Tuesday, May 26, 2026

 

                                         በሌ ክፍል-2

                                         

ወደፊት አራት አመታትን ከትሜ የምኖርባት በሌ ከተማ አንድ ቀን ብቻ አድሬ ተመልሼ ወደ ወላጆቼ ቤት አቀናሁ። በመጀመሪያው ቀን ውሎዬ፤ወረዳው ት/ቤቶች /ቤት የነበረኝን ጉዳይ አጠናቅቄ ትንሽ የመረጋጋት ስሜት ሲሰማኝ ከፍተኛ ረሃብ ለቀቀብኝ። ትዝ ሲለኝ ቁርስም ምሳም አልበላሁም።  ጾም ከተባለ እንደዚህ ነው አልኩና ብቸኛ በሆነው በከተማይቱ ዋና መንገድ ምግብ ቤት ፍለጋ  ወደላይ ሳቀና ከተማዋ እምብርት በሚባለው ቦታ/ዳወን ታወን/ እዚህ ቤት ለምለም እንጀራ አለ፤ የሚል ባማረ እጅ ጹሑፍ በፓርከር በተጻፈ፤ነገርግን ሳድስና ሳልስ ተቀላቅለው የተሰቀሉበትን የምግብ ቤት ማስታወቂያ አይቼ የራበው ሆዴን ላስታግሰው ወደ ቤቱ አመራሁ። ቤቱ ጽድት ያለ ጠረጼዛዎቹ ባማሩ በእጅ በተሰሩ የ ስራዎች የተሸፈነ ለመንፈስ ቀለል የሚል ቤት ነው። አጠገቡ ያለው ትልቅ ሀገር በቀል ዛፍ ቤቱ በመንገድ ዳር ሆኖም ቀዝቀዝ ያለ አየር እንዲኖረው በማድረግ ለእንግዶች ተዝናኖትን መፍጠር ችሏል ቤቱን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ካማተርኩ በሁዋላ አይኔን፤ወደ ውስጥ ስወረውር ውስጠኛው ክፍል አልፎ ወደ ዋናው ክፍል የሚደርስ የሰዎች ድምጽና ጀርባቸው የሚታይ የሁለት ሰዎችን አካል ማየት ቻልኩኝ። ጀርባቸውን ከሰጡኝ መካከል አንዱዋ ዞር ስትል ጅዋ የመጫወቻ ካርታ የያዝች እንስት መሆኑንዋን አረጋገጥኩኝ። ብዙም ሳትቆይ የመጫወቻ ካርታዎቹ ጅዋ እንደያዘች ምንልታዘዝ እያለች ያለውን፤ የምግብ ዝርዝር ስታስመርጠኝ፤ ካርታ በያዘችው ጣቶችዋ መካከል እከክ/ጭርት/የፈጠራቸው ቁስሎች ስመለከት ትግስት አጥቶ ነበረው ርሃቤ ጥሎኝ ጠፋ። በዝርዝር ከጠራቻቸው ምግቦች ውጭ ሌላ ምግብ ጠይቄ በብልሃት አለመብላትን ውጀው ወጣሁ። ከዚ በሁዋላ፤ ድካሜንና ረሃቤን በውስጤ ሸሽጌ ቤቱ እንዳድር ወደፈቀደልኝ አቶ ዶሎ ዳና ቤት ቀናሁ።

በወቅቱ የአቶ ዶሎ ባለቤት / ዘውዲቱ ቶንጃ ወልዳ አራስ ስትሆን በዚያን ቀን ከገጠር  ዘመዶችዋ ሊጠይቋት ይመጡ ስለነበር በርካታ ሰው በዋናው ቤት የሁዋለኛው በር በኩል ይገባሉ። ሁሉም ግን ወደ ሳሎን ሳይሆን ወደ አራስዋ ክፍል ነው የሚገቡት። እኔ ሳሎን ተቀምጨ፤ ማንም ከውጭ ሲገባ አያየኝም ረጂም ሰአት ቁጭ ብያለሁ። በመካከል አንድ ህጻን ወደሳሎን ገባና የሚፈልገውን ዕቃ መፈለግ ጀመረ። በእ ቤት ማንም የለም፤እኔ ስለመኖሬ ምንም አይነት መረጃ የለውም። ብቻውን ያንጎራጉራል፤ የሚፈልገውን አግኝቶ ይሁን አጥቶ ቀና ሲል ሰው መኖሩን አየና "ጦሶ" ብሎ በድንጋጤ ሳሎ በሩጫ ለቆ ወጣ። ጦሶ የምትለውን ቃል በያዝኩት መጽሐፍ በመጨረሻው ውስጠኛ ገጽ በኩል ጻፍኩዋት። መስከረም ተመልሼ ስራ ስጀምር ጦሶ ማለት የወላይትኛ ቃል ሲሆን አቻ የአማር ትርጉሙም እግዚአብሔር ማለት እንደሆነ ለማወቅ ቻልኩኝ።

ያንን ምሸት እራቴን አቶ ዶሎ ቤት ከበላሁ በሁዋላ አዲስ እያሰራ ባለው ሰርቢስ ክፍል ውስጥ በጊዜ እንዳርፍ ተፈቅዶልኝ፤ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ ወሰደኝ። መጥፎው ነገር ከሌሊቱ ስምንት ሰአት መንቃቴና በቅርበት፤ የምሰማው የእንቁራሪቶችና የሌሎች በርካታ ፍጡራን ድምጽ በድጋሚ እንቅልፍ በአይኔ እንዳይዞር አለመቻሉ ነበር። በዚህም የተነሳ ጠዋት ስነሳ አንገቴ ራሴን መሸከም ካለመቻሉም ባሻገር የሆነ ግዑዝ አካል አንገቴ፤ ላይ የተጫነብኝ አስመስሎኝ ነበር ይሁን እንጂ ይህ ስሜት አቶ ዶሎን በጠዋት ተሰናብቼ መኪና ከመጠበቅ ሊያስቆመኝ ስላልቻለ በአንዲት ፒክ አፕ መኪና ከላይ ተጭኜ በሌን ተሰናበትኳት።ከላይ በመሆኔ አይንን የሚያጠፋ ነፋስ እየገረፈኝ ስለነበር የማላውቀው አካል ጭንቅላቴ ላይ ጭኖት የነበረውን ሸክም አሽቀንጥሮ ስለጣለልኝ፤ ልቤ ወደ ቤተሰቦቼ፤ እየሄድኩ መሆኔን አስታውሶኝ የደስታ ስሜት በውስጤ ዘራብኝ። 

 ከወላጆቼ ጋር ራሴን ከመቻሌ በፊት የመጨረሻውን አዲስ አመት በልዩ ስሜት አክብሬ አዲሰ አመት በገባ በ 8ኛው ቀን 1988 ዓም ወደ ስራ፤ ቦታዬ ለስራ ዝግጁ መሆኔን አሳወቅሁ። አሁን በሌ ስገባ አልጋ ማግኘት እንደማይቻል ስላወቅሁ፤ልክ ሆቴል እንደያዘ ሰው ቀጥብዬ የሄድኩት ወደ አቶ ዱሎ ዳና ቤት ነበር በወቅቱ ስራ ስላልተጀመረ፤ ት/ቤት ደርሶ መመለስ እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የማሳልፈው ከተማዋን በማየትና ከሰዎች ጋር በመጫወት ነበር። እስከመስከረም 11 ቀን ቆይታ ማንም ሰው በስሜ ጠርቶ ሰላም ያለኝ አልነበረም። የሚያገኘኝ ሁሉ እጅግ በደመቀ ፈገግታ እቅፍ አድርጎ ሰላም ይለኛል፤ለመድክ ብሎም ጫውተኛል አንድም ሰው ግን በስሜን አይጠራኝም። ለተወሰኑ ሰአታት ያክል ግራ ቢገባኝም ስሜ ትንሽ ከበድ ስለሚል እንጅ ህብረተሰቡ ስሜን ስለተጠየፈው ወይንም ስም አለመጥራት ባህሉ እንዳልሆነ መገንዘብ ቻልኩ

መስከረም 11 /1988 ወደ አመሻሹ ላይ በከተማዋ ብቸኛ መንገድ ዳር ከጽ/ቤት ሰዎች ጋር ቆሜ ወጪ ወራጁና እያየሁ ከርቀት አንድ ጸጉሮቹ ያለ እድሜው ገባገባ ያለ ከወጣትነት ብዙም ያልዘለለ፡ ግለሰብ፤ ሰዎችን ለየት ባለ ፈገግታ፤ፍቅርና ሞቅ ባለ ሰላምታ እየሰጠ ወደ እኛ ሲመጣ፡ ልቤን በተወሰነ መልኩ ሰርቆት ከርቀት ጀምሬ እያየሁት አጠገባችን ደረሰና ሁሉንም በፍጹም ትህትና ስማቸውን እየጠራ፤ሰዎቹም ስሙን እየጠሩ ረጂም ሰላምታ ከተለዋወጡ በሁዋላ እኔንም ፤ የሞቀ ሰላምታ አቀረበልኝም። የትም ቦታ አይቸው እንደማላውቅ እርግጠኛ ነኝ። ነገር ግን ሳየው ደሰ የሚል ስሜት ተስምቶኛል። አንድ ላይ አብረውን ቆመው ከነበሩት ሰዎች መካከል ደምሴ የሚባለው፡ የጽ/ቤት ሰራተኛ "ለገሰ ተዋወቀው አዲስ ተመድቦ የመጣው መምህር ነው" አለና እኔን ሲያስተዋውቀን እንደገና በሞቀ ፈገግታ ሰላም ብሎኝ አጠገቤ ቆመ። ስለቆይታው ትንሽ ካወራቸው በሁዋላ ሁሉም በቆመበት የጎንሽ ወሬ ሲጀምር ለመጀመሪያ ጊዜ በበሌ ምድር "እሺ፡ እንዴት ነህ" ብሎ በፍጹም ወንድምነት ጀርባዬን ያዝ አድርጎ በስሜ ሲጠራኝ የተሰማኝ ስሜት በፍጹም በቃላት የሚገለጽ አልነበረም፥ አንዳንድ ጊዜ ወደ ሁዋላ ያንን ጊዜ፤ሳስበው እስከአሁን ሳንለያይ አብረን ለመቆየታችኝን ዋነኛው ምክንያት በዚያን ዕለት በመካከላችን በተለይም በእኔ ውስጥ የተፈጠረው ልዩ ስሜት ነበር። ከጥቂት ደቂቃዎች አብሮ ቆይታ በሁዋላ፤ ቀኑ እየመሸ ስለነበር ሁላችንንም ወደ የባዕታችን ስንገባ የአቶ ዱሎ ባለቤት ወ/ሮ ዘውዲቱ "አይታ ቱኬ" የሚባለውን ቡና አስፈልታ፤የበቆሎ እሸት ጠብሳ ነበር የጠበቀችን። የዚያን ዕለት ምሸት፡ ብዙ ስንጫወት አመሸንና በመካከል ስለተዋወቅሁት ለገሰ ስለሚባል ወጣት መሳይ ሽማግሌ ስጠይቃቸው "የኬሚስትሪ መ/ርና ጥሩ ሰው እንደሆነ አቶ ዱሎም ወ/ሮ ዘውዲቱም ነገሩኝ።  አቶ ዶሎና ወ/ሮ ዘውዲቱ ምንያክል የሚዋደዱ ባልና ሚስት እንደነበሩ፤ በሌም ለቅቄ እስከወጣሁ ድረስ ይገርመኝ ነበር። ሁለቱም በደርግ ሰአት የኢሰፓ አባል የነበሩና ራሽያ ድረስ እንደሄዱ በግርግዳዎቻቸው የለሰጠፉዋቸው ባለቀለም ፎቶ ግራፎቻቸው ምስክሮች ናቸው። አቶ ዱሎ ተጫዋች፤ሰው ወዳድ፤ደግ ሲሆን ወ/ሮ ዘውዲቱም ቢሆን እንደዚያው ናት። በየአመቱ በወላይታ በድምቀት የሚከበረውን የመስቀል በአል በርካታ ላጤ መ/ራን ከእርሱ ቤት ነበር የምናሳልፈው። ሁለቱም ልጆች ወልደው ለወግ ለማዕረግ ያደረሱ ሲሆን አቶ ዶሎ ከተወሰኑ አመታት በፊት ወደ አምላኩ መራቱን ሰምቻለሁ። በዚህ መልኩ የተዋወቅሁት፤ ለገሰ ፤የስራ ባልደረባዬ እንደሚሆን ሳስብም ልዩ የደስታ ስሜት ተሰማኝ። ወ/ሮ ዘውዲቱ ቀስ እያለች ጨዋታዋን ቀጥላ "ለገስ ሃይስኩል ብቻ ሳይሆን፤ ቤተክርስቲያንም እንደሚያስተምር ስትነግረኝ፡" እውስጤ ሲመላለስ የነበረ አንድ ጭንቅ አስታወሰችኝ። አስከአሁን ቤተክርስቲያን መኖር ስለአለመኖሩ ማንንም መጠየቅ አለመድፈሬን። በመጀመሪያው ቀን የሰማሁት የቤተክርስቲያን ስም ግራ ስላጋባኝ፤ ይህ የሆነው። አሁን ግን ደፈር አልኩና "የት ቤተክርስቲያን" ብዬ ጠየቅሁ። "እዚህ እኮ ከተማው ጠባብ ነው አንድ ቤተክርስቲያን ነው ያለው መድሀኔአለም" ስትለኝ፡ ውስጤ ታምቆ የነበረው ፍርሃት በአንዴ ጠፍልኝ። ወ/ሮ ዘውዲቱ እያዩ የጠቀሰልኝ ቤተክርስቲያኖች ሁሉ ሳይሆን የጠራችልኝ እኔ የምፈልገውን ነው። እኔ እንደምፈልገው ምናልባት አንገቴ ላይ ያለውን መስቀል አይታ አለበለዚያም እርሱዋ ኦርቶዶክስ፤እምነት ተከታይ ስለሆነች ይሆናል።  ወ/ሮ ዘውዲቱን ነገ ጠዋት ቤተክርስቲያኑን የሚያሳየኝይኖራል ስላት፤ "እንዴ ነገማ ሚካኤል ነው ከልጆች ጋር ትሄዳለህ" አለች። በነጋታው መስከረም 12 በጠዋት ተነስቼ ነጠላዬን መስቀልያ ለብሼ ሄድኩ፤ አንድ ጥግ ውዳሴ ማርያሜን አድርሼ ኪዳኑ አልቆ መስቀል ለመሳለም ወደ ቤተክርስቲያኑ ስጠጋ ለገሰን አየሁት። ምናልባት ካላጋነንኩ ክርስቶስ ራሱን ያየሁ ያክል ነበር ደስታዬ፤ ከዚያማ ከለገሰ ጋር ስለግቢ ጉባዔ፤ ስለባህርዳር፤ ብዙ አወራን። አጋጣሚ ሆኖ ሁለታችንም ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተማርነው ባህርዳር ስለሆነ፡ በጋራ ልናወራባቸው የምንችላቸው፤ በርካታ ጉዳዮች ስላሉ ብዙ አወራን። ለገሰን ከ አመታት በፊት ጥሎት ወደ መጣው ፔዳና ፖሊ ግቢ ጉባኤ በሃሳብ ወሰድኩት። በዕለቱ ወርሃዊ የዝክርና የመማማሪያ የሚካኤል ማህበር ስለነበረ ማምሻችንንም አብረን አመሸን። በዚያው ቀን የሰ/ትቤታችን ሊቀመንበር የነበረውን ወርቁን፤ ባልና ሚስቱ አቶ ታዬ ታቦርና ወ/ሮ ሚሊዮን ከበደን ከነልጆቻቸው፤አቶ ጫፎ ጨመረን፤ አቶ ፍቅሬን ከነባለቤቱ እና ሌሎችን፥ለመተዋወቅ በቃሁ። እናም መስከረም 12/1988 ዓም በሌ፤ ከስራ ባለፈ በእምነት የሚመስሉኝን በርካታ ሰዎች ያወቅሁበት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ህብረታቸውም የተቀላቀልከበት ዕለት ነበር። 

 


No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...