Wednesday, May 27, 2026

 

           

-----------ለገሰና ጌቱ-------

ስራ በያዝኩ 2 አመቴ አብረውኝ የነበሩትና የአንድ አመት ወንድሞቼ ለገሰና ጌቱ ስራ በመልቀቃቸው የተነሳ፤ ጓደኛ አልባ ሆኛለሁ፤ ሰንበት /ቤት ሙሉ ሃላፊነት እኔ ላይ ነው፤ካለኝ ልምድና እውቀት አንጻር ከአቅም በላይ ሆኖብኛል። በአፌ ተስፋ ባልቆርጥም ውስጤን ድክም ብሎታል፤ /ትቤትን መተው አልችልም፤አደራ አለብኝ። ወላጅ እናቴ አደራ ከቤተክርስቲያን እንዳትርቅ፤ ብላኛለች፤ ግቢ ጉባኤ ስንማር አደራ ተቀብያለሁ፤ ከለገስና ጌቱ ጋር እያለሁ በተግባር ያየሁት ትጋት አለ፤ይህንን ሁሉ እዳ ተሸክሜ መራቅ ስለማልችል በመውደቅና በመነሳት መካከል እያለሁ ከዕለታት በአንዱ ቀን ጫማ ላስጠርግ ሊሰትሮ ጋር ቁጭ ብዬ አንዲት ለከተማ እንግዳ የምትመስል ሴት ከቤት አከራዮቼ ልጅ ጋር ወደ እኔ ሲመጡ በሩቅ እየተመለከትኩ ነበር። ወደ እኔ ሲመጡ ፈገግ እያለች መጥታ ስሜን ጠርታ ለሰላምታ አቀፈችኝ። የት እንደማውቃት ግራ ገብቶኛል። እርሷ ግን አጥብቃ ሰላምታ አቀረበችልኝ። ጫማ ማስጠረጉን ጨርሼ ወደቤት እንሂድ ብያት መራመድ እንደጀመርን አስታወስከኝ አለችኝ፤ ግራ በመጋባት ይቅርታ ጠይቂያት እንዳላወቅሁዋት ስነግራት ትከሻዬን ያዝ አድርጋ ቅድስት ቦቦሻ እባላለሁ፤ "ማህበረ ቅዱሳን የትም ብትገባ አይተውህም" አለችኝ። ስሟን አውቀዋለሁ ግን ሁለት አመት አለፈው እንዴት ይሆናል ብዬ ስጠራጠር፡ "አርባምንጭ ማዕከል ያሉ ወንድሞች እዚህ እንዳለህ ስለነገሩኝ ለስራ ስመጣ ሳልጠይቅህ አልሄድም ብዬ ነው አለችኝ።" ቅድስትን አስታውሻት እንደገና እንደአዲስ ሰላምታ አቀረብኩላት። ቅድስትን የማውቃት ከባህርዳር ተመርቄ ወደዞን ለመመደብ ክልል ላይ እጣ ለማውጣት ሄድን ስለነበር፤ በዚያ ካሉ የማህበረ ቅዱሳን የሃዋሳ ማዕከል ወንድሞችና እህቶች ጋር በተዋወቅን ጊዜ ነበር። የተወሰኑ ቀናት እዚያ ያሉ ወንድሞቻችን ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቀጥረውን ያወሩን ያበረቱን ነበር። እኔ ግን ከስራ ሰአት በሁዋላ ወደ አጎቴ ቤት ስለምሄድ በጊዜው ከነበሩ የሀዋሳ ማዕከል አባላት ጋር ብዙ አልቆይም ነበር። የሚገርመው ቅድስት የጽዋ ዳቦ ይዛልን መጥታ እኔ ስላልነበርኩ ነገ ጥዋት ስጡት ብላ ዳቦ በአደራ የሰጠችህ ንጹህ እህቴ ነበረች። መልካምነቷ ነው እንግዲህ አለሁበት ድረስ ፈልጋ መጥታ እንድትጠይቀኝ ያስገደዳት። ቅድስት ብላቴ ዘምቶ የነበረው የዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ባች ስትሆን ማህበረ ቅዱሳንን ከመሰረቱ ቀደምት አባላት አንዷናት። ቅድስት መጥታ ከጠየቀችን በሁዋላ ከቤተክርስቲያን በፍጹም መራቅ እንደማልችል ለራሴ ቃል ገባሁ።

ለገሰና ጌቱ ከእኔ በፊት ሁለት አመታት በበሌ ከተማ ውስጥ በመምህርነት አገልግለዋል። ከተመረቁበት የመ/ርነት ሙያ ባሻገር ሁለቱም ባለችው ጸጋ ቤተክርስቲያንን ያገለግላሉ። ለቤተክርስቲያና ያላቸው ቀናኢነት ሰው መውደዳቸው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንድቀርባቸው አድርጎኛል። የተከራየነው አንድ ግቢ ሲሆን ሁለቱ በአንድ ቤት ይኖራሉ። ከተወሰኑ ወራቶች ቅርርባችን በጣም ስለተጠናከረ ለመኝታ ወደ የቤታችንን እንሄዳለን እንጂ በገባንበት ቤት በልተን እዚያው እንቆያለን። ቤተክርስቲያን ያለው ሰ/ትቤትም ሆነ መደበኛው የእሁድና ሰርክ አገልግሎት ሁሉ ሃላፊነቱ በእነርሱ ላይ ስለነበር እኔም ሳላስበው ሙሉ በሙሉ ገባሁበት። አጋጣሚ ሆኖ መንገድ ስራው ኣመጣቸው በርካታ ወንድሞችና እህቶችም ስለነበሩ፤ ቤታችን ሰው አይጠፋበትም። ብዙ ነገሮች የሚከናወኑት በጋራ ነው። ይህ መሆኑን ኑሮን ከማቅለል ባለፈ የቤተክርስቲያን አገልግሎትም ላይ ትልቅ መልካም ጎን እንዲኖረው አድርጎልን ነበር። ግቢ ጉባኤ ጀምሬውን የነበረውን የመዝሙር አገልግሎት በሰ/ት/ቤትም ማስቀጠል ጀመርኩ። ለገሰና ጌቱ በስብከትም በዝማሬም አገልግሎት የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ። ለገሰ ቅዳሜና እሁድ በአብዛኛው ገጠር ወዳሉ ቤተክርስቲያናት ይሄዳል፤ በአስተርጓሚ ይሰብካል። እግዚአብሔር ከሰጠው የማስተማር ጸጋ ባለፈ ትላልቅ አይኖችን ሲያጉረጠርጥ፤ በርካታ ሰዎች ስለሚፈሩት የተጣሉ ካሉ እና እርሱ ካለ ያስታርቃል። እርሱ ፊት ሳቅ ጨዋታ የለም፤ ሁሉም ነገር ኮስተር ያለ ነው። ይህ ኩስትራናው እኔና ጌቱ ዘንድ ግን ቦታ የለውም፤ እኛም ኮስታራ ስለመሆኑን አናውቅም እርሱም ልኮሳተር ቢል እንደማይሆን ስለሚያውቀው፤አይኮሳተርም፡ ነገር ግን አንዳንዴ ኮስትራናው ለእኔ ይከብዳል። አንድ ቀን ስጋ አምቦ ውሃ መጠጣት ፈለገን፤ መሸት ሲል ወደ ሆቴል አመራን። ከተማዋ መብራት ስለሌላት አንድ ሆቴል ላይ የማሾ መብራት አለ። መብራቱ ዋናው ቤት ሲሆን ከፊትና ከሁዋላ ከዋናው ቤት ውጭ ያሉት ውጭ መስተናገጃ ከፍሎች ግን ወጋገን እንጂ ብርሃኑ ስለማይደርስባቸው በደንብ አይታይም፤ በለገሰ ሃሳብ አፍላቂነት በጓሮ በኩል ባለው መቀመጫ ተቀመጥን። ቁጭ እንዳልን ጌቱ አይ ይህ ቦታ አይሆንም ውስጥ እንግባ አለ፤ ለገሰ አይሆንም እዚያ ብዙ ሰው ቢራ ይጠጣል፤ እዚህ ነው መሆን ያለብን አለ፤ በሁለቱ መካከል በነበረው ረጂም ሰአት ክርክር ሊታዘዝ የመጣው ልጅ ሁለት ሶስት ጊዜ ተመላለሰ፤ በዕለቱ በክርክሩን የሚሸነፍ ስለጠፋ፡ አምቦ ውሃውን ሳንጠጣ ወደ ቤት ተመለስን። ስንመለስ ሁለቱም ለየብቻቸው ስለሆነ እኔ ከማን ጋር እንደምሆን ግራ ገባኝ፤ ጭንቀቴን የተረዳው ለገሰ እየሳቀ አብራችሁ ሁኑ እለ በምልክት ወደ ጉቱ እንድሆን ያሳየኛል። ጥዋት ስንገናኝ ሁሉም ነገር ተረስቶ እየተሳሳቅን ነበር ወደ ስራ አብረን የሄድነው። 

 

No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...