የወለጋ ምድር የንጹሃን ምድር እየጠጣ ለምለምነቱን ቀጥሏል፡፡
ምንጩ
በትክክል፡ ማን እንደሆነ ማወቅ ባልችልም፡ ሰሞኑን ከመንግስትና መንግስት አፍቃሪ ከሆኑ መገናኛ ብዙሃን፡ የህዳሴ ግድብ መገንባት
ከጀመረበት አመት አንስቶ በየዓመቱ በወርሃ ሰኔ በርካታ ወገኞች ከውጭ ተላላኪ አካላት ጋር በመሆን ኢትዮጲያ ላይ ጫናቸውን እያጠናከሩ
በርካታ ህዝባችንን ይገድላሉ፤ በሀገራችን ላይም የመከራ ዶፍ ያወርዱባታል፤ ይሁን እንጅ እኛ ብልጽግናችንን ከማረጋገጥ ወደ ሁዋላ
ሊመልሰን የሚችል አንዳችም ምድራዊ ሃይል አይኖርም የሚል፤ዜና በመስራት፡፡
የውጭ
ሃይሎች የኢትዮጲያ ቋሚ ጠላቶች እንደሆኑና ሁሌም ባገኙት አጋጣሚ በጦርነት፤በዲፕሎማሲ እና በመሳሰሉት ሁሉ፡ እንደሚያጠቁን ማንም
ያውቃል፡፡ አሁን የመጣው አዲስ ነገር በሰኔ ይጠነክራል መባሉ ነው፡፡ ግን አንድ ጥያቄ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡ ጥቃቱ ሰኔ ላይ እንደሚበረታ
ጥናት ወይንም መላምት ካረጋገጠ፡ ለምን ሰኔ ላይ ስስ የሆኑ ቦታዎች ላይ ጥበቃ ማድረግ አልተቻለም? ጥቃቱን የሚፈጽመው አካል ደግሞ
በምን ስሌት ነው ብሔርን መርጦ የሚያጠቃው? በቅርቡ ጥቃት የተፈጸመባቸው ቦታዎች በቁጥጥር ስር ናቸው ሲባል ከርሞ አደጋ አድራሹ
አካል በየትኛው መንገድና ሰዓት ገብቶ አደጋ አደረሰ?
ምናልባት ከቀደሙት ወራትና ቀናት ለየት የሚለው፡ ሃዘናቸውን ለመግልጽ፡ የሀገሪቱ የጦር መሪ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት፡ ከግንባር ቀደምቶቹ ተርታዎች መሆናቸው ነው፡፡ ስህተቶች ይሰራሉ፡ ግን በወቅቱ ይታረማሉ፡፡ ሀገርን ከጠላት የሚጠብቅ፤ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ የአየርና እግረኛ ጦር ገንብተናል እየተባለ በሚወራበት ሰኣት፡ የሀገር ዋልታና ማገር የሆነው ሚስኪኑ ዜጋን ከሞት መታደግ ካልቻለ፡ ዘመናዊ ጦር መታጠቁስ ምን ይረባል? በርግጥ በሀገሬ የጦር ጀግንነት ጥርጥር የለኝም፡ ግን ጦሩን የሚመሩት አካላት ለጦሩ ስኬትና ውድቀት የራሳቸው አሰተዋጽኦ አለው፡፡ አድዋን፤ካራማራን፤ባድመን፤ ሌሎች በርካታ የጦር ሜዳዎችን በድል የተወጣነው፡ በቆራጡ ወታደራችን ወኔ ቢሆንም መሪዎቹ ሚና ግን ወሳኝ ነበር፡፡ ተመሳሳይ፡ስህተት፤በተመሳሳይ ቦታና በተቀራራቢ ጊዜ ሲደጋገም A mistake repeated more than once is a decision.(Paulo Coelho) የሚለውን አባባል እውነተኛነት ያጎላዋል፡፡
ተጠያቂነት ከሌለ የዜጎች ሞት አሁንም ይቀጥላል፡፡ ታዬ ደንደአ!!
ጥፋቱ የማነዉ? ጠያቂና ተጠያቂ ሊኖር ግድ ይላል! ተጠያቂነት ባለመኖሩ አንድ ችግር መቶ ጊዜ ራሱን ይደጋግማል! "
(ታዬ ደንደአ)
ንፁኃን ዜጎች በግፍ ሲገደሉ የሁሉም ጤነኛ ሰዉ ልብ ያዝናል:: ያዘነ ሀዘኑን መግለፁም አግባብ ይሆናል:: እኛ ደግሞ እንደመንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስከበር ትንሹ ኃላፊነታችን ይመስለኛል:: ሰላምና ፀጥታ ከሰፈነ ሌላዉን ህዝቡ ራሱ ይሰረዋል:: ነገር ግን የዜጎች ሞት በየቀኑ ይሰማል::
ግምቢ ላይ የተፈፀመዉን አስነዋሪ ጭፍጨፋ ሳንረሳ ሌላ ጭፍጨፋ በቄለም ዛሬ ተደግሟል:: በነገራችን ላይ ጥፋቱ የማነዉ? ጠያቂና ተጠያቂ ሊኖር ግድ ይላል! ተጠያቂነት ባለመኖሩ አንድ ችግር መቶ ጊዜ ራሱን ይደጋግማል!
በርግጥ ላለፉት ሦስት ዓመታት ኦሮሚያ ላይ የፀጥታ ችግር ገንግኗል:: ከመቼዉም ጊዜ በላይ ህዝባችን እጅግ የከፋ መከራ አይቷል:: እዉነታዉን መናገር " ስልጣን ፈላጊ" ያስብላል:: እዉነትን ለመደፍጠጥ የስልጣን ልበወለድ ተፅፎ ወደ ላይ ይተረካል::
ለመሆኑ ህዝብ በሌለበት ምድር ስልጣን ለምን ይጠቅማል? አሁን ተጠያቂነትን በማስፈን እንቆቅልሹን መፍታት የህልውና ጉዳይ ሆኗል! ከዚህ ካለፈ አደጋዉ ከቁጥጥር ይወጣል!
እንግዲህ፡ ህሊና ያለው ባለስልጣን
ካለ፤ ህዝብ መርጦኝ ለህዝብ ቆሜያለሁ ካለ ከላይ ባለስልጣኑ ያስቀመጡት መልዕክት፡ የሚያስተምረው ይመስለኛል፡፡