Friday, May 29, 2026

 

                          ገበር አምባ

                   ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች

                      በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡

                     ጊዜው ሲለዋወጥ ሁሉም ጥሎ ሸሸ

                      ትርንጎ ሚመስለው ጉንጭሽም ሟሸሸ፡፡

                      ስንቱ ነበር ያንች ፍቅር ያሳበደው

                     ውበት ቁንጅናሽን ዛሬ ማን ወሰደው፡


ልጅ ደግሞ አይራበው እንጂ መቀጣት ምን ይጎዳዋል፡ የሚለው አባባል የሠፈራችን ሰዎች በተለይም ከእናቶች፤ አፍ ላይ የማጠፋ ቃል ነው፡፡ በደንብ እስከምንጠግብ አብልተው ማሳረጊያው ኩርኩም፤ ልንበላም ስንዘጋጅ እስኪ እጅህን ታጠበው አቧራህንም አራግፈው ኩርኩም የምግቡ ማጠፋጫና ማሳረጊያ ነው፡፡ እኔ በተለይ የምበላው የማያጠግበኝ ከበላሁም በሁዋላም ቢሆን ሆዴ የማይቆይ ይመስለኛል፡ ከምግብ በፊትና በሁዋላ ኩርኩም ካልተጨመረልኝ፡፡ አንዳንዴ ጊዜ ጠዋት ት/ቤት ስሄድ ምክንያት ፈልጌ የምመታበት ሁሉ ትዝ ይለኛል፡፡ በቀልድ ሰአት ለምንድነው እንደዚህ የምታደርገው ተብሎ ጠየቅ አይ እኔ ትዬ(እናቴ) ካልመታኝ አይቀናኝም እል ነበር፡፡ ይህ፤ መመታቴ ሁሌ ያናድድደው የነበረው የእናቴ ልጅ ታላቅ ወንድሜ ለምን ጣፋለህ፤ሁሌም ትመታለህ ሲለኝ እኔ ትዬ(እናቴ) ካልመታኝ አይቀናኝም እያልኩ እነግረው እንደነበረ አሁንም ያነሳዋል፡፡ እኔ ብቻ አይደለሁም ታላላቆቼም ታናናሾቼም፤ የአጎቴ ልጆችም ሁላችንም እንመታለን፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በኩርኩም ስንመታ እናቶቻችን እጃቸውን ስለሚያማቸው፤ ኩርኩም የጋራ በትር ነው፡ይላሉ፡፡

ተወልጄ ያደኩባት ሠፈር ገር አምባ ትባላለች፡፡ የስሟን የትመጣነት ማንም አያወቅም፡፡ ገር አምባ ከምስራቅ ላይ አምባንና ዳዎ ኢየሱ ቤተክርስቲያንን፤ ከምዕራብ ታች አምባን፤ከሰሜን መረሬን ከደቡብ የጨለለቂት ወንዝ ተዋስና በአንጻራዊነት ከፍ ያለ ቦታ ላይ ትገኛለች፡፡ ከላይ አምባ እና በከፊል ከመረሬ የሚመጣው ውሃ በሰፈራችን ግራና ቀኝ ባሉት መለስተኛ ቦዮች አድርጎ ቁልቁል ወደ ጨለለቂት ወንዝ ይንደረደራል፡፡ ልጆች እያለን ክረምት ክረምት፤ ቦዮቹን ገበን ፏፏቴ እየሰራን፡ ጭቃውን በደንብ እያደለጥን መልሰን ራሳችን የምንወድቀበትን ጨዋታ የሰፈራችን ህጻናት ሁሉ የዘመን ትዝታ ነው፡፡ ሰፈራችን ጥቅጥቅ ባለ የቁልቋል አጥር የታጠረ ሲሆን፡ በመካከል የአባቴ ወላጆች ቤት ዙሪያውን የአባቴ፤ የሁለቱ አጎቶቼ ቤት፤ የአያታችን ወንድም ቤት፤ በሚቀጥለው በቁልቋል በታጠረ ግቢ ውስጥ የእማማ መርሻ፤ የጋሸ አስራቴና የአለሙ ቤት፤ ከዚህ ቀጥሎ በሌላ ቁልቋል አጥር ውስጥ የጋሸ ወርቁና የእኩያዬ የእነአብራራው ቤት አለ፡፡ የእኛ ሰፈር ሰዎች ያላቸው ቅርርብ በጣም ደስ የሚል ነበር፡፡ የሁሉም ቤት የእንጀራ መሶብ ለሁላችንም ልጆች የጋራ ነው፡፡ ከውጭ መጥቼ ወይንም የአቶቼ ልጆች ከውጭ መጥተው ወላጆቻችን ከሌሉ አንደኛው ቤት ገብተን ረሃባችንን እናስታግሳለን፡፡ ልጆቹ በጣም ስለምንቀራረብ ወላጆቻችንም በጣም ይቀራረባሉ፡፡ የዛሬ አያድርገውና እኔና የታላቁ አጎታችን ሴት ልጅ ያለን ቅርርብ፤ እጅግ የሚገርም ነበር፡፡ ከእኛ ቤት ሲያባርሩን እነርሱ ቤት ከእነርሱ ቤት ስንባረር እኛ ቤት፤ ከሁለቱም ስንባረር አጥር ስር ሆነን የምናወራው ወሬ፤ ለቤተሰቦቻችን ቅርርብ የራሱ አስተዋጽ ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ከሰው አልፎ እንሰሶቻችንም እርስ በርሳቸው ይተዋወቃሉ፡፡ የሁላችን ከብቶች ሜዳ ተለቀው ማታ ሁሉም ተከታትለው በተመሳሳይ ሰአት ያለምንም ፈላጊ አብረው ይመጣሉ፡፡ ይህንን የሚያውቁ የላይ አምባ ሰዎች ገረ አምቦች ሰዎቹ ቀርቶ እንሰሳቶቻቸው ይተዋወቃሉ ይላሉ፡፡

ታላቁ አጎታችን በጣም ታታሪ ገበሬ፤ በስራ ቀልድ የማያወቅ፤ ስራ ካለ አይደለም እርሱ ቤተሰቡም አያርፍ፡፡ ሲበዛ ጎበዝ ገበሬ ነው፡፡ ስራውን ጨርሶ አረፍ ሲል ደግሞ ተጫዋችነቱ፤ሰው ተራቢነቱ፤ ከማንም አይገጥምም፡፡ ማታ ማታ ድድ ማስጫ በሚባለው እኛ አጥር ስር ባለው መቀመጫ ቁጭ ተብሎ የሚደረገው ጨዋታ ላይ እርሱና እኔ ታላቅ ወንድም ከሌሉ በፍጹም አይደምቅም፡፡ ታላቁ አጎታችን ማንንም ለመተረብ ሲፈልግ አቆላምጦ ነው የሚጠራው፤ ለምሳሌ የእኔን ወንድም ቀለመወርቅ ነው ስሙ፤ቀለም ብሎ ነው የሚጀምረው፤ እርሱም ስሚገባው ሺ ደግሞ ምንልትል ነው ሲለው ደግሞ ምናባክ እልሃለሁ ይላል፤ ከዚያ በቃ ተረብ ተጀመረ፡፡ ትንሽ ትልቁ ዘመድ ከባዳ፤ እዚያው አጠገብ ያለ ሰው ይተረባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሁሌም ደስተኛ የማይሆነው አባቴ ነው፡፡ አባቴ መጨወት፤መቀለድ ይፈልግና ይመጣል፡፡ ግን ሌሎች ሰዎች በተለይም እርሱ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ስማቸው በተረብ ሲነሳ ይቆጣል፡፡ ትልቁ ተራቢ ደግሞ የእኔ ወንድም ስለሆነ፤ እርሱን ስለሚቀጣው፡ አባቴ ያለ ዕለት ድድ ማስጫ ቀዝቀዝ ይላል፡፡ በሂደት ተመካክረው ይመስለኛል፡ አስቀድመው ወንድሜና አጎቴ አባቴን ሲተርቡት ደግሞ ጀመራችሁ፤አንት ትልቅ ሰው አይደለህም ብሎ ወንድሙን ተናግሮ፤ ተነስቶ ይገባል፡፡ የድድ ማስጫው ሰአት በጣም፤ ሲቆይ ወንድሜ ቢጠራም መጣሁ እያለ ስለሚቆይ ራቱን ተቀምጦለት ብቻውን ይበላል እንደነበር አልዘነጋውም፡፡ ትልቁ አጎታችን፡ ተረቡ ማንንም ነው፡፡ የራሱን ልጆች ተርቦ አስለቅሶ ከድድ ማስጫ ወደ ቤት ሊያስገባቸው ይችላል፡፡ አፈሩን ገለባ ያድረግለትና አዲሱ የሚባለው ልጁ እያደገ ሲመጣ መልሶ እርሱንም ይተርባል እንጂ በፍጹም ከጨዋታው አይለይም ነበር፡፡ እየቆዬ ሲመጣ ግን መታዘብ የቻልኩት ልቹ የራሳቸው ግሩፕ ፈጥረው ሲተራረቡን ስሰማ ተረብ ከላይ ወደታች እንደወረደ እንገነዘብ ነበር፡፡

የአባቴ ታናሽ ወንድም ገና በጎልሳ እድሜው ነው፡ በሞት ያጣነው፡፡ እርሱም ተራቢ፤ተጨዋች ነው፡፡ ተረቡ በተለይ ከታላቅ ወንድሞቹ ሚስቶች ጋር በጣም ይለያል፡፡ ጠዋት ጠዋት ድምፁን ከፍ አድርጎ ዳዊት ይደግማል፡፡ ወላጅ እናቴ በቅርብ ርቀት ትሰማዋለች፡ ዳዊት መስማት ስለምትወድ፡ አልፎ አልፎ ተው ተው እንደርሱ አይነበብም ድገመው፤ ጸያፍ ነው ትለዋለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይደግማል፤ አንዳንድ ጊዜ ምን እርስዎ ብሎ ሊተርባት ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሁለቱ አይንና ናጫ ናቸው፡፡ ከመንገድ ሲመጣ፤ በጣም ከራበው፤ በሩ ላይ የእኛ ቤት ስላለ ይገባና ሞትኩ አጉርሱኝ ይላታል እናቴን፤ ሁለት ሶሰት ጊዜ ካጎረሰ በሁዋላ አይ አይጣፍጥም፤ ድሮም እንደእኔ ሚስት ሙያ የላችሁ ብሎ ተሳድቦ ይሄዳል፡፡ ሌም ገዜ ይደግመዋል፤ እናቴም መሳደብህ አይቀር ብላ ትሰጠዋለች እርሱም ይሳደባል፡፡ ይህንን ታላቅ አጎታችን ባለቤት ላይም ያደርገዋል፡፡ የእኔ ሚስት ሙያ ማንም አይደርሳባትም፤ ብሎ ጎራውን ይነዛባቸዋል፡፡

ይህ ታናሽ አጉቴ ሲበዛ ከሰው ጋር ተግባቢና ብልጥ ነው፡፡ ብዙ ስራዎቹን ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ወይንም በትንሽ ዋጋ ያሰራል፡፡ ለዚህ ምስክሩ እኔና የታላቁ አጎታችን የእድሜ እኩያዬ አበበ ነን፡፡ አጎታችን ረጅም አጥር ሲያጥር ቁልቋል እየወጋን፤ ጉድጓድ ቆፍረን አጥር ሲያሳጥረን እዋለ የሚሰጠን ለጂራፍ መስሪያ የግራር ልጥና ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ ፈለጋችሁትን ያክል ጭራ ከፈረሴ ወስዳችሁ ለጂራፋችሁ ይለናል በዚህ ተስፋ ሲያሰራን ውሎ ልጥ ይሰጠናል፡፡ ፈረሱን ፈቅዶልናል ብለን ሄደን ከፈረሱ ጭራ ስንነጭ በፍቅር ጠርቶ ገርፎን ጭራውን ነጥቋናል፡፡ አወቀ የሚባል በእድሜ ከእርሱ ብቻ ሳይሆን ከአባቴ ሁሉ ታላቅ የሆነ ሰውን ጋሸ አቅዬ እያለ ብዙ ስራ ያሰራል፡፡ ሰውየውም ስለሚወደው ከቤቱ አይጠፋም፡፡ ትልቁን የአጎቴን ልጅ ሰፈሩ ሁሉ ሲፎግረው የአወቀ ልጅ ይሉታል፡፡ ልጁም እንደዚህ ያለውን በድንጋይ ሲወራወር ይውላል፡፡ በተለይ የእኔን እናት፡ ምንም፤ሳትል ከአባቱ ጋር ከሆነ፤ አባትየው ምንድ ነው ያሉት ልጄን እርሱ እኮ የኔ ነው ካለ በቃ የድንጋይ መአት ያወርደዋል፡ ቤት ሁሉ ያዘጋታል፡፡ አይ ልጅነት ደጉ፡፡

የአባቴ ታናሽ ወንድም ሃይለኛ የሆነ የሆድ ህመም አለበት፡ በጣም ያሰቃየዋል፡፡ በህይወቴ የማልረሳው 1982 ዓ.ም ክረምት/ነሀሴ/ ቅዳሜ ቀን ነው፡፡ የዚያን ዕለት ታላቅ ወንድሜ ጥርሱን አሞት በጣም ይሰቃያል፡፡ አጎቴም ሆዱን አሞት ሲሰቃይ ከጎረቤት ይሰማል፡፡ ወላጅ አባቴ አዲስ አበባ ነው ያለው፡፡ ታላቅ እህቴ፤ከሁለት ህጻን ልጆቿና ሌላው ታላቅ ወንድሜ እናቴ፤ አያቶች ጋር ሄደዋል፡፡ ድንገት በግምት 3 ሰአት አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የከባድ መሳሪያ ተኩስ መሰማት ጀመረ፡፡ በዝናብ እርሶ የነበረው መሬት ከባድ መሳሪያው ሲተኮስ ይነቃነቃል፡፡ የተቀመጥንበት መሬትለ አልጋው ሁሉ መነቃነቅ ጀመረ፡፡ የከባድ መሳሪያውን ተኩስ ተከትሎ፡ አብሪ ጥይት መተኮስ ሲጀምር ሰማዩ በብርሃን ተሞላ፡፡ ተሱ ቀዝቀዝ ሲል ሁላችንም እናታችንን ቀሚስ ይዘን፡ ከሁሉም ቤት ሌላው ቤተሰብ ወጣ፡፡ ከላይ ሰፈር ያሉትም ወጡና መካከል ላይ ሆነን ምን እንደሆነ ሁሉም ግምቱን ሲገጽ ፤ፍካሬ እየሱስና ነበቡት እናቴና ያመው የነበረው አቴ በቃ ሽሽታችሁ በሰንበት ወይንም በክረምት አይሁን ብሏል፤ የምድር መጨረሻ ነው እያሉ የፍርሃት ድባቡን ከፍ አደረጉት፡፡ እናቴ ወይኔ ልጆቼ ትላለች ቤት የሌት ልጆቿን እየጠራች፤ ወይኔ እጅ ትላላች ቤት የሌለው ባለቤቷን እየጠራች፡ በዚህ ቀውጢ ሰአት ተኩሱ እንደገና ሲጀመር ሁላችንም ተራሩጠን ወደቤታችን ገባን፡፡ ከትንሽ ቆይታ በሁዋላ ተኩሱ ጸጥ ሲል፡ ሁላችንም በራሳችን ሃሳብ ገብተን ሳለ፡ ጥርሱን ሲያመው የነበረው ወንድማችን ድንገት አሰይ ጥርሴን ተሻለኝ አለና በሳቅ ፍርሃታችን አስወገደልን፡ እናቴም ተረበኛ ስለነበረች ጆሮዋን ጣል አድርጋ ድምጽ ስታጣ ወይ ወርቅየንም( አጎታችንን) ሆዱን ተሻለው ስትለን፤ ቤቱ በሳቅ ፈነዳና እንደገና ወደ ነበርንበት አለም ተመለሰን፡፡ በነጋታው ጉዳዩ ሲጣራ ለካስ ወታደር የተግባር ልምምድ እያደረገ ነው፡፡

 

Wednesday, May 27, 2026

 

           

-----------ለገሰና ጌቱ-------

ስራ በያዝኩ 2 አመቴ አብረውኝ የነበሩትና የአንድ አመት ወንድሞቼ ለገሰና ጌቱ ስራ በመልቀቃቸው የተነሳ፤ ጓደኛ አልባ ሆኛለሁ፤ ሰንበት /ቤት ሙሉ ሃላፊነት እኔ ላይ ነው፤ካለኝ ልምድና እውቀት አንጻር ከአቅም በላይ ሆኖብኛል። በአፌ ተስፋ ባልቆርጥም ውስጤን ድክም ብሎታል፤ /ትቤትን መተው አልችልም፤አደራ አለብኝ። ወላጅ እናቴ አደራ ከቤተክርስቲያን እንዳትርቅ፤ ብላኛለች፤ ግቢ ጉባኤ ስንማር አደራ ተቀብያለሁ፤ ከለገስና ጌቱ ጋር እያለሁ በተግባር ያየሁት ትጋት አለ፤ይህንን ሁሉ እዳ ተሸክሜ መራቅ ስለማልችል በመውደቅና በመነሳት መካከል እያለሁ ከዕለታት በአንዱ ቀን ጫማ ላስጠርግ ሊሰትሮ ጋር ቁጭ ብዬ አንዲት ለከተማ እንግዳ የምትመስል ሴት ከቤት አከራዮቼ ልጅ ጋር ወደ እኔ ሲመጡ በሩቅ እየተመለከትኩ ነበር። ወደ እኔ ሲመጡ ፈገግ እያለች መጥታ ስሜን ጠርታ ለሰላምታ አቀፈችኝ። የት እንደማውቃት ግራ ገብቶኛል። እርሷ ግን አጥብቃ ሰላምታ አቀረበችልኝ። ጫማ ማስጠረጉን ጨርሼ ወደቤት እንሂድ ብያት መራመድ እንደጀመርን አስታወስከኝ አለችኝ፤ ግራ በመጋባት ይቅርታ ጠይቂያት እንዳላወቅሁዋት ስነግራት ትከሻዬን ያዝ አድርጋ ቅድስት ቦቦሻ እባላለሁ፤ "ማህበረ ቅዱሳን የትም ብትገባ አይተውህም" አለችኝ። ስሟን አውቀዋለሁ ግን ሁለት አመት አለፈው እንዴት ይሆናል ብዬ ስጠራጠር፡ "አርባምንጭ ማዕከል ያሉ ወንድሞች እዚህ እንዳለህ ስለነገሩኝ ለስራ ስመጣ ሳልጠይቅህ አልሄድም ብዬ ነው አለችኝ።" ቅድስትን አስታውሻት እንደገና እንደአዲስ ሰላምታ አቀረብኩላት። ቅድስትን የማውቃት ከባህርዳር ተመርቄ ወደዞን ለመመደብ ክልል ላይ እጣ ለማውጣት ሄድን ስለነበር፤ በዚያ ካሉ የማህበረ ቅዱሳን የሃዋሳ ማዕከል ወንድሞችና እህቶች ጋር በተዋወቅን ጊዜ ነበር። የተወሰኑ ቀናት እዚያ ያሉ ወንድሞቻችን ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቀጥረውን ያወሩን ያበረቱን ነበር። እኔ ግን ከስራ ሰአት በሁዋላ ወደ አጎቴ ቤት ስለምሄድ በጊዜው ከነበሩ የሀዋሳ ማዕከል አባላት ጋር ብዙ አልቆይም ነበር። የሚገርመው ቅድስት የጽዋ ዳቦ ይዛልን መጥታ እኔ ስላልነበርኩ ነገ ጥዋት ስጡት ብላ ዳቦ በአደራ የሰጠችህ ንጹህ እህቴ ነበረች። መልካምነቷ ነው እንግዲህ አለሁበት ድረስ ፈልጋ መጥታ እንድትጠይቀኝ ያስገደዳት። ቅድስት ብላቴ ዘምቶ የነበረው የዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ባች ስትሆን ማህበረ ቅዱሳንን ከመሰረቱ ቀደምት አባላት አንዷናት። ቅድስት መጥታ ከጠየቀችን በሁዋላ ከቤተክርስቲያን በፍጹም መራቅ እንደማልችል ለራሴ ቃል ገባሁ።

ለገሰና ጌቱ ከእኔ በፊት ሁለት አመታት በበሌ ከተማ ውስጥ በመምህርነት አገልግለዋል። ከተመረቁበት የመ/ርነት ሙያ ባሻገር ሁለቱም ባለችው ጸጋ ቤተክርስቲያንን ያገለግላሉ። ለቤተክርስቲያና ያላቸው ቀናኢነት ሰው መውደዳቸው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድቀርባቸው አድርጎኛል። የተከራየነው አንድ ግቢ ሲሆን ሁለቱ በአንድ ቤት ይኖራሉ። ከተወሰኑ ወራቶች ቅርርባችን በጣም ስለተጠናከረ ለመኝታ ወደ የቤታችንን እንሄዳለን እንጂ በገባንበት ቤት በልተን እዚያው እንቆያለን። ቤተክርስቲያን ያለው ሰ/ትቤትም ሆነ መደበኛው የእሁድና ሰርክ አገልግሎት ሁሉ ሃላፊነቱ በእነርሱ ላይ ስለነበር እኔም ሳላስበው ሙሉ በሙሉ ገባሁበት። አጋጣሚ ሆኖ መንገድ ስራው ኣመጣቸው በርካታ ወንድሞችና እህቶችም ስለነበሩ፤ ቤታችን ሰው አይጠፋበትም። ብዙ ነገሮች የሚከናወኑት በጋራ ነው። ይህ መሆኑን ኑሮን ከማቅለል ባለፈ የቤተክርስቲያን አገልግሎትም ላይ ትልቅ መልካም ጎን እንዲኖረው አድርጎልን ነበር። ግቢ ጉባኤ ጀምሬውን የነበረውን የመዝሙር አገልግሎት በሰ/ት/ቤትም ማስቀጠል ጀመርኩ። ለገሰና ጌቱ በስብከትም በዝማሬም አገልግሎት የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ። ለገሰ ቅዳሜና እሁድ በአብዛኛው ገጠር ወዳሉ ቤተክርስቲያናት ይሄዳል፤ በአስተርጓሚ ይሰብካል። እግዚአብሔር ከሰጠው የማስተማር ጸጋ ባለፈ ትላልቅ አይኖችን ሲያጉረጠርጥ፤ በርካታ ሰዎች ስለሚፈሩት የተጣሉ ካሉ እና እርሱ ካለ ያስታርቃል። እርሱ ፊት ሳቅ ጨዋታ የለም፤ ሁሉም ነገር ኮስተር ያለ ነው። ይህ ኩስትራናው እኔና ጌቱ ዘንድ ግን ቦታ የለውም፤ እኛም ኮስታራ ስለመሆኑን አናውቅም እርሱም ልኮሳተር ቢል እንደማይሆን ስለሚያውቀው፤አይኮሳተርም፡ ነገር ግን አንዳንዴ ኮስትራናው ለእኔ ይከብዳል። አንድ ቀን ስጋ አምቦ ውሃ መጠጣት ፈለገን፤ መሸት ሲል ወደ ሆቴል አመራን። ከተማዋ መብራት ስለሌላት አንድ ሆቴል ላይ የማሾ መብራት አለ። መብራቱ ዋናው ቤት ሲሆን ከፊትና ከሁዋላ ከዋናው ቤት ውጭ ያሉት ውጭ መስተናገጃ ከፍሎች ግን ወጋገን እንጂ ብርሃኑ ስለማይደርስባቸው በደንብ አይታይም፤ በለገሰ ሃሳብ አፍላቂነት በጓሮ በኩል ባለው መቀመጫ ተቀመጥን። ቁጭ እንዳልን ጌቱ አይ ይህ ቦታ አይሆንም ውስጥ እንግባ አለ፤ ለገሰ አይሆንም እዚያ ብዙ ሰው ቢራ ይጠጣል፤ እዚህ ነው መሆን ያለብን አለ፤ በሁለቱ መካከል በነበረው ረጂም ሰአት ክርክር ሊታዘዝ የመጣው ልጅ ሁለት ሶስት ጊዜ ተመላለሰ፤ በዕለቱ በክርክሩን የሚሸነፍ ስለጠፋ፡ አምቦ ውሃውን ሳንጠጣ ወደ ቤት ተመለስን። ስንመለስ ሁለቱም ለየብቻቸው ስለሆነ እኔ ከማን ጋር እንደምሆን ግራ ገባኝ፤ ጭንቀቴን የተረዳው ለገሰ እየሳቀ አብራችሁ ሁኑ እለ በምልክት ወደ ጉቱ እንድሆን ያሳየኛል። ጥዋት ስንገናኝ ሁሉም ነገር ተረስቶ እየተሳሳቅን ነበር ወደ ስራ አብረን የሄድነው። 

 

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...