Thursday, April 30, 2026

የሰፈራችን ትልቁ ሰው


የሰፈራችን ትልቁ ሰው የአባባ ጋሼ

ተወልጄ ባደኩባት የገጠር መንደር ውስጥ ሰፈራችን በርካታ ሰዎች በአስተዳደጋችን ውስጥ ብዙ አስተዋጽኦ አላቸው። ልጅነታችን የጋራ ነው። በወላጆቻችን ስም እንጠራለን፤ወላጆቻችን ቤት እናድራለን እንጂ፤ ምግባችን፤አገልግሎታችን፤ስናጠፋ የሚገርፉን፤ጥሩ ስንሰራም የሚያመሰግኑን፤ ለወደፊት ማንነታችን ትልቅ አስተዋጾኦ ያላቸው በርካታ ሰዎች አሉ።ከእነዚያ ዘመን ካፈራቸው ሰዎች መካከል አባባ ጋሼ አንዱ ነበሩ። አባባ ጋሼን ወላጆቻችንን፤ ታላላቆቻችንን ሁሉም አባባ ጋሼ ነው የሚላቸው። ሙሉ ስማቸው ጋሸ ታፈሰ ይባላሉ። አባባ ጋሼ በስማቸው የውሃ ምንጭ አላቸው፤ሱልላ ወይንም አባባ ጋሼ ምንጭ ሄዳችሁ ውሃ ቅዱ ይባላል። ምንጩ ጥልቅ ሲሆን፡ በበጋ እንኳን የማይቀርቅ በክረምት ጎርፍ ገብቶበት የማይደፈርስ ነው። ምንጩ መቼና በማንም እንደተቆፈረ ጥርት ያለ መረጃ ባይኖረኝም፤እርሳቸው ስለቆፈሩት ይመስለኛል፤ በስማቸው የሚጠራው። በበጋ ወራት፡ በተለይም የእህል ውቃ በሚከናወንበት ወቅት፡የውሃ ወረፋ ካለ ከእርሳቸው ቤት የሚመጣ ልጅ ወረፋ አይጠብቅም፡ ቅድሚያ ይሰጠዋል።ባለቤታቸው ወ/ሮ ዘነበወርቅ ከመጡ ደግሞ እዚያ ያለ ሰው ቀድቶ እቤታቸው ያደርሳል። እማማ ዘነበወርቅ፤ ህጻን እንኳን ቢሆን ዝም ብለው አያልፍም፡ የማይሆን ቦታ ከሆነ የተገኘው፤ ተቆጥተው፤ ቤት ድረስ ሄደው እንዴት በዚህ ሰአት እዚህ ቦታ ትለቁታላችሁ፡ ብለው የተሰብን ሁሉ፤ የሚቆጡ ደርባባ እናት ነበሩ። ለእማማ፤ ዘነበወርቅ ምንጭ ሲመጡ ይህ የሚደረግላቸው፤ እርሳቸው ፈልገውት ሳይሆን ፍቅራቸውና እናትነታቸው፤ስለሚያስገድድ ነው። አንዳንድ ጊዜ እርሳቸው እዚያ፤ካገኙት ሰው ጋር ሲጫወቱ ልጆችን ሲመክሩ ውሃ ተቀድቶ ቤታቸው መድረሱን እንኳ ላያውቁ ይችላሉ። ቤታቸው ድግስ አይጠፋም፤በቅርበት ልጅ ካዩ ቤት ገብተው ያላቸውን አውጥተው የሚሰጡ ደገኛ የዚያ ዘመን እናት ነበሩ። አይ ሞት ግን ስንቱን ደግ ሰው ወስዶ ደሃ አደረገን።አባቴ የአባባ ጋሸንና የወ/ሮ ዘነበወርቅን ሴት ልጅ፡ለማግባት አጭቶ፤ ነገር ግን ጋብቻው አልተፈጸመም። ምክንያቱን እኔ አላውቅም። ይሁን እንጂ አባቴን ልክ እንደልጃቸው፤እርሱም እንደወላጆቹ ነው የሚተያዩት፡ በሚገርም ሁኔታ አባቴ ሊያገባት የነበረችው ልጃቸው የጓደኛዬና አብሮ አደግ ወንድሜ አደፍርስ ከፈለው  እናት ናት። ባትወልደኝም እናቴ ናት። አባባ ጋሼ ያላቸው ቅርበት በተወሰኑ ጉዳዮች ከወላጅ አባቴ  ጋር ላቅ ይላል እንጂ ለአባቴ ወንድሞችና ለሌላው ሰው ሁሉ ያላቸው ቅርበት አንድ ነው። አባባ ጋሼ ብልህ፤ ወጌሻና ብዙ ጥበብ አላቸው። ለበርካታ ሰው መፍትሔ የሚሰጡ፤የተጣላን የሚያስታርቁ ነበሩ። ልጅ ሳለሁ እግሬን አልቤን ማጭድ ቆርጦኝ ሽባ ይሆናል መራመድ አይችልም ሲባል፤ ጨው በብረት ምጣድ እያቀለጡ፤ በየሶስት ቀን እያጠቡና በንጹህ ጨርቅ እየሸፈኑ፤ በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ ጤነኛ ያረጉኝ ትልቅ አባት ናቸው። ዛሬ ጫማዩን ባሰርኩና በፈታሁ ቁጥር ጎንበስ ስል፤ ያኔ በጨው ሲያጥቡኝ ፤ሳለቅስ፤አይዞህ እያሉ ያባብሉኝ የነበረው አንደበታቸውና አባታዊ የፊታቸው ጭንቀት ድቅን ይልብኛል። አባባ ጋሼ ከከተማ ስንመጣ፤ ስለኑሮው ስለከተማ ደህንነት ይጠይቁኛል።

አባባን ከውስጤ እንዳልረሳቸው የሚያደርገኝ ግን አንድ ነገር ነው። ማትሪክ አልፌ፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመማር በዘመኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር በነበረው ባህርዳር መምህራን ኮሌጂ ደርሶኝ የመጀመሪያ አመት ትምህርቴን ጨርሼ፡ ስመለስ፤ በተደጋጋሚ ይጠይቁኝ የነበረው ስለሀገሩ ርቀት ለምን ባህርዳር እንደተባለ ነበር። ትልቅ ባህር አለ፤ እያልኩ የጣናን ግዘፈት ያክል ሳይሆን እርሳቸው በሚገባቸው ልክ ነገርኳቸው፡ በጣም ተገረሙ። በውይይታችን መጨረሻ፡ አደራ ወደዚያ ባህር አጠገብ እንዳትሄድ እያሉ ሲያስጠንቅቁኝ፤ በጣና ሃይቅ ላይ በጀልባ እንደሄድኩ፡ አባይን በእግሬ ለመሻገር ሙከራ እንዳደረግሁ ብነግራቸው እንዳይደነግጡ በማሰብ ተውኩት። ከዚያ በሁዋላ ላገኙት ሰው ሁሉ የሚያወሩት የእኔ ትምህርት በጣም ለየት ያለ ባህር አለበት ሀገር እንደምማር ነው። እኛም ቤት መጥተው የሚያወሩት ይህንኑ ነው። በአባባ አረዳድ የትምህርት ክብደትና ቅለት የሚለካው ከአካባቢ ርቆ በማማር ስለሆነ። ተመርቄ ለስራ ደቡብ ክልል ደረሰኝ፤ ያኔ የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሀዋሳ ናት። ሀዋሳ ደርሼ እጣ አውጥቼ  ወደ ቤት ሄድኩኝ፤ ስራ የት ደረሰህ ሲሉኝ ለገጠር ሰው ደቡብ ክልል ማለት ቶሎ ላይገባቸው ይችላል ብዬ በማሰብ ሀዋሳ ነበር የምለው። ብዙ ሰው የሀገሩን ርቀት፤እንጀራ አለ፤ሰላም ነው፤ እንደው የምታውቀው ሰው ይኖራል ብለው ነው የሚጠይቀኝ። አባባ ግን ስለአየሩ፤ስለሚመረተው ምርት፤ሰው ስለሚናገረው ቋንቋ፤ ነው። ያኔም በጣም አስፍቼ የነገርኩዋቸው ስለ ሀዋሳ ሀይቅ ነው። በጣም የሚገርመው፤ ድጋሚ ለዞን እጣ ሳወጣ የደረሰኝ፤የቀድሞው፡ ሰሜን ኦሞ ዞን ሲሆን ዋና ከተማው አርባምንጭ ነው። ለአባባ ስለአርባምንጭ ስለሁለቱ የጫሞና አባያ ሃይቆች አንስቼ ስለነገርኳቸው፡ውስጣቸው የደረሰበት ድምዳሜ እኔ የተማርኩት ትምህርት ከሁሉም የላቀ እኔ ከሁሉም በጣም ጎበዝ የሆንኩ፤ ወደፊትም በቃ ስራዬ ሁሉ ውጭ እንደሆነ  ነበር። ከዚያ በሁዋላ ለእረፍት ስሄድ በጣም እንደትልቅ ሰው አውርተውኝ፤ሸኝተውኝ፤መክረውኝ ፤ እቤት ሄጄ ጋብዘውኝ ነበር የምንለያየው። አባባ ሰፈራችን ሰው ሲሞት አስከሬን አጥበው፤የሚገንዙ ሰው አጥብቆ ሲያዝን የሚቆጡ፡ነበሩ። አባቴም ከልቡ ነበር የሚወዳቸው፤አማካሪያቸው፤ የሚላክላቸው፡ ነበር። የሚገርመው የአባባ ሁሉም ልጆቻቸው፡ በሚባል ደረጃ ቁምነገረኛ፤ ሰው የሚወዱ፤ ለሰው ፈጥነው የሚደርሱ ናቸው። እትዬ እትሜ፤እትዬ ትርንፍስ በብዙዎቻችን የማይረሱ የአባባ ፍሬዎች ናቸው። አሁን ቤታቸውን ይዞ ያለው ልጃቸው በእርሳቸው ቦታ የተተካና ለሰፈሩ ሰው ሁሉ ፈጥኖ ደራሽ ነው። ከእርሳቸው አንጻር ልጅ አልኩት እንጂ ጋሽ ንጉሴ( ብዙ ሰው አንች ነው የሚለው) ወልዶ የዳረ ትልቅ ሰው ነው።

አባባ ጋሼ ነብስዎት በቅዱሳን እቅፍ ያኑረልኝ።

የአባባ ጋሼና  ያደኩባት መንደሬ የወላጆቼ መንደር


Wednesday, April 22, 2026

ባህርዳር

 

                          


እስከአሁን ካየሁዋቸው ቦታዎች ሁሉ በልቤ የተለየ ቦታና ፍቅር ያላት ባህርዳር ናት:: ባህርዳር ለሁሉ ነገር የመጀመሪያ ናት:: ያለቤተሰብ ተከታይነት ለብቻዬ አንድ ቀን ተኩል የተጓዝኩባት፤ መኪና ካስተዋወቅን በፍጹም ከዚ ቀን በፊት ከማላውቀው ከአሰላ ከመጣ ልጅ ጋር አብረን በአንድ አልጋ ላይ ያደርኩባት፤ብር በባንክ ተልኮልኝ የተቀበልኩባት፤ በርታ የወደፊት ማንነቴን የሚቀይሩ ውሳኔዎችን በራሴ ወሰንኩባት ቦታ ስለሆነች ባሀርዳር ለእኔ ልዩ ናት:: ጋዜጠኛ ሄኖክ ጎንደር ሴት ብትሆን ደጋግሜ የማገባት እኔነኝ እንዳለው፤ እኔም ባህርዳርንበሴት ጾታ ከመጠራት አልፋ ሴት ብትሆንና ድጋሚ ማግባት ቢፈቀድ የማገባት ይመስለኛል:: ምስጋና ለአይነስውሩ የአማርኛ አስተማሪያችን ጋሽ ክንፈ ይሁንና ፍቅር እስከመቃብር መጽሐፍን 11ኛ ክፍል እያለን አስነብበውን ስለነበር፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስገባ ወደ ባህርዳር ለመሄድ በጣም ጓጉቼ ነበር፡ በመጽሐፍ የተገለጡት ቦታዎችን ለማየት፡ ዲማ ጊዮርጊስን፤የአባይ በረሃን፤ የእናቴ ሞክሼ የሆኑትን ወ/ሮ ውድነሸ በጣሙን፤ፊታውራሪ መሸሻን፡ በዛህንና በልጅነቴ ያየሁዋቸው የነበሩትን የቆሎ ተማሪ መኖሪያ ዳስ(ጎጆ) ቤቶችንና የተማሪዎችን አኮፈዳ

የተማሪ ወዳጅ ይቅር ምናባቱ

ዱላ ሲያነሱበት ይላል ባዛኝቱ::

 እየተባላ የተገጠመላቸውን የቆሎ ተማሪዎች ለማየት:: ተማሪ ሲባል የአስኮላውን ሳይሆን ቆሎ ተማሪን እንደሆነ ይታወቅልኝ::

የባህርዳር ግን የመጀመሪያ ጉዞዬ፤ በጣም አስፈሪ ነበር::የሰላሌ ሜዳዎችን ጨርሰን ድንገት ሳላስበው መኪናችን አባይ በረሃ ውስጥ ጎዞውን ሲጀምር በሁሉም አቅጣጫ አድማስ እንጂ መሬት ማየት ስላልቻልኩ፤ ያ በፊት ሲያወራ ሲያውካካ የነበረ ሁሉ ሰው ፀጥ ሲል ልቤ በፍርሃት ርዶ፤እንባዬ መውረድ ጀመረ:: አብዛኛው አውቶቡስ የሞላው ተማሪ ስለሆነና ሁሉም በሚባል ደረጃ ለቦታው አዲስ በመሆኑ ማንም ማንን አያይም፡ሁሌም በራሱ ስሜት የተያዘ ይመስላል፨ በአባይ በረሃ በየመንገዱ ላይ አደገኛ ናዳ ስላለ ተጠንቀቁ የሚል ጹሑፍ አለ:: ከተወሰኑ አመታት በሁዋላ ያንን ጹሑፍ ሳስታውሰው፤ እንዴው ናዳ ከላይ ቢመጣ ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ሊገባኝ አልቻለም፨ የኢትዮጲያ መድህን ድርጅት የለጠፈው አርማ ግን ተስፋ ሰጭ ይመስለኝ ነበር:: ለፍተው ላፈሩት ንብረትዎ ለማትተካ ህይወት መድህን ይሁን አለኝታዎ የሚል ታፔላ::እኔ መድህን ምንእንደሆን በደንብ ባይገባኝም ደስ የሚል ስሜት ፈጥሮልኝ ነበር:: ሞጣ ያደረው አውቶቡሳችን በቀጣይ፤ ቀን ጥዋት ወደ 3 አካባቢ አዴት ከተማ ደርሶ፤ ለትንሽ ደቂቃ ሲያቆም የተጠበሰ በቆሎ ገዛሁ፡ በቆሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀመስኩ:: የሚያሳዝነው ዕለቱ ረቡዕ ስለነበር ከሁዋላችን የነበሩ አንድ በእድሜ ዘለግ ያሉ አባት አይ የሸዋ ሰው ጾም የለም እንዴ፤ በጠዋት ምግብ ብለው የምንበላውን ሲያበሻቅጡን አንድ ጊዜ ብቻ አፌ ውስጥ ያለውን ውጬ ሌላውን መብላት አቆምኩ:: ከላይ ያለውን አምላኬን ሳልፈራ አጠገቤ ያሉትን ትልቅ አባት ፈርቼ::

አይደርስ የለ ባርዳር በሁለተኛው ቀን ወደ አምስት ሰአት አካባቢ ደረሰን፡ ሁላችንም በአንድነት ወደ ፔዳ ግቢ ገባን:: እንደደረስን የመጀመሪያ ምዝገባ ስለነበር ለመመዝገብ ፎቶ ከፒ ስለሚያስፈልግ ብዙዎቻችን ፎቶ ኮፒ ስላልነበረን ሲኒየር ተማሪዎች ካፌ ፎቶ ኮፒ እንዳለ፤ሲነግሩን ግር ብለን ሄድን፤እዚያ እንደደረስን የሻይቡና ማሽን የሚያሞቅ ልጅ አይተን ፎቶ ኮፒ ፈልገን ነው ስንለው ቁጭ በሉ ማሹን እያሞቀሁ ነው ብለን ቁጭ አልን፨ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በሁዋላ ሌሎች ሲኒየሮች መሸወዳችን ገብቷቸው፤ይህ የሻይ ማሽን እንጂ የፎቶ ኮፒ ማሽን አይደለም ብለው ፡ ነገሩን:: ሽወዳ ቁጥር አንድ፨

ምዝገባው በዚሁ መልኩ አለቀና ሚሊካርድ ባይኖረንም ካ ገብተን ምሳ በላ:: ምሳ ለመብላትም ሰልፍ መኖሩን አወቅን::ከምሳ ሁሉም ተማሪ ፎቶ ኮፒ አለ ወደተባል ነው ቤት ያመራል፡ወደ ሻይ ቤት ማለት ነው፨ ስንደርስ የተወሰኑ ተማሪዎች ሰልፍ የመሰለ ነገር ሰርተው ግርግዳውን ይዘው ያወራሉ፤ ሲኒየሮች ናቸው፤ ተሰለፉ አሉን፤ ተሰለፍን፤ የተወሰነ ፍሬሽ እየመጣ እኛን ተከትሎ ይሰለፋል:: ሌሎች ግን ዝም ብለው ይገባሉ፤ አሁን እኛ ፍሬሽ ስለሆንን አውቀው ነው ሰልፍ ሳይጠብቁ የሚገቡት እያልን ውስጣችን ሲያማቸው፡ ከፊታችን ተሰልፈው የነበሩት ልጆች እየሳቁ ትተውን ሄዱ:: ሽወዳ ቁጥር 2:: ከዚያ ገባን ስንገባ በግራ በኩል ትንሽ ክፍል ውስጥ አለ፨ ቲኬት ከዚያ ይገዛና ሻይ ራስህ ሄደህን ነው የምትወስደው:: እኛ ገብተን ቁጭ አልን፡ የሚያመጡልን መስለን፡ ቁጭ እንዳልን አንዱ መጣና ፍላጎታችንን ጠየቀን ተናገር፡ የታዘዘን ልጅ ወዴት እንደሄደ አላወቅንም:: የሻይ ቤቱ ሰራተኛ ብርጭቆ ሲሰበስብ፡ እኛ እኮ አዘናል ፤አልደረሰንም ሲለን ቁጭ በሉ ይመጣላችሁዋል ብሎን ቁጭ አልን::ከተወሰኑ ደቂቃዎች በሁዋላ እንደተሸወድን ገባንና ተነስተን ወጣን::

በዚህ በዚህ መልኩ እየተሸወድን ከተወሰኑ ቀናት በሁዋላ፤ዲፖርትመንት መረጥን ኦረንቴሽን ሳይሰጠን ቤተመጻህፍት ቤት መግባትም ጀመርን:: አንድ እኔ የማውቀው ትንሽ ግንዛቤ ያለው የሚመስል ጓደኛችን እንግባ ብሎኝ ገባን:: የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት የቤመጻህፍት ክበብ አባል ሆኜ ተማሪ አስተናግድ፤የምፈልገውን መጽሐፍ ቀድሜ አውጥቼ ተማሪ ወስዶታል እያልኩ አነብ ስለነበር ትንሽ ግንዛቤው ቢኖረኝም ይህ፤ጓደኛዬ ግን  ትንሽ ደፋር ፈጣን ነገር ስለሆነ ካታሎግ ሲያገላብጥ አንድ የመጽሐፍ ርዕስ አገኘና ፤ገንጥሎ ሰርኩሌሽን ዴስክ ሄዶ ስጡኝ ሲላቸው፤ የቤተመጻህፍቱ ሰራተኞች ተጠራሩና አጭር ስብሰባ አድርገው መታወቂ አም አሉት አዲስ ነኝ የለኝም አላቸው፡ ወዲያውኑ፤ አንድ ሰራተኛ አጭበጨበና ፍሬሽ ተማሪዎች ውጭ ስለምትፈለጉ ውጡ ሲን ገብተን የነበርነው ሁሉ ወጣን፡ ወዲያውኑ ፍሬሽ ተማሪዎች ኦረንቴሽን ሳይሰጥ ወደ ቤተመጻህፍት ቤት ዝር እንዳትሉ የሚል ማስታወቂያ ተለጠፍ:: ከተቀመጡት ምክንያቶችየመጀመሪያው ካቶግ መቅደድ የሚል ጓደኛዬ ገበና ነው::

 

Saturday, April 18, 2026

አህያ መግፊያ

 




ፎቶው አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የተማርኩበት ቅጥር ግቢ ሆኖ፤ ተጉለትና ጭንብሩ ተብሎ የሚጠራው ቦታ ነው፨

1974 ዓበቅርባችን ባለ ቦታ ሰፊ ተብሎ በሚጠራና በድንጋይ በተሸፈነ ሜዳ ከአድማስ በምስራቅ በኩል በግርማ የሚታየውን የኮምቦልቻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን፤ በሰሜን የተጉለትና አጎራባች ቦታዎችን፤ በደቡብ ቀርሳ፤ኩሳዬን አጉልቶ በሚያሳይ ቦታ ላይ አዲስ ት/ቤት የዳዎ ኢየሱስ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ተገንብቶ ስራ ጀመረ፨ ት/ቤቱ ፤ሁለት ህንጻዎች ኖረውት፤እያንዳንዱ ህንጻ ሁለት የመማሪያ ክፍልና አንዳንድ ቢሮዎች አሉት፨ ግድግዳው በእንጨት ተሰርቶ በጭቃ የተለሰነ ቢሆንም ወለሉ ምንም ማስተካከያ ሳይደረግበት ተማሪ ወንበር ከቤቱ እያመጣ ነበር የሚቀመጥበት፨ እየቆየ ሲሄድ ጭቃው ምርግ እየተሰነጠቀና እየወደቀ ንፋስ እየገባ እንቸገር እንደነበር፤ አመታት እየጨመሩ ሲሄዱም ከሁላ በኩል በደንብ አድርጎ ስለፈረሰ እጅግ በማስገባት ከውስጥ እቃ ማንሳት እንደሚቻል፤ በሮቹም እየወላለቁ፤ አለቆች ማታ ዘግተው ለመሄድ በጠም ችግር ይገጥማቸው እንደነበር አይረሳምኝም፨ መቼም ለቀበሌያችንና ለአጎራባች ቦታዎች የመጀመሪያ ት/ቤት ስለሆነ ልጆችም ወደ ት/ቤት መላክ ግዴታ ጭምር ስለነበር ለተለያዩ አቅጣጫ ወደ ት/ቤት የሚገርፈው ተማሪ አጅግ በርካታ ነበር፨ የመጀመሪየዓ ት/ቤት ስለነበር ከህጻን እስከ አስራዎቹ ድረስ የሚደርስ ወጣት ሁሉ ወደ ት/ቤት ከመሄዱ የተነሳ፤ በእድሜ የምናንስ ህጻናት ከፍተኛ፤እንግልት፤ይደርሰብን ነበር፨የተቀመጥንባቸውን ቦታዎች ለእነርሱ እንድንለቅ፤ እነርሱ ያሉትን እንድንሰራ ግዴታ ሲሆን እንቢ ካልን ኩርኩም አይቀርም፨ በጣም ደጉ ነገር ከበርካታ ቦታዎች ተማሪዎች ስለሚመጡ በርካታ ዘመዶችን ማግኘት ይቻላል፨ እኔ ከማልረሳው፤ ከአህያ መግፊያ፤ከአልባሳ፤ ከቁጢሱ፤ከቀርሳ፤ ከመስቀል የሚመጡ በርካታ ዘመዶቼን ማግኘት መቻሌ አንዱ ትልቅ ደስ የሚያሰኝ ጉዳይ ነበር፨ ወሩን በትክክል ባላስታውሰው በዚያው አመት፤ ምናልባትም፤ የግብርና ስራ ሲገባደድ፤ ወደ ህዳርና ታህሳስ አካባቢ ሊሆን ይችላል፡ትምህርት ጀምሬያለሁ፨ ት/ቤቱ እንደተጀመረ እጅግ በርካታ ተማሪ ወደ ት/ቤት ይሄድ ስለነበር፤ መንገድ ዳር የባቄላና የአተር እሸት ያላቸው ሰዎች ጠዋትና ማታ ተማሪ ጥበቃ ጊዜያቸውን ያባክኑ ተማሪም በሩቅ ሲያያቸው ደንግጦ ይበረግግ ነበር፨ አንዳንድ ጊዜም ገበሬዎች ት/ቤት እየመጡ በዚህ መንገድ የሚሄዱ ተማሪዎች ሰብላችንን አበላሸዑት ብለው ስሞታ ሊያቀርቡ፤ ይህንን ተክትሎም ት/ቤቱ በሰልፍ ላይ ጥብቅ መልዕክት በተደጋጋሚ ሲነገር አስታውሳለሁ፨ት/ቤቱ ወንበር አልነበረውም ሁሉም ተማሪ አንድ ክፍል ይገባል ፊደል ይማራል፨ ከተወሰኑ ወራት በሁዋላ ቀድመው የተመዘገቡ 2ኛ ከፍል ሲገቡ ዘግይተው የተመዘገቡ 1ኛ ከፍል ቀሩ፨ ለማለፍ ቀድሞ መምጣት እንጂ ችሎታ ቦታ አልነበረውም ብለን ስናወራ ነበር፨ ግን መ/ሩ በራሱ መገምገሚያ የተሻሉትን አሳልፎ እንጂ መቼም ይህንን ያደርጋል ብዬ አላስብም፨ ለማንኛው ታላቅ እህታችን 2ኛ ክፍል ስትገባ  ታላቅ ወንድሜና እኔ 1ኛ ክፍል ቀረን፨ በአመቱ አሁንም ክፍል መቀዳደማችን እንዳለ ሆኖ ታላቅ እህታችን በእንግልጣር አፍ አላስቆም አላስቀምጥ አለችን፨ ዶግ፤ካው፤ካት የመሳሰሉት የእንሰሳ ስምብቻ ሳይሆኑ የእኛ መሰደቢያ ሆኑ፨ በ 1ኛ ወሰነ ትምህርት ደብል አልፌ የታላቄን ታላቅ ደረስኩባት ግን የ1 ሰሚስተር ልዩነት በእንግሊዘኛው መመጣጠን አልቻልንም፨ ከተወሰኑ ወራቶች በሁዋላ እንደምንም ብዬ ደረስኩባት፨ ወንድ መሆኔና ስራ አለመስራቴ በስራ የምትደክመውን እህቴን መብለጥ ጀመርኩ፨ ሴት ልጅ ለአቅመ ሄዋን ከደረሰች ማማሩ ሌላ ችግር ያመጣል በሚለው አመለካካት እህቴ፡ ትምህርቷን አቋርጣ ባል አግብታ ዛሬ የአራት ልጆች እናት ሆናለች፨ መሰረተ ትምህርትን ያመጣው ደርግም ከወንዴዎች ጋር ( ደርግ እንደሚለው) ጦርነት ላይ ስለነበር፤ ወጣቶችን በውድም በግድም እያለ ያዘምት ስለነበር ቤተሰብ ወደ ጦርነቱ እንዳይሄድ በመፍራት ትምህርቱን አቋርጦ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ እንዲኖር በማድረጋቸው፤ወንድሜም ከ6ኛ ክፍል በላይ ሳይቀጥል፤ቀርቶ እርሱም አግብቶ ዛሬ የአራት ልጆች አባት ሆኗል፨

የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት ቆይታ በጣም ደስ የሚል፤ ቀስ በቀስ ከበርካታ ነገሮች ጋር የመላመድ፤ አካባቢን የማወቅ፤እድሎችን ፈጥሮልኛል፨ በዚህ በ1ኘኛ ደረጃ ት/ቤት ቆይታዬ፤ ለፋሲካ ማንም ሳይፈቅድ፤ አንድ ሳምንት፤ ት/ቤት ዝግ ነው፡ ማንም ተማሪ ብቅ አይልም፡ ምናልባት መ/ራኑም የሚመጡ አይመስለኝም፤ ለጥር ኢየሱስና ጥር ስላሴ፤ በምንም ቀን ይዋሉ፤ ማስፈቀድ የለም ዝም ብሎ መቅረትና ቤተክርስቲያን መሄድ ማንም ሊገረስሰው የማይችል ያልተጻፈ ህግ ነው፨ የተማሪ መጽሀፍ፤ ምናልባት አንድ ለአራት ወይንም ለአምስት ስለሚሰጠን ብዙዎቻችን የመጽሐፍን መልክ የምናውቀው አይመስለኝም፨ እንደ ጽዋ ጠጪ መጽሐፍቶቹ ባወጣነው ህግ መሰረት ከአንዳችን ወዳንችን ይተላለፋሉ፨ በልጅነት እድሜ የ1ኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ይገርሙኝ ከነበሩት አንዱ ሬዲዮ ሲያስተምር መስማት ነበር፨ ት/ቤታችን ካለው ሬዲዮ ቀደም ብዬ አውቃለሁ፤ ትልቁ አጎታችን ቤት አለ፤ እርሱ ያኔ ለእኛ የማይገባን ወሬ፤ አንዳንዴ ደግሞ ደስ የሚል ዘፈን የሚየዓስደምጥ እንጂ እንደት/ቤቱ የትምህርት አይነት፤የክፍል ስም እየጠራ የሚያስተምር ነበር፨ 2ኛ ክፍል እያለ በወርሃ መስከረም ወይ ጥቅምት ላይ ይመስለኛል፡ መ/ሩ ነገ ትምህርት በሬዲዮ ስለሚጀምር በጥዋት እንድትመጡ ተብሎ ተነግሮናል፨ ወንድምና እህቴ ገና ትምህርት አልገቡም፤ጉልበታቸው ለስራ ስለሚፈለግ፨ እና የዚያን ዕለት በሬዲዮ ትምህርት ተማርን፤ ምሳ ሰአት ይህንን ትልቅ ዜና ለወንድሜ ለመንገር ወደ ምሳ መሄድ ሳያስፈልገኝ እርሱ ወደላበት ስራ ሄድኩኝ፨ በቃ ሬዲዮ የክፍል ስም የትምህርት አይነት እየጠራ፤ ለእኘዓ ሁሉ ሰላምታ እየሰጠ ያስተምራል ብዬ እርሱንም ስራ አስፈታሁት፨ ስለሬዲዮው ይጠይቀኛል፤ እመልሳለሁ፨ ወደ መጨረሻ ላይ ግን ሬዲዮ ሁለተኛ ከፍል ብሎ 1ኛ ከፍል ቢወስዱት በምንያውቃል ሲለኝ፡ ያውቃል አይሰራም እሺሺሺ ይላል አልኩት፡ እንግዴህ ይህ ፈጠራ ነው፡ ከወንድሜ የተሻልኩ መሆኔን ማስመስከሪያ፨ ይህንን ጉዴን ያወቁት ግን አንድ ቀን ነው፨ መ/ሩ ሬዲዮው ካስተማረ በሁዋላ ያልገባችሁ ጥያቄ ካለ ጠይቁ እያሉን፤ ያልተዘጋው ሬዲዮ እሺሺሺ ማለቱን ትቶ የ5ኛ ክፍል ህብረተሰብ ሳይንስ ማስተማር ጀመረ፤ እኔና ወንድሜ አይን ለአይን ተጋጨን፡ ነቅቻለሁ አይነት ነው የእርሱ አስተያየት እኔ ደግሞ ውሸቴ ተጋለጠ ነው፨ የሚገርመው በዚህ ጉዳይ እሳቅን ያወራነው በጣም ትልቅ ከሆንን በሁዋላ ነው፨

በ1ኛ ደረጃ ተማሪነት ወቅቴ ከማልረሳው ትልቁ ጉዳይ የእጅ ስራ የሚባለው ክፍለ ጊዜ ሲሆን፤ ሁላችንም በርካታ የእጅግ ስራዎችን እንሰራለን፨ ሹራብ፤ከአክርማ፤ቆብ፤ከእንጨት የግብርና መገልገየዓ ቁሳቁሶችን እንሰራ ነበር፨ እነዚህ የሚሰሩ የእጅ ስራዎች በተለይም በሴቶች የሚሰሩ የስፌት ዕቃዎች፤ ዳንቴሎች፤ የሚለበሱ ሹራቦች፤ ማርክ ከማግኘት ባሻገር ዋጋ ተተምኖላቸው፤ ለወላጅ ይሸጣሉ፨ ብዙ ጊዜ ሹራቦቹ የሚሰራውን ልጅ ታሳቢ ተደርገው ስለሚሰሩ የሚገዛቸው የዚያው ተማሪ ወላጂ ነበር፨ ይህ በመሆኑ ለበርካቶቻችን የማናወቅውን ክህሎት ለማዳበር እድል ከፍቶልናል፨ ተግባር ተኮር ትምህርት ማለት ይህ ይመስለኛል፨ የእርሻ ትምህርት ቢኖርም፤ ብዙ በተግባር የተደገፈ አልነበረም፨ የማስታውሰው፤ ባቄላ ተክለን ስር አወጣጡን፤ ጸሐይ ብርሃን ሲያጣ ጸሐይ ለመፈለግ ወደ አንድ አቅጣጫ ማዘንበሉን በተግባር አይተናል፨ ነገር ግን መስኩን ላቦራቶሪ አድርጎ ብዙ ተግባር ተኮር ትምህርት መስጠት ይቻል ነበር፨ በርግጥ መ/ራኖቻችን ጋርም የእውቀት ብሎም የክህሎት ችግር ሊኖር ይችል ይሆናል፡ ከዚያም በላይ እኛም ለእርሻ ትምህርት ያለን አመለካከት ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል፨

4ኛ ክፍል ሳለሁ አባቴ ወደ ወረዳ ዋና ከተማ  ደነባ ይዞኝ ሄደ፨ ደነባ ያኔ በጣም ድምቅ ያለች ደስ ደስ ያላት ከተማ ነች፨ ለጂም አመታት ከተማ ሲባል ውስጤ የምትመጣው ደነባ ነበረች፨ መኪናዎች አልፎ አልፎም ቢሆን ይንቀሳቀሳሉ፨ በርካታ ቤቶች ላይ ስም ተፅፎ ምን አይነት አገልግሎት እንደሚሰጡ ከበራቸው ላይ ተለጥፏል፨ ለምሳሌ ነገሰ ሸንቁጥ ሱቅ፤ ሲሳይ ብሩ ጠጅ ቤት፤ በቀለች ገብሩ ቡና ቤት፤ ገመቹ ዲነግዴ ሱቅ፤ሽብሩ ዘገየ ሻይ ቤት፤ ተዋበች ከልሌ ቡና ቤት፨ አባቴ እንደደረሰን የሚያውቀው ቡና ቤት ስለነበር እዚያ ሄድን፤ ምግብ ገዛልኝ፤ ነጭ እንጀራ እጅግ ነጭ በሆነ የንኬል ትሪ ቀረበልኝ፡ ለስላሳም ቀርቦልኛል፨ የእንጀራውን ንጣት ሳደንቅ ለመቁረስ በጣም ዘግይቼ ነበር፨ አባቴ ከሌሎች ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር እያወራ ስለ ጉብዝናዬ ይተርክላቸዋል፡ እርሱ አይበላም፨ ምግብ መጨረስ ነውር ስለሆነ ያንን የሚጣፍጥ የነጭ ጤፍ እንጀራ እያማረኝ ተውኩት፨ ለስላሳው ግን፤ የጠርሙሱን አፍ አፌ ውስጥ አስገብቼ አልወጣ ብሎኝ ስታገል፤ በግድ አወጣሁት፤ ለስላሳው ገንፍሎ ልብሴን አጠበው፨ አባቴ አይዞህ፤ይደፋ ብሎ አፅናናኝ፨ 

በአንደኛ ደረጃ ሳለሁ የስዕል ክፍለ ጊዘ ነበር፡ ስዕሉም ሳሉ እየተባልን እንፈተን ነበር፨ ያው አብዛኞቻችን በሬ፤ ጎጆ ቤት፤ እንስራ የመሳሰሉትን እንስል ነበር፨ የያኔ የክፍላችን አንድ ወጣት አሁን ካህን የሆኑ ወታደር ስዕል ሳሉና እጁን ሲስሉ ስዕሉ እየተበላሽ ሲያስቸግራቸው፡ እጅ የሌለው ሰው ሳሉና ከስዕሉ በታች ጀግናው የኢትዮጲያ ጦር የሶማሌን ወታደር እጁን ቆርጦ እንደጣለው የሚል መግለጫ ጨመሩበት፨ ይህ ሀሳብ ሊመጣ የቻለው አባታቸው በጡረታ የተገለሉ ሻምበል ስለሆኑ ምናልባትም፤ በሶማሌ ጦርነት ጊዜ ተሳትፈው ልጆቸው ይህንን መሰል ታሪኮች ከእርሳቸው ሰምቶ ሊሆን ይችላል፨ የዚያ ዘመኑ ተማሪ አከበር፤ሸዋሰማ ግን በጣም ቀልደኛና ተጨዋች ብቻ ሳይሆን ጎበዝ ተብሎ ከሚጠሩር ተርታ ነበር፨ እንዲህ እንዲህ እያለ 6ኛ ከፍል ደረስኩና ለሚኒስትሪ ፎቶ ለመነሳት የተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ደብረብርሃን ከአባቴ ጋር ሄድኩኝ፨ ይህ ጉዞ ኮለምበስ አሜሪካን ለማግኘት ካደረገው ጉዞ አይተናነስም፨ ለመጀመሪያ ጊዜ በሎንችና ሁለት ሰአት መንገድ፤ መሄድ፤ ቀንና ሌሊት መብራት ካለበት ከተማ መሰንበት፤ መኪናም እንደሬዲዮና ቴፕ ዘፈን ሲዘፍን መስማት፤ መስኪድ፤ማየትና አዛን ሲባል መስማት፤ በፈረስ ጋሪ መሄድ'አስፋልት ማየት፤ ብር እየተቆጠረ ከሚሰጥበት ባንክ ቤት መግባት፡ ኧረ ስንቱ ይነገራል፨ አባቴ ለሌላም ስራ ስለመጣን 3 ቀን አደርን፨ ደብረብርሃንን በደንብ አየሁዋት፡ ፎቶ ሲራክ የመጀመሪያውን ጉርድ ፎቶ ግራፍ ተነሳሁ፤ ለማስረጃ የመጀመሪያው ጉርድ ፎቶ ግራፌ ከነካርዱ ተለጥፏል፨ የት/ቤታቸን የመጀመሪያ ዙር የ6ኛ ክፍልሚኒስትሪ ፈተና ተፈታኞች ቁጥራችን 21 ሲሆን ትልቁን ውጤት ያመጣው፤ከፈለኝ ሀብቴ የሚባለው ጓደኛችን ሲሆን 100 ፐርሰንት ነበር ያመጣው፤ አፈሩን ይቅለላትና ተናኘ ሃ/ጊርጎስ እና ፀጋው መኮንን 98 ፐርሰንት ሲያመጡ፤ ከታች ካርዳቸውን ያያዙት የዚያ ዘመን ጨቅላ ደግሞ ከታች ያለውን ውጤት አምጥተዋል፨ የዚያ ዘመን የክፍላችን ዝቅተኛ ውጤት የይብራለም ሞገድ ሲሆን ያመጣችው 65 ፐርሰንት ነበር፨ ይብራለም በአሁኑ ሰአት የት እንዳላች አላውቅም፨ ይብራለም፡ስልጡን የምትባል፤ ከብዙዎቻችን ቀድማ ከተማን የቀመሰች ልጅ ነበረች፨ በሸዋ ክፍለሀገርም በሩጫ ታዋቂ የነበረችውና እስከ ጀርመን ድረስ ሄዳ ሜዳሊያ ታሽነፍ የነበረችው ግርድሽ ንጉሴም የክፍላችን ተማሪ ነበረች፨ ግርድሽ ከብዙዎችን ቀድማ ሰአት ያሰረች፡ ተማሪ ነበረች፤ ሩጫ በሰጣት ትሩፋት፨ ሰአትን በተመለከተ ግርድሽና አደፍርስ ከፈለው የተለየ ገጠመኝ አላቸው፨ አደፍረስ ብዙ ጊዜ ሰአት ሲጠይቃት ሩብ ጉዳይ 20 ጉዳይ ምናምን በሚባልበት ሰአት ስለሆነ፤ በጭንቅላቱ የሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ኖሮ አንድ ጊዜ ግርድሽ ስንት ሰአት ነው፤ መቼም የአንች ሰአት ያለ ጉዳይ አያውቅ ያላት ብዙዎቻችን እስከዛሬ ድረስ ስንገናኝ የምናነሳው ትውስታቸን ነው፨                                          



Wednesday, April 15, 2026

አንጭቆረር


ወላጆቼ ሰፈር ሆኖ ከርቀት አንጭቆረርን የሚያሳይ ፎቶ
-------------
የትምህርትአጀማመር---------

የመጀመሪያው ዙር የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ በኢትዮጵያ በ1971 ዓ.ም የተካሄደ፣ መሃይምነትን ለማጥፋት እና ማንበብና መጻፍን ለማስፋፋት የተደረገ ታሪካዊ ዘመቻ ነው። ይህ ዘመቻ አዋቂዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ፣ በማንበብና በመጻፍ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ ያስቻለ ሰፊ እንቅስቃሴ ነበር። ይህ የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ፣ በወቅቱ በነበረው የእድገት በህብረት ዘመቻ ማዕቀፍ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበረው ይህንን እድል በለጋ እድሜያቸው ካገኙ የዚያ ዘመን ህፃናት አንዱ እኔ ነበርኩ፨ ትምህርቱ በቀን በሁለት ዙር ጠዋት ከ 12-2 ሰአት ለአዋቂ ወንዶችና ፈቃደኛ ለሆኑ ሴቶች፤ ማታ ከሆነ ሰአት ገበሬ በሬውን ፈትቶ ወደ ቤት እስከሚመለስበት ሰአት ለእናቶች ይሰጥ ነበር፨ ትምህርቱ ደግሞ ለሁለት ወራት ክረምት ነው የሚሰጠው፤ መቅረት፤ ብዙ ያስቀጣል፨ የትምህርት ፈረቃው ስራን ማዕከል ያደረገ ነበር ወንዶቹ ወደ እርሻ ስለሚሄዱ ጠዋት ይማራሉ፤ እነርሱ እዚያ ሲማሩ ስራ መፍታት የለም በሬዎቻቸው ቁርሳቸውን እየበሉ ለስራ ይዘጋጃሉ፨ እናቶች ደግሞ በማታው ክፍለ ጊዜ ይማራሉ፨ እኔና እኔን መሰል ኩታሮች፤ ከሆዳችን ውጭ ምንም እሴት የማንጨምር (ልጅ በመውለዳቸው ቤተሰብ ደስተኛ መሆናችንን፤ሳይጨምር) በሁለቱም ክፍለ ጊዜ እንድንማር እድል ክፍት ስለነበርን፤እሳት ነበርን

          ተማርልኝ ብዬ ዋሽራ ሰድጄ

          ቀለም ገባው አሉ እሳት ሆነ ለጄ፨ 

ተብሎ እንደተዘፈነላቸው፨

 መሰረተ ትምህርት መማር ለበርካታ ሰዎች እስከዚህ ዘመን፤ ድረስ ስማቸውን  በጣት ሳይሆን፤በእስኪርብቶ እንዲፈርሙ ከማድረግ ባሻገር፤ እኔን መሰሎችን ደግሞ ትምህርት እንጀራችን እንዲሆን አድርጎታል፨ እኔ በሁለቱም ፈረቃ መማሬ ጎበዝ እንድሆን ከማድረጉ ባሻገር በእናቶችና በአባቶች መካከል ያለውን የስራ ክፍፍልና ልፋት እንድገነዘበው ረድቶኛል፨ ነፍሳቸውን በቀኝ ያቁመውና የእኔ ወላጆች ግን እድሜ ለወላጆቻቸው የተማሩ ስለነበሩ፡( ኮሌጅ ግን አልበጠሱም) የዚህ መርሃ ግብር ታዳሚ አልነበሩም፨ ኣባቴ እንዴው በቀጣይ ዙሮች በቀበሌው ያሉትን እንዲያስተምር ተደርጎ እንደነበር አስታውሳለሁ፨ እናቴም ዳዊት መድገም የጀመረች ስለነበር ለመማር አትሄድም፨ በአጭሩ በዚያ ዘመን መረዳቴ የእኛ ቤት የሊቅ ቤት ነበር፨ እናቶች ከሰአት ስለሚማሩ ቶሎ ወደ ቤት ተመልሰው በስራ ሲደክም ለዋለው የትዳር አጋራቸው፤ ለእግሩ ውሃ ለአፉ ጥሬ አዘጋጅተው መጠበቅ፤ ከተቻለም እስከመንገድ ሄድ ብሎ የግብርና ዕቃውን መቀበል ስለሚጠበቅባቸው፡ ልባቸው እቤት እንጂ ትምህርቱ ላይ የለም፨ በዚያ ላይ ሁሉም እናቶች ሲገናኙ ለመጫወት መፈለግ እንጂ ትምህርት ለእነርሱ ትልቅ ዳገት ነበር፨ ምናልባት አንድ ሰአት ከተማሩ ቶሎ ወደቤት ለመሄድ ፤ በተለያዩ ዘዴዎች፤ ኧር ይብቃን ለነገ ያልቅብናልና ትልቅ ዝናብ መጥቷል፡ በተለይ በተጉለት በኩል ሰማዩ ጠቆር ካለ በቃ  አቤቱታ በየመካከሉ ይቀርባሉ፨ የሁሉም ልብ ቤታቸው ነው፤ የደከመ ባልን ከእርሻ፤ ከብት ሲጠብቅ የዋልን ልጅ ከዱር ከነከብቶቹ፤ ለመቀበልና ቀዝቀዝ ያለውን ቤት ሙቅ አድርጎ፤ ምሽቱን ደማቅ ለማድረግ፨  ሴት ነት እኮ ትልቅ ፀጋ ነው፨ ያለ ሴት ቤት በረት ነው የሚባለው በምክንያት ነው፨ በተለይ ደግሞ ሃይለኛ ባል ያላቸው እናቶች አለመረጋጋታቸው አሁንም ፊቴ አለ፨ ሲለቀቁ ሁሉም በሩጫ ነበር የሚሄዱት፨ ትምህርቱ እንዳለቀ ሁሌም ግራ እጅ ወደላይ እየተደረገ መፈክር ይባላል፨ በየቀኑ አንድ አንድ ሰው እንደመሪ ይመረጥና እርሱን ተከትሎ ሌላውም ይላል፨ በዚህ ረገድ እኔና ሌሎች፡ እናቶች፤ የኔን ፋንታ እርሱ ይበል እያሉ እድሉን ስለሚሰጡን፤ በርካታ እናቶችን ተክተን እንላለን፨ እኛ ምንቸገረን ስህተት ብርቃችን አይደል፤ በስህተታችን ሲሳቅ ደስ ብሎን እንስቃለን፨ በዚህ ረገድ ሁሌም የማልረሳው አንድ ታሪክ አለ፨

በአንደኛው ቀን መ/ሩ ሴቶች እናቶች መሪ ሆነው መፈክር ካልተፎከረ አትወጡም ብሎ ድርቅ አለ፨ ሁሉም እናቶች እንቢ አሉ፨ መ/ሩ በሩን ዘግቶ በመስኮት እያየ፤ አልከፍትም አለ፨ በዚህ ረገድ ብዙ መቆየቱ ቤት ውስጥ የሚያመው ጣጣ ያስፈራቸው እትዬ ግርድሽ     ( ነፍሳቸውን ይማር) በቃ እኔ እላላሁ ተከተሉኝ አሉና እጃቸውን አወጡ፨ የመጀመሪያው መፈክራቸው፤ ማይምነት ግቡን ይመታል ሲል ብዙዎችን ስንስቅ መ/ሩ ደንግጦ በሩን ከፍቶ ለቀቀን፨ ለካ እትዬ ግርድሽ ማለት የነበረባቸው ማሃይምነት ይወድማል ነበር፨ እሳቸው ኢሰፓኦ ይሳካል ወይ ግቡን ይመታል ማለት ነበረባቸው፨ መሰረተ ትምህርት በዚህ መልኩ ከፊደል አስተዋወቀንና በዚያ ዘመን ከምተኛበት አጎዛ  ስፋት የበለጠ የምስክር ወረቀት በመስጠት፡ የብርሃን ጎህን ቀደደልኝ፨

1972 ዓም ምናልባት ከብት ስጠብቅ ወይንም ሰፈር ሳውደለድል ከርሜ፤ በ1973 ዓም ላይ ከሰፈራችን የአንድ ሰአት ተኩል ርቀት ላይ እንጭቆረር ከተማ ውስጥ:  ዋዩ 1ኛ ደረጃ፤ ት/ቤት ውስጥ ቀደም ብለው ትምህርት የጀመሩ ፡የቀበሌያችን ልጆች ስለነበሩ፤ ከብዙ ጥያቄና ልፋት ወሩንና ቀኑን በማላውቀው ዕለት ት/ቤት ሄደኩኝ፨ ለምዝገባ ስሄድ መሰረተ ትምህርት ማጠናቀቄን የሚገልጥ ካርድ ይዣለሁ፨  ስለአንጭቆረር ሁሌም ግርም የሚለኘ ነገር አንጭቆረር ድረስ ተብሎ አንጭቆረር፡ የሀገር ቂጥ እንደሆነ ተደርጎ የሚወራው ነገር ነው፨ አንጭቆረር እጅግ በጣም ቢረዝም ከአዲስ አበባ ከ150- 200 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነበረች፨ አሁን ግን ከተማዋ  አድጋ ተመንድጋ ሳር ቤቶችዋ ሁሉ ወደ ቆርቆሮ ተቀይረው፤ የከተማ ሽታ የሚነፍስባት ከተማ ከሆነች ውላ አድራለች፨ በአንድ ወቅት አንጭቀረር የሚለው ስም ከየት እንደመጣ ስጠይቅ ያገኝሁት ምላሽ እንደሚየዓስረዳው፡ ቀደም ባለት ዘመናት ደገኛኛ ቆለኛው ገበያያ የሚገበያይበት ቦታ ላይ የጤፍ  ሰብል የሚዘራበት ቦታ ሲሆን ጤፍ ሲታጨድ፤ በዚያ ገበሬ መሬት ላይ ሰዎች ሲገበየዓዩ አይቶ  አንች ቆረኔ የገበያ ቦታ ትሆኝ ብሎ ንዴቱን በግርምት ሲገልጽ ( ቆረን ማለት ዋናው ሰብል ታጭድ መሬቱ ላይ የሚቀረው ተረፍ ምርት ማለት ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ እዚያው ስለሚበሰብስ ለመሬቱ ለምነት የራሱ ድርሻ አለው)  እንዴት ይገበያያሉ እያለ ሲቆጣ የዚያ መገበያያ ቦታ የጤፍ ቆረን የሚለው ቀስ በቀስ አንጭ ቆረር ተብሎ፡ የገበየዓ ቦታው ሶቀየር ስሙን ይዞ መጣ ይባላል፨                 

እንግዲህ ያንን የያዝኩትን ሰርትፍኬት የተመለከተ  አንድ መ/ር አይቶ ዜሮ ክፍል ግባ ተባልኩ፨ ት/ቤቱ በሲዳ ርዳታ የተሰራ ህንፃ ሲሆን እጅግ ያማረ ወንበር የነበረው ክፍል ገባሁ፨ ወንበሩ ደብተሮቻችን፤ የምሳ መያዣ ትንሹዋን አገልግላችንን፤ ከፈለግን እኛን ጭምር ከተት ማድረግ የሚችል የውስጥ ኪስ አለው፨ አንድ ወንበር ሶስት ተማሪ ያስቀምጣል፨ የሴቶች ቁጥር ጥቂት ሲሆን ከበሩ መግቢያ ባለው ረድፍ ተቀምጠዋል፨ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ የክፍሉ አለቃ የሆነችውና በሁዋላ እንዳወቅሁት የጥበቃው ልጅ የሆነችው፤ ምላሰ ረጂም እንስት፤ ከአንድ እህቷ ጋር ይቀመጣሉ፨ እኔ ት/ቤቱ በገባሁ በማግስቱ አንድ ተማሪ ገባ፡ ልጅ አዲስ በመሆኑ ወንበሩንም ስላላወቀው ሲገባ በሩ ስር ባለው በአለቃዋ እና በአህቷ ወንበር ተቀመጠ፨ በዚህ ጊዜ ክፍሉ በሳቅ ተቀወጠ፡ እንደፈለጋቸው እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው፤ አለቃዋና እህትዋ ከክፍሉ ወጭ ስለነበሩ ለምን ሳቃችሁ ብለው ሊቆጡን ሲገቡ ልጁ ወንበራቸው ላይ ተቀምጧል፨ ምድር ቁና ሆነች፨  አለቃዋ እና የጥበቃው ልጅ ወንበር ላይ ካለእርስዋ ፈቃድና እውቅና ሌላ ሰው ተቀመጠበት፨ ስሙ ተጠይቆ በረባሽነት ተፅፎ በደሉ ተዘርዝሮ ለጥበቃው፡ ለአለቃችን አባት ተሰጣቸው፨ የሚያውቁትን የምት አይነት ጎማ ጫማ በተጫማ እግራቸው፤ በእጃቸው፤ አልስታውስም እንጂ በጥርሳቸው ጭምር ተደበደበ፡ ያ ልጅ ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ የት/የቤቱን ደጃፍ አልረገጠም፨ ጥበቃው አቶ ተካ፤ ልጃቸው ደግሞ መርሻ ትባል ነበር፨ እኔ የገባሁ ቀን አንድ መ/ርም ሊያሰተምረን አልገባም ዘፈን ብቻ ሆኖ ዋለ፨ ይህው ድርጊት ለአንድ ሳምንት ሲቀጥል እንቢ ብዬ ቀረሁ፨ አንዲት ዘመዴ መ/ርት ስለነበረች ችግሩ ተነገራት፤በቃ ይምጣ እኔ አንደኛ ከፍል አስገባዋለሁ አለች፨  በዚህ ጥሪ መሰረት ወደ ት/ቤቱ አቅንቼ እኔ ሆዬ ማንንም ሳላማክር 1ኛ ክፍል ትማር ከነበረችው የአጎቴ ልጅ በለጡን ተከትዬ  1ኛ ክፍል ስገባ የመጀመሪያው መንፈቀ አመት ፈተና እየተሰጠ ነበር'፤ ፈተናውን ተፈተንኩ፨ መልሴ ለሁሉም አይነት ጥያቄዎች እውሸት የሚል ነበር፨ 8/100 አመጣሁ፨ ሲገባኝ የመጀመሪያዎቹ 10 ወይም 5 ጥያቄዎች እውነት ወይንም ውሸት በል የሚል ትዕዛዝ ስላላቸውን ነው መሰል፤ ከእውነት እ ን ከውሸት ደግሞ ሙሉቃሉን ወስጄ እውሸት ብዬ ለዳሽ ሙላውም፤ ለምርጫውም የመለስኩት፨ 

ይቀጥላል




                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...