Sunday, November 27, 2022

መስረከም ሲጠባ

 

መስከረም ------ ህዳር-------

 



በልጅነቴ እረኛ እያለሁ፡ በዘያ ዘመን ከነበሩኝ ጓደኞቼ ጋር በአረንጓዴው ስፍራ ከብቶቻችንን እየጠበቅን፤ የባቄላ፤ የአተር፤የሽንብራና የምስር እሸታችንን እየጠረጠርን ስንጠግብ ከምናጎራጉራቸው ዘፈኖች መካከል

መስረከም ሲጠባ ህዳር ሲታጠን

እልክልሻለሁ ልቤን በሳጥን፡፡

 የምትል ያኔ ትርጉሟ እንኳ ምንድነው ብዬ የማልጠይቃት ግጥም ከእንጉርጉሮዎቻችን መካከል አንዱዋ ነበረች፡፡  አሁንም ቢሆን ትርጉሙ ምንድነው የሚለውን ከመጠየቅ ውጭ፡ ውስጤ የሚገባኝ ነገር ትክክል ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ብቻ ይህ አፍቃሪ ባለፉት የክረምት ወራት፡ ወንዞች ሞልተውበት ዝናብ መንቀሳቀሻ አሳጥቶት በርቀት ያለችውን አፍቃሪውን ማየት እንደተቸገረ፡ብሶትና ፍቅሩን መግለጫ ትመስላለች፡፡ ምንም እንኳን፡ደገኛው የዝናብ ወራት ወጥቶ የእርሱ ተከታይ የሆነውና ምድር በአረንጓዴ ያለበሳት፤ መስከረም፡ጥቅምትንና ህዳርን አስከትሎ ቢመጣም፤ አረም፡ ባቄላ ሰበራና ሌላም ተያያዥ በርካታ ስራዎች ሊኖሩት፤ ስለሚችል እርሱ አሁንም፡ ሊያያት ባለመቻሉ እያዘነ፡ ልቤ ግን አሁን እንዳፈቀረሽ ነው፡ ካላመንሽ በድኔን አስቀርቼ  ለመልክተኛ ልቤን በሳጥን ልኬልሻለሁ፡ ጠብቂው፤ያዠው፡ መከር ሲሰበሰብ በየካቲት እመጣለሁ አይነት መልዕክት ይመስለኛል፡፡

ያ የእረኝነት ዘመን አለፈና ትልቅ ሰው ተሆኖ፡ ህዳር ሲታጠን የሚለው ወሬ ሲወራ በወርሃ ህዳር፡ በለምለሙ መስክ ላይ የባቄላ እሸት እየጠበስን ሆዳችንን በባቄላው፡ አየሩን ደግሞ በጭሱ የምናጠግበውና የምናጥነው፡ ትዝታ ግን አይረሳም፡፡

የሽንብራው ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ

የትም የትም ዞሮ ትዝ አለኝ መንደሬ፡፡ አይደል ነገሩ፡፡

በህዳር 11 ከአሁን በፊት፡ ሁለት ወሳኝ የሆኑ፡ የህይወት ሁነቶችን ከውኜባቸዋሉ፡፡ በዚህ አመትም ህዳር 11 የዋለው፤በዕለተ ሰንበት፡ ስለነበር፡ ምንም እንኳ ስራ ላይ ብሆንም በነጋታው ያለውን አመታዊውን ቅዱስ ሚካኤል በኣል በአጥቢያዬ፤ ከቤተሰቦቼ ጋር ለማክበር አመሻሹም ላይ በልጆቻችን አነሳሽነት በጋራ መኖሪያ፡ ህንጻችን፡ ላይ በቅርብ በመሰረትነው የጋራ፤ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍና እንዲጠናከር የራሴን አስተዋጽኦ ለማድረግ ውጥን ውስጤ ስለነበር፡ የሰኞን ጉዞ በጥበብ ወደማክሰኞ፤አሻግሬው ስለነበር፡ ውስጤ ደስተኛ ነበር፡፡ ግን ደስታዬ 24 ሰኣት ሳይሞላው፡ ይህንን ፕሮግራም የሚያፋልስ ሌላ ካለኝ ኃላፊነትና ስልጣን ውጭ የሆነ ጉዳይ ተፈጠረ፡፡ በቃ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡ እንዴውም ቅዱስ ሚካኤል በወላይታ ሶዶ ደብረመንክራት አቡነተክለኃይማኖት ገዳም በረከቱን እሳተፋለሁ ብዬ ውስጤን በማሳመን፡ እሁድ ህዳር 11፡ ጉዞ ወደ ወላይታ፡ በፈጣኑ መንገድ፡፡ በዕለቱ፡አዲስ አበባ በታላቁ ሩጫ የተነሳ ጠዋት መንገዶቿ ስለሚዘጉ፡ ረፈድ አደርግን ለመውጣት ቀጠሮ አሰርንና ወደ አራት ሰኣት ገዳማ አዲስን ለትተናት ቱዲ ፈጣን መንገድ መግቢያ ደርሰን ረጁሙን መንገድ ተያያዝነው፡፡ አብዛኛውን የመንገዱን ክፍል በእጄ ላይ ያለውን ኦርቶጵያ  የሚል መጽሀፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ ልክ 5፡30 አካባቢ፡ ሞጆን አልፈን፡ጉዞአችንን ቀጥለናል፡፡ አልፎ አልፎ ቀና እያልኩ ግራ ቀኙን ባይም፡ ንባቤ ላይ ቸክያለሁ፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በሁዋላ ወይኔ የሚል ድምጽ ከአሽከርካሪው ሰምቼ ቀና ስል እጀግ በርካታ የበግና የከብት መንጋ የፍጥነት መንገድ አጥሩን አቋርጦ፤ ከሁዋላ በእረኞች በጅራፍና ዱላ እየተደበደበ አንዱና አስፋልት አቋርጦ በእኛ የመሄጃ አስፋልት ላይ ሲደረስ፡ እኛም ስንደርስ በቁጥር ከሚበዙት እንሰሳት፡ ጋር አንድ ላይ ነበር፡፡ በተፈቀደልን የፍጥነት ገደብ ስንፈጥን ስለነበርን፡ አሽከርካሪው የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም አደጋውን ማስቀረት አልተቻለም፡ ምናልባት ወደ ግራ ቢይዘው ከእንሰሳቱ ይልቅ እረኞቹ ላይ አደጋው ይበረታ ነበር፡፡ ከመኪናችን፡ ውጫዊ አካል ጉዳትና ከተወሰኑ እንሰሳት መጎዳት በስተቀር ምንም አይነት አደጋ አልነበረም፡፡ መቼም ፈጣሪ ጥበቃው ብዙ ስለሆነ አደጋውን አራቀው እንጂ ከዚህም በላይ ችግር ይፈጠር ነበር፡፡ የሚገርመው እረኞች ከብቶቻቸው ተጎድተውባቸው ከእኛ ጋር መጥተው ይጣላሉ፤ የህግ አካል እስከሚደርስ ትንሽ እንቸገራለን፡ ብዬ ባስብም እረኞች ግን እየበረሩ አድረሻቸውን አጠፍ፡፡ ምክንያቱን ሳጣራ ለካስ ከብቶቹ አጥሩን አልፈው ከተገኙ ቅጣት ስላለው ተይዘው መቀጣት አይፈልጉም፡፡ ምናልባት አደጋውን ያደረሱት ከብቶ ስለሆኑ ይህ ቅጣት ደግሞ ከበድ ሊል እንደሚችል ስለሚገመት የመጥፋታቸው ሚስጢር ለካ እርሱ ነው፡፡ እንደ መንገዱ ፈጣን የሆነ አገልግሎት የሚሰጡት የፍጥነት፡ መንገዱ የሚመለከታቸው ባለሙዎች በፍጥነት ደርሰው እኛንም፡ መኪናችንን አንስተው መንገዱ ቶሎ ለትራፊክ ከፍት አደረጉት፡፡ ከዚያ በሁዋላ እኛን እንደ ኳስ ተቀባበሉን፡፡ እንትና ጋ ሂዱ ስንሄድ፤መጀመሪያ እንትና ጋ፡ እንትና ጋ ስንሄድ ፡ ዛሬ አይመቸኝም፡ ሁሉም ሳይሳካ ሶዶ ሊያድር የነበረው ቡድን ምስራቅ ሸዋ ለማደር ተገደደ፡፡ በቀጣዩ ቀናት ጉዳዩን ለማፋጠን በጠዋት ተነስተን ተፍ ተፍ ማለት ብንጀምርም፡ ካሰብነው በተቃራኒ ባላሰብነው ፍጥነት ጥፋቱ ሁሉ ወደ እኛ እየመጣ መሆኑ ገባን፡፡ አብሮን ፕላን ለማንሳት የሄደው፡ አባል

አባል፡ አደጋው ለምን ተፈጠረ፡ የሚልጥያቄ አነሳ ሹፌር ይመልሳል፡ ፍጥነት ላይ ነበርክ፡ ሹፎር፡- በተፈቀደው ፍጥነት ገደብ ላይ ነበርኩ፤

አባል፡-ለምን ታዲያ አላቆምክም፡

ሹፎር፡-ለማቋም እኮ ሞክሬያለሁ ግን እንሰሳቱ ይፈጥኑ ብዙዎችና ፈጣኖች ስለነበሩ አልቻልኩም፡

አባል፡- እና ጥፋቱ የእንሰሳቱ ነው እያልክ ነው፡

ሹፌር፡- አዎ፡፡

አባል፡-እንሳሰቱ ምን ያውቃሉ፡

ፌር፡- እነርሱማ ምን ያውቃሉ ያው የሚነዳቸው ሰው እንጂ፡

አባል፡- እርሱ ምንያደርግ፡

ሹፊር፡-በዚህ በተከለከለ መንገድ ማምጣት አልነበረበትም፡፡

አባል፡-ሰው አይሰማማ፡ ቢነገረው፡፡

ሹፌር፡ እና

አባል፡- አሁን ጥፋተኛ ነህ አንተ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ሹፎሩ መልስ መስጠት አልፈለገም፡፡ በርግጥ በእኛና በአባሉ መካከል፡የቋንቋ ችግር አለ፡፡ እንዴውም እርሱ ይሻላል፡ አማርኛ ይናገራል፡፡ እኛ ደግሞ አፋን ኦሮሞ አንችልም፡፡  

ልክ በመጨረሻ የመንግስት የስራ ሰኣት ሊበቃ ሰኣት ሲቀር ቅን ሰው አገኘንና ጉዳያችን ለጊዜው ያለቀ መሰለ፡፡ አሽከርካሪችን ግን ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቶት ተለያየን፡፡

አደጋው ከተፈጠረ ከሰዓታት በሁዋላ ለባለቤቴ ስደውል ደረሳችሁ፤ በሰላም ገባችሁ ብላ ጠየቀችኝ፡ ቀስ እያልኩ እያዋዛሁ ሁኔታውን ነግሬያት ነገ ወደ ቤት እንደምመለስ ስነግራት፡ በቃ እንኳን ተረፋችሁ፡ ቅዱስ ሚካኤል፡ በዓሉን ከእኛ ጋር አብረን እንድናሳልፍ ፈቃዱ ሆኖ ነው፡ በሰላም ተመለስ፡፡ እንዴውም፡ የማታው ፕሮግራም ላይ የማትገኝ ስለነበር ጎረቤቶቻችንን  እንዳዘኑ ነግራኝ አሁን በጣም ደስ ይላል፡ በቃ ነገ በጊዜ ና ብለን ተለያይተናል፡፡

እናም ህዳር 12ን ቤቴ ተመልሼ በምሽቱ የሠፈር፡ ፕሮግራም ላይ ከጎረቤትና በተሰብ ጋር እጅግ ደስ የሚል ፕሮግራም አሳልፈን የህዳር 11ኑ ትዝታ ለዘመን ሰጥነው አለፍን፡፡ የቅዱሳን አምላክ የአመት ሰው ይበለን፡፡  

 

Friday, November 25, 2022

ጃፓንን ስናነሳ



         Two Victories from A single game-The Japanese

                                             

22ኛው የዓለም እግር ኳስ፡ ውድድር በአረቡ አለም በኳታር አስተናጋጅነት እየተከወነ ሲሆን ገና ከማለዳው በርካታ ከግምት የራቁ እውነታዎችን ማስተናገዱን፤ ተያይዞታል፡፡ ከ 32 ቱ የኳሱ አለም ተፋላሚ ሀገራት መካከል አፍሪካ 5 ተወካዮች፡ አሏት፡፡ እስከአሁን ከተስተናዱት አዲስ የመሰሉ ክስተቶች መካከል ጃፓኖች የፈጸሙትና ለአለም በተግባር ያሳዩት ድንቅ ስራ ነው፡፡ በርግጥ ለእኔ ዘመን የፌስ ቡክ መረጃ ቃራሚ ትውልድ ካልሆነ በስተቀር ጃፓኖች ጽዳት የህይወታቸው አንድ አካል እንደሆነ ብዙዎች ይመስክሩላቸዋል፡፡  ተማሪ እያለሁ፡ በተለይም እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ሁሌ አርብ አርብ በቡድን እየተመደብን መማሪያ፤ክፍላችንን እናጸዳ ነበር፡ ያም ክፍል ማጽዳት፤ ማጽዳት ከተባለ ማለቴ፤ ነው፡፡ ወለሉን ሞልቶት የነበረውን አቧራና አፈር በቅጠል እየጠረግን በግድግዳ፤ጠረጴዛና ወንበር ብሎም በራሳችን ልብስና ሰውነት ላይ፤ የመቀመጫ ቦታውን እንዲቀየር እናደርጋለን እንጂ እንደማነጻዳው፡ አስታውሳለሁ፡፡ ጃፓን ግን ተማሪ ብቻ ሳይሆን መ/ራን ጭምር ክፍላቸውን እንደሚያጸዱ፡ በአለም ዋንጫው ሰበብ ሰማን፡፡

ጃፓንን ስናነሳ፡ የቶክዮ አሎምፒክ ጀግናችንን አበበ ቢቂላን፡ አንጋፋው የስነጽሑፍ ባለሙያችንን ክብር ዶ.ር ከበደ ሚካኤል ጃፓን እንደምን ሰለጠነች የሚለውን መጽሐፍ፡ ሩቅ ምስራቅ ሳለሁ ጃፓኑዋን ወድጄ በማለት በድምጹ ስለጃፓኑዋ ወጣት ያዜመውን ክቡር ዶ.ር ጥላሁን ገሰሰን፡ እናስታውሳለን፡፡ ጃፓን ተጋጣሚዋን አሸንፋ፡ ደጋፊዎቿ ቡድናቸውን ደግፈው ለጭፈራ አልወጡም፡ ይልቁንም፤ ደስታቸውን በውስጣቸው ይዘው የተቀመጡበትንና ድል ያደረጉበትን ቦታ ጽድት አድርገው፡ ለቀጣዩ ጨዋታ አስተካክለው፡ አለምን አስተምረው፡ ከስታዲዮሙ ወጡ እንጅ፡፡ ይህ በሆነ በሁለተኛው ቀን፡ ከስራ ወደቤቴ ፡ለመግባት ወደ 500 ሜትር ሲቀረኝ፡ የወጣትነት እድሜን በግድ እንለቅም የሚሉ ሶስት ኢትዮጲያዊያን፡ ሲዝናኑ ከቆዩበት ቦታ ከተጎነጩት መጠጥ ጋር በተሰጣቸው አማርዝኛ( አማርኛ እናእንግሊዘኛ) ስለጃፓኖች ጽዳት እያወሩ ሳለ እንድደግፋቸው ይመስላል፡ ደስ በሚል የመጠጥ ፈገግታ ኃሳቤን ጠየቁኝ፡ አንደበቴን ሳላወጣ ድጋፌን እንደነርሱ መለስኩላቸው፡፡ አቦ ይመችሽ ያራዳ ልጅ ብለውኝ የምስጋና ጎርፍ አወረዱልኝ፡፡ ወደ ተመሳሳይ አቅጣጫ ጥቂት እንደተጓዝን አንዱ ወደ ዳር ወጣና የግሉን ቧንቧ ከታችያው የሰውነቱ መንደር አውጥቶ፡ እውነተኛውን ባህሪውን ሲያስተናግድ ጓደኞቹም ሲከተሉት በግርምት ሳያቸው፡ ያራዳ ልጅ የሚለው አንደበት፡ ፈጠን ብሎ ሸባው ምነው፡ አንችም ማስለቀስ፡ አማረሽ እንዴ ብሎ፡አንዱ ሲናገር በሳቅ ፈረሱ፡፡ ሳቃቸውን እንደምን እስከሚጨርሱ ጠብቄ  እኔ እንኳ ቅድሙ ጃፓንን ያደነቃችሁበት ጭውውታችሁ፡ ለምን እናንተስ አልተገበራችሁትም ብዬ ገርሞኝ ነው ስላቸው፡ አባ ከየት ነው ከብልጽግና፤ ከኢዜማ ወይስ ከሊግ ብለው አሁንም በራሳቸው አለም በሳቅ ፈረሱ፡ ከዚያ በሁዋላ መልስ መመላለሱ ተጨማሪ ዳፋ አይጠፋውም ብዬ ወደቤቴ አቀናሁ፡፡ የወጣቶቹ ድርጊት ግን ከውስጤ ቶሎ ሊጠፋ አልቻለም፡ እንዴውም ህዳር 12 ፡ ህዳር ሲታጠንን አስታወሰኝ፡፡

በቀደመው ታሪካችን ህዳር 12 በየኣመቱ ጽዳት ተደርጎ፡ቆሻሻ፤ይቃጠል ነበር፡፡ በዚያ ዘመን በዚያ አስተሳሰብ፤ በዚያ ዘመን በአለ የአለም የአየር ንብረት፡ የሚከወን ስለነበር፡ ስለእርሱ ሂስ ማንሳቱ ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡ የጽዳቱ መነሻ ከታች ያለው ነው፡፡

20ኛው ክፍለ ዘመን በመላው ዓለም 1914 እስከ 1918 .. መነሻውን አሜሪካ ያደረገው በተለምዶ ስፓኒሽ ፍሉ የሚባለው ወረርሽኝ በዓለም ላይ 15 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ህይወት እንደቀጠፈ በታሪክ ይነገራል። ይህ ወረርሽኝ በተከሰተ 10 ወራት በኋላ 1911 . በኢትዮጵያ የበርካታ ዜጎችን ህይወት ቀጥፎ አልፏል። በዚህም ምክንያት ይህ ቀን በርካታ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት በመሆኑ በቀኑም የፅዳት ዘመቻ እንዲደረግ በአዋጅ ተነግሮ ስለነበረ ከዚህ አዋጅ በኋላ እንደ ባህል ተወስዶ በየዓመቱ ህዳር 12 ሲመጣ በአብዛኛው የሀገራችን አካባቢዎች ነዋሪዎች መንደራቸውን የማፅዳት ሥራ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

አሁን በደረስንበት የአስተሳሰብ ደረጃ፡ የአለም ሙቀት መጠን መጨመር የበካይ ጋዞች ወደ ከባቢ አየር በመግባት እየፈጠሩት ካለው፡ ችግርና በአይናችንን እያየነው ካለነው በርካታ ሁነቶች አንጻር ቆሻሻን ሰብስቦ ማቃጠል፡ አይመጥነንም፡፡ ቆሻሻን፤በቡድን በግል፤ በዘመቻ፡ በሳምንታዊ ወርሃዊና አመታዊ በዓላት፡ማጽዳት እጅግ የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡ ግን ግን ሰብሰብነው ቆሻሻ የምናስወግድበት መንገድ አስተማሪ፤ እግርና ከማቆሸሽ አልፎ የመተንፈሻ አካል የሚጎዳ ይባሱኑ ከባቢ አየሩም የሚጎዳ መሆን የለበትም፡፡ የአፍሪካዊያኑ መዲና፡ አዲስ አበባ ባለስልጣናት ግን ትጥቃቸውን አሳምረው፡ ህዝባቸውን አስከትለው፡ ለጽዳት መውጣት እንጂ ስለአወጋገዱ ብዙ የሚገዳቸው አይመስልም፡፡ ገራሚው ነገር ደግሞ የሀገሪቱ ብሎ የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ፡ባለስልጣን ጽ/ቤቶች መቀመጫ እዚሁ አዲስ አበባ ሆኖ፡ ችግሩ ፡ ግን መቀጠሉ ነው፡፡( ለችግሩ አለመፈታት የሁላችንም ችግር ቢሆንም መ/ቤቶቹ ግን የተሰጣቸው ተግባርና ኃላፊነት ጭምር ስለሆነ ብዬ ነው፡ ደግሞ እኮ ባለስልጣን ነው) ከታች የተያያዙት ሁለት ሳንሳዊ ጥናቶች በተለይም አንዱ ከህዳር ሲታጠን ጋር ቀረበ ግንኙነት ስላለው፡ ቆሻሻን ማቃጠል ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው ያስረዳናል፡፡C:\Users\user\ENAB Dropbox\Wogderes Ejigu\PC\Desktop\Impact of open burning of refuses on air quality.pdf

C:\Users\user\ENAB Dropbox\Wogderes Ejigu\PC\Desktop\Toxic substance from plastic waste.pdf

ማጠቃለያ፤ ቆሻሻን ማጽዳት ልምዳችን ይሆን ፡ ቤታችንን አጽድተን በግቢያችን ግቢያችንን አጽድተን በመንገድ ላይ ቆሻሻን በመድፋት፤ አግባባዊ ባልሆነ መንገድ ቆሻሻን ማስወገድን ግን ልናስቀር;

ይገባል፡፡Description: World Cup: Japa Fans Clean Up Stadium after Historic Win ...


Friday, November 11, 2022

ተው ዘገየህ

ዛሬ ህዳር 1/2015 . ወደ ስራ ሳመራ የተሳፈርኩበት ተሸከርካሪ፡ ውስጥ ከአንድ ሬዲዮ ጣቢያ የተለቀቀ ቆየት ያለ ዘፈን በድንገት ማሰማት ሲጀምር ሶስት አስርት አመታትን ወደ ሁዋላ ይዞኝ በትዝታ ሸመጠጠና ሳላስበው ሳቅሁ አንዲት እናት ምነው ልጄ ምንአይተህነው የምትስቀው ብለው እስኪያናግሩኝ ድረስና ከትዝታ ባህር ሳልሰጥም ሲያወጡኝ ነበር ውስጤ የተናጠው፡፡ ባለቤቴ ይህንን ዘፈን አልሰማችሁ ካልሆነ በስተቀር ትደውልልኝ ነበር፡ታሪኩን ስለምታውቀው፡፡

ከሠላሳ አመት በፊት አንድ ጥፋት አጠፋሁና ብዙም፡ማገናዘብ፤ ባልቻልኩበት የለጋ ዕድሜ አንድ ከናድ ውሳኔ ወሰንኩ፡፡  የጥፋቱን ክብደት፡ በዚያ ዘመን የማገናዘብ ችሎታዬ ሳስበው፡ከባድ ስለነበር ራሴን፡ ካደግሁበት ቦታ መሰወር ወይም መሞት ነበር፡ውሳኔ፡፡ ተወልጄ ካደኩሁበት ቦታ  ወደሌላ ቦታ መጥፋትና ራስን መሰወር ወይንም በኪሴ የነበረችው አስራ ሰባት ብር እካለቀች ድረስ በህይወት መቆየት ከዚያ በሁዋላ የክብር ሞት መሞትን መረጥሁ፡፡ ለዚያች ጥፋት ሞትን መምረጤ ምን ያክል የገዘፈ ጥፋት እንደሆነ የገባኝ አንዲት: የቅርቤ የምላት ነርስ ጓደኛዬ የአንድ ህመምተኛዋን ታሪክ ባወጋችኝ ጊዜ ነው፡፡ ጓደኛዬ እንደነገረች፡ህምተኛዋ ራሱን ለማጥፋት መርዝ ጠጥቶ ለመሞት እያጣጣረ ሳለ፡ የአካባቢው ሰው፡ የወሳንሳ ይዘው  እርስዋ ወደምትሰራበት ጤና ጣቢያ ወስደውት የመጀመሪያ ርዳታ፡ እንዲያገኝ፡ በሚደረግ፤ ግብግብ ውስጥ ወተት ፈልጉ ብላ  ወተት ተፈልጎ መጥቶ እንዲጠጣ  ሲቀርብለት ፡ አስገራሚውም ግለሰብ፡ዛሬ ረቡዕ ነው እኔ እጾማሁ አልጠጣም ያለውን የታማሚዋን ታሪክ ነግራኝ፡ አምላክ የሰራውን ቤተመቅደስ ሰውነቱን ለማፍረስ ህግ አልፈራ፡ ጾም መሻር እንቢ አለ ቤተክርስቲያን ያላት ትውልድ ይህ ነው ስትለኝ፡ በታማሚዋ በኩል አርጩሜው ለኔም ነበር የደረሰኝ፡፡

ወደ ቀደመው ትዝታዬ ልመለስና፡ራሴን ችዬ ከወላጆቼ ቤት እስከወጣሁበት ድረስ ያለወላጆቼ፤ እውቅናና ፈቃድ ውጭ ያደርኩት በእነዚያ 3 ቀናት ብቻ ነበር፡፡ የጠፋሁበት ጉዳይ ያስጠፋ ነበር ወይስ አያስጠፋም የሚለው ብዙ አነጋጋሪ ቢሆንም ለእኔ ግን በዚያን ወቅት ትልቅ ጥፋት ነበር፡፡ እኔ ጠፍቼ ወላጆቼና ዘመዶቼ በወርሃ ነሀሴ 3 ቀናት የለፉትን ልፋትና እንግልት ሳስበው ውስጤ ያዝናል፡፡እድሜ፡አቻዬ ከእናቴ ጋር ውሃ ወስዶት ነው እያሉ ወንዝ ውስጥ ሲፈልጉ ወራጅ ውሃ ሊወስደው በመከራ ነበር የተረፈው፡ አብሮኝ ይማር የነበረና ትምህርቱን አቋርጦ የነበረ ሌላ ጓደኛዬን አንተ የት እንደሄደ ታውቃለህ አምጣ እያሉ ያስጨነቁት፤ ሌላም ሌላም ነገር ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡ በጣም የሚገርመው ይህ ሁሉ ሰው፡ እኔን ለመጥፈት ያነሳሳኝ፡ ጥፋቱን ቢያውቅ ምን ያክል እንደሚስቅብኝ ነው፡፡

እና በዚያ በወርሃ ነሐሴ 1314 እና 15 አንድ ከተማ ላይ ቁጭ ብዬ ውሎየን የማሳልፈው ሙዚቃ ቤቶች አቅራቢያ ነበር፡፡ ይህ ዛሬ የሰማሁት ዘፈን አዲስ የወጣና 2 አንጋፋ ወንዶችና 2 አንጋፋ ሴቶች፡ በቅንጅት ያወጡት ነበር፡፡ በሙዚቃው መካከል ስለሙዚቃው የሚነገር ማስታወቂያ ሙዚቃውን ተከትለው አብረው የሚዘፍኑየሚጨፍሩና የሚደንሱ ታዳጊዎች፤ከመንገዳቸው እርምጃቸው ቀንሰው ሙዚቃውን የሚሰሙ ሰዎች መንገዶኞች፤ ጫማዎቻቸውን፡ የሚያስጠርጉ፡ ሰዎች፤ ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ሰሜን ኢትዮጲያ የሚጓዙ ሀገር አቋራጭ አውቶቡሶች፡ጋሪዎች ሁሉም፡ ነገር አሁንም ፍንትው ብሎ ይታየኛል፡፡ እናም ዛሬ ያንን ዘፈን ስሰማ፡ ያሁሉ ትዝታዬ ነበር ፊቴ የተደቀነው፡፡ በወላጆቼ ብርታትና በአምላክ ፈቃድ እራሴን አጣፈለሁ ያልኩት ልጅም ራሴን ሳላጠፋ መሀል መንገድ ላይ አባቴ አገኘኝ፡፡ አባቴ ከርቀት አይቶኝ ስሜን ሲጠራ፡ እንባዬን ለቀቅሁት፡ የአባቴ እንባ ዛሬም ይታየኛል፡፡ ልክ ከሞት የተነሳሁ ያክል ነበር፡ ፊቱ የደስታ ጸዳል ሞልቶታል ግን ያለቅሳል፡፡ አባቴ እኔ ላልቅስልህ በጥፋቴ፡ አስለቀስኩህ፡፡ እና ያወደ ሁላ በትዝታ ያስኬደኝ ዘፈን መሀሙድ አህመድና ብዙነሽ በቀለ 

ተው ዘገየህ አንተ ዘው ዘገየህ ቆሜ

መራመዴን መሄዴን እያየህ፡፡ በመባባል በቅብብል፡

የሚዜሙት ዜማ ነበር፡፡

ትዝታ መልካም ነው፡ ያንን ሁሉ ጊዜ አስታወሰኝ፡፡


                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...