባልኩና ወደውጭ ወጣሁ። ከረጂም፤ውይይት በሁዋላ በቃ ነገ እስከምሳ ሰአት ድረስ እንደምንም አድርግን ቢያንስ ግማሽ ደሞወዝክህን እንሰጥሃለን፡ ለዛሬ እንደምንም ተቸገረኝ ሲሉኝ፤ እጅግ በደስታ እሺ ብያቸው ከቢሮ በደስታ ስወጣ ደሞወዝን በብድር ማግኘት እስከ ታህሳስ መጀመሪያ ወር ይሄዳል ብዬ አላሰብኩም ነበር።


                 ----------------ይቀጥላል-------------

No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...