Saturday, April 18, 2026

አህያ መግፊያ

 




ፎቶው አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የተማርኩበት ቅጥር ግቢ ሆኖ፤ ተጉለትና ጭንብሩ ተብሎ የሚጠራው ቦታ ነው፨

1974 ዓበቅርባችን ባለ ቦታ ሰፊ ተብሎ በሚጠራና በድንጋይ በተሸፈነ ሜዳ ከአድማስ በምስራቅ በኩል በግርማ የሚታየውን የኮምቦልቻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንን፤ በሰሜን የተጉለትና አጎራባች ቦታዎችን፤ በደቡብ ቀርሳ፤ኩሳዬን አጉልቶ በሚያሳይ ቦታ ላይ አዲስ ት/ቤት የዳዎ ኢየሱስ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ተገንብቶ ስራ ጀመረ፨ ት/ቤቱ ፤ሁለት ህንጻዎች ኖረውት፤እያንዳንዱ ህንጻ ሁለት የመማሪያ ክፍልና አንዳንድ ቢሮዎች አሉት፨ ግድግዳው በእንጨት ተሰርቶ በጭቃ የተለሰነ ቢሆንም ወለሉ ምንም ማስተካከያ ሳይደረግበት ተማሪ ወንበር ከቤቱ እያመጣ ነበር የሚቀመጥበት፨ እየቆየ ሲሄድ ጭቃው ምርግ እየተሰነጠቀና እየወደቀ ንፋስ እየገባ እንቸገር እንደነበር፤ አመታት እየጨመሩ ሲሄዱም ከሁላ በኩል በደንብ አድርጎ ስለፈረሰ እጅግ በማስገባት ከውስጥ እቃ ማንሳት እንደሚቻል፤ በሮቹም እየወላለቁ፤ አለቆች ማታ ዘግተው ለመሄድ በጠም ችግር ይገጥማቸው እንደነበር አይረሳምኝም፨ መቼም ለቀበሌያችንና ለአጎራባች ቦታዎች የመጀመሪያ ት/ቤት ስለሆነ ልጆችም ወደ ት/ቤት መላክ ግዴታ ጭምር ስለነበር ለተለያዩ አቅጣጫ ወደ ት/ቤት የሚገርፈው ተማሪ አጅግ በርካታ ነበር፨ የመጀመሪየዓ ት/ቤት ስለነበር ከህጻን እስከ አስራዎቹ ድረስ የሚደርስ ወጣት ሁሉ ወደ ት/ቤት ከመሄዱ የተነሳ፤ በእድሜ የምናንስ ህጻናት ከፍተኛ፤እንግልት፤ይደርሰብን ነበር፨የተቀመጥንባቸውን ቦታዎች ለእነርሱ እንድንለቅ፤ እነርሱ ያሉትን እንድንሰራ ግዴታ ሲሆን እንቢ ካልን ኩርኩም አይቀርም፨ በጣም ደጉ ነገር ከበርካታ ቦታዎች ተማሪዎች ስለሚመጡ በርካታ ዘመዶችን ማግኘት ይቻላል፨ እኔ ከማልረሳው፤ ከአህያ መግፊያ፤ከአልባሳ፤ ከቁጢሱ፤ከቀርሳ፤ ከመስቀል የሚመጡ በርካታ ዘመዶቼን ማግኘት መቻሌ አንዱ ትልቅ ደስ የሚያሰኝ ጉዳይ ነበር፨ ወሩን በትክክል ባላስታውሰው በዚያው አመት፤ ምናልባትም፤ የግብርና ስራ ሲገባደድ፤ ወደ ህዳርና ታህሳስ አካባቢ ሊሆን ይችላል፡ትምህርት ጀምሬያለሁ፨ ት/ቤቱ እንደተጀመረ እጅግ በርካታ ተማሪ ወደ ት/ቤት ይሄድ ስለነበር፤ መንገድ ዳር የባቄላና የአተር እሸት ያላቸው ሰዎች ጠዋትና ማታ ተማሪ ጥበቃ ጊዜያቸውን ያባክኑ ተማሪም በሩቅ ሲያያቸው ደንግጦ ይበረግግ ነበር፨ አንዳንድ ጊዜም ገበሬዎች ት/ቤት እየመጡ በዚህ መንገድ የሚሄዱ ተማሪዎች ሰብላችንን አበላሸዑት ብለው ስሞታ ሊያቀርቡ፤ ይህንን ተክትሎም ት/ቤቱ በሰልፍ ላይ ጥብቅ መልዕክት በተደጋጋሚ ሲነገር አስታውሳለሁ፨ት/ቤቱ ወንበር አልነበረውም ሁሉም ተማሪ አንድ ክፍል ይገባል ፊደል ይማራል፨ ከተወሰኑ ወራት በሁዋላ ቀድመው የተመዘገቡ 2ኛ ከፍል ሲገቡ ዘግይተው የተመዘገቡ 1ኛ ከፍል ቀሩ፨ ለማለፍ ቀድሞ መምጣት እንጂ ችሎታ ቦታ አልነበረውም ብለን ስናወራ ነበር፨ ግን መ/ሩ በራሱ መገምገሚያ የተሻሉትን አሳልፎ እንጂ መቼም ይህንን ያደርጋል ብዬ አላስብም፨ ለማንኛው ታላቅ እህታችን 2ኛ ክፍል ስትገባ  ታላቅ ወንድሜና እኔ 1ኛ ክፍል ቀረን፨ በአመቱ አሁንም ክፍል መቀዳደማችን እንዳለ ሆኖ ታላቅ እህታችን በእንግልጣር አፍ አላስቆም አላስቀምጥ አለችን፨ ዶግ፤ካው፤ካት የመሳሰሉት የእንሰሳ ስምብቻ ሳይሆኑ የእኛ መሰደቢያ ሆኑ፨ በ 1ኛ ወሰነ ትምህርት ደብል አልፌ የታላቄን ታላቅ ደረስኩባት ግን የ1 ሰሚስተር ልዩነት በእንግሊዘኛው መመጣጠን አልቻልንም፨ ከተወሰኑ ወራቶች በሁዋላ እንደምንም ብዬ ደረስኩባት፨ ወንድ መሆኔና ስራ አለመስራቴ በስራ የምትደክመውን እህቴን መብለጥ ጀመርኩ፨ ሴት ልጅ ለአቅመ ሄዋን ከደረሰች ማማሩ ሌላ ችግር ያመጣል በሚለው አመለካካት እህቴ፡ ትምህርቷን አቋርጣ ባል አግብታ ዛሬ የአራት ልጆች እናት ሆናለች፨ መሰረተ ትምህርትን ያመጣው ደርግም ከወንዴዎች ጋር ( ደርግ እንደሚለው) ጦርነት ላይ ስለነበር፤ ወጣቶችን በውድም በግድም እያለ ያዘምት ስለነበር ቤተሰብ ወደ ጦርነቱ እንዳይሄድ በመፍራት ትምህርቱን አቋርጦ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ እንዲኖር በማድረጋቸው፤ወንድሜም ከ6ኛ ክፍል በላይ ሳይቀጥል፤ቀርቶ እርሱም አግብቶ ዛሬ የአራት ልጆች አባት ሆኗል፨

የ1ኛ ደረጃ ት/ቤት ቆይታ በጣም ደስ የሚል፤ ቀስ በቀስ ከበርካታ ነገሮች ጋር የመላመድ፤ አካባቢን የማወቅ፤እድሎችን ፈጥሮልኛል፨ በዚህ በ1ኘኛ ደረጃ ት/ቤት ቆይታዬ፤ ለፋሲካ ማንም ሳይፈቅድ፤ አንድ ሳምንት፤ ት/ቤት ዝግ ነው፡ ማንም ተማሪ ብቅ አይልም፡ ምናልባት መ/ራኑም የሚመጡ አይመስለኝም፤ ለጥር ኢየሱስና ጥር ስላሴ፤ በምንም ቀን ይዋሉ፤ ማስፈቀድ የለም ዝም ብሎ መቅረትና ቤተክርስቲያን መሄድ ማንም ሊገረስሰው የማይችል ያልተጻፈ ህግ ነው፨ የተማሪ መጽሀፍ፤ ምናልባት አንድ ለአራት ወይንም ለአምስት ስለሚሰጠን ብዙዎቻችን የመጽሐፍን መልክ የምናውቀው አይመስለኝም፨ እንደ ጽዋ ጠጪ መጽሐፍቶቹ ባወጣነው ህግ መሰረት ከአንዳችን ወዳንችን ይተላለፋሉ፨ በልጅነት እድሜ የ1ኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ይገርሙኝ ከነበሩት አንዱ ሬዲዮ ሲያስተምር መስማት ነበር፨ ት/ቤታችን ካለው ሬዲዮ ቀደም ብዬ አውቃለሁ፤ ትልቁ አጎታችን ቤት አለ፤ እርሱ ያኔ ለእኛ የማይገባን ወሬ፤ አንዳንዴ ደግሞ ደስ የሚል ዘፈን የሚየዓስደምጥ እንጂ እንደት/ቤቱ የትምህርት አይነት፤የክፍል ስም እየጠራ የሚያስተምር ነበር፨ 2ኛ ክፍል እያለ በወርሃ መስከረም ወይ ጥቅምት ላይ ይመስለኛል፡ መ/ሩ ነገ ትምህርት በሬዲዮ ስለሚጀምር በጥዋት እንድትመጡ ተብሎ ተነግሮናል፨ ወንድምና እህቴ ገና ትምህርት አልገቡም፤ጉልበታቸው ለስራ ስለሚፈለግ፨ እና የዚያን ዕለት በሬዲዮ ትምህርት ተማርን፤ ምሳ ሰአት ይህንን ትልቅ ዜና ለወንድሜ ለመንገር ወደ ምሳ መሄድ ሳያስፈልገኝ እርሱ ወደላበት ስራ ሄድኩኝ፨ በቃ ሬዲዮ የክፍል ስም የትምህርት አይነት እየጠራ፤ ለእኘዓ ሁሉ ሰላምታ እየሰጠ ያስተምራል ብዬ እርሱንም ስራ አስፈታሁት፨ ስለሬዲዮው ይጠይቀኛል፤ እመልሳለሁ፨ ወደ መጨረሻ ላይ ግን ሬዲዮ ሁለተኛ ከፍል ብሎ 1ኛ ከፍል ቢወስዱት በምንያውቃል ሲለኝ፡ ያውቃል አይሰራም እሺሺሺ ይላል አልኩት፡ እንግዴህ ይህ ፈጠራ ነው፡ ከወንድሜ የተሻልኩ መሆኔን ማስመስከሪያ፨ ይህንን ጉዴን ያወቁት ግን አንድ ቀን ነው፨ መ/ሩ ሬዲዮው ካስተማረ በሁዋላ ያልገባችሁ ጥያቄ ካለ ጠይቁ እያሉን፤ ያልተዘጋው ሬዲዮ እሺሺሺ ማለቱን ትቶ የ5ኛ ክፍል ህብረተሰብ ሳይንስ ማስተማር ጀመረ፤ እኔና ወንድሜ አይን ለአይን ተጋጨን፡ ነቅቻለሁ አይነት ነው የእርሱ አስተያየት እኔ ደግሞ ውሸቴ ተጋለጠ ነው፨ የሚገርመው በዚህ ጉዳይ እሳቅን ያወራነው በጣም ትልቅ ከሆንን በሁዋላ ነው፨

በ1ኛ ደረጃ ተማሪነት ወቅቴ ከማልረሳው ትልቁ ጉዳይ የእጅ ስራ የሚባለው ክፍለ ጊዜ ሲሆን፤ ሁላችንም በርካታ የእጅግ ስራዎችን እንሰራለን፨ ሹራብ፤ከአክርማ፤ቆብ፤ከእንጨት የግብርና መገልገየዓ ቁሳቁሶችን እንሰራ ነበር፨ እነዚህ የሚሰሩ የእጅ ስራዎች በተለይም በሴቶች የሚሰሩ የስፌት ዕቃዎች፤ ዳንቴሎች፤ የሚለበሱ ሹራቦች፤ ማርክ ከማግኘት ባሻገር ዋጋ ተተምኖላቸው፤ ለወላጅ ይሸጣሉ፨ ብዙ ጊዜ ሹራቦቹ የሚሰራውን ልጅ ታሳቢ ተደርገው ስለሚሰሩ የሚገዛቸው የዚያው ተማሪ ወላጂ ነበር፨ ይህ በመሆኑ ለበርካቶቻችን የማናወቅውን ክህሎት ለማዳበር እድል ከፍቶልናል፨ ተግባር ተኮር ትምህርት ማለት ይህ ይመስለኛል፨ የእርሻ ትምህርት ቢኖርም፤ ብዙ በተግባር የተደገፈ አልነበረም፨ የማስታውሰው፤ ባቄላ ተክለን ስር አወጣጡን፤ ጸሐይ ብርሃን ሲያጣ ጸሐይ ለመፈለግ ወደ አንድ አቅጣጫ ማዘንበሉን በተግባር አይተናል፨ ነገር ግን መስኩን ላቦራቶሪ አድርጎ ብዙ ተግባር ተኮር ትምህርት መስጠት ይቻል ነበር፨ በርግጥ መ/ራኖቻችን ጋርም የእውቀት ብሎም የክህሎት ችግር ሊኖር ይችል ይሆናል፡ ከዚያም በላይ እኛም ለእርሻ ትምህርት ያለን አመለካከት ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል፨

4ኛ ክፍል ሳለሁ አባቴ ወደ ወረዳ ዋና ከተማ  ደነባ ይዞኝ ሄደ፨ ደነባ ያኔ በጣም ድምቅ ያለች ደስ ደስ ያላት ከተማ ነች፨ ለጂም አመታት ከተማ ሲባል ውስጤ የምትመጣው ደነባ ነበረች፨ መኪናዎች አልፎ አልፎም ቢሆን ይንቀሳቀሳሉ፨ በርካታ ቤቶች ላይ ስም ተፅፎ ምን አይነት አገልግሎት እንደሚሰጡ ከበራቸው ላይ ተለጥፏል፨ ለምሳሌ ነገሰ ሸንቁጥ ሱቅ፤ ሲሳይ ብሩ ጠጅ ቤት፤ በቀለች ገብሩ ቡና ቤት፤ ገመቹ ዲነግዴ ሱቅ፤ሽብሩ ዘገየ ሻይ ቤት፤ ተዋበች ከልሌ ቡና ቤት፨ አባቴ እንደደረሰን የሚያውቀው ቡና ቤት ስለነበር እዚያ ሄድን፤ ምግብ ገዛልኝ፤ ነጭ እንጀራ እጅግ ነጭ በሆነ የንኬል ትሪ ቀረበልኝ፡ ለስላሳም ቀርቦልኛል፨ የእንጀራውን ንጣት ሳደንቅ ለመቁረስ በጣም ዘግይቼ ነበር፨ አባቴ ከሌሎች ከሚያውቃቸው ሰዎች ጋር እያወራ ስለ ጉብዝናዬ ይተርክላቸዋል፡ እርሱ አይበላም፨ ምግብ መጨረስ ነውር ስለሆነ ያንን የሚጣፍጥ የነጭ ጤፍ እንጀራ እያማረኝ ተውኩት፨ ለስላሳው ግን፤ የጠርሙሱን አፍ አፌ ውስጥ አስገብቼ አልወጣ ብሎኝ ስታገል፤ በግድ አወጣሁት፤ ለስላሳው ገንፍሎ ልብሴን አጠበው፨ አባቴ አይዞህ፤ይደፋ ብሎ አፅናናኝ፨ 

በአንደኛ ደረጃ ሳለሁ የስዕል ክፍለ ጊዘ ነበር፡ ስዕሉም ሳሉ እየተባልን እንፈተን ነበር፨ ያው አብዛኞቻችን በሬ፤ ጎጆ ቤት፤ እንስራ የመሳሰሉትን እንስል ነበር፨ የያኔ የክፍላችን አንድ ወጣት አሁን ካህን የሆኑ ወታደር ስዕል ሳሉና እጁን ሲስሉ ስዕሉ እየተበላሽ ሲያስቸግራቸው፡ እጅ የሌለው ሰው ሳሉና ከስዕሉ በታች ጀግናው የኢትዮጲያ ጦር የሶማሌን ወታደር እጁን ቆርጦ እንደጣለው የሚል መግለጫ ጨመሩበት፨ ይህ ሀሳብ ሊመጣ የቻለው አባታቸው በጡረታ የተገለሉ ሻምበል ስለሆኑ ምናልባትም፤ በሶማሌ ጦርነት ጊዜ ተሳትፈው ልጆቸው ይህንን መሰል ታሪኮች ከእርሳቸው ሰምቶ ሊሆን ይችላል፨ የዚያ ዘመኑ ተማሪ አከበር፤ሸዋሰማ ግን በጣም ቀልደኛና ተጨዋች ብቻ ሳይሆን ጎበዝ ተብሎ ከሚጠሩር ተርታ ነበር፨ እንዲህ እንዲህ እያለ 6ኛ ከፍል ደረስኩና ለሚኒስትሪ ፎቶ ለመነሳት የተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ደብረብርሃን ከአባቴ ጋር ሄድኩኝ፨ ይህ ጉዞ ኮለምበስ አሜሪካን ለማግኘት ካደረገው ጉዞ አይተናነስም፨ ለመጀመሪያ ጊዜ በሎንችና ሁለት ሰአት መንገድ፤ መሄድ፤ ቀንና ሌሊት መብራት ካለበት ከተማ መሰንበት፤ መኪናም እንደሬዲዮና ቴፕ ዘፈን ሲዘፍን መስማት፤ መስኪድ፤ማየትና አዛን ሲባል መስማት፤ በፈረስ ጋሪ መሄድ'አስፋልት ማየት፤ ብር እየተቆጠረ ከሚሰጥበት ባንክ ቤት መግባት፡ ኧረ ስንቱ ይነገራል፨ አባቴ ለሌላም ስራ ስለመጣን 3 ቀን አደርን፨ ደብረብርሃንን በደንብ አየሁዋት፡ ፎቶ ሲራክ የመጀመሪያውን ጉርድ ፎቶ ግራፍ ተነሳሁ፤ ለማስረጃ የመጀመሪያው ጉርድ ፎቶ ግራፌ ከነካርዱ ተለጥፏል፨ የት/ቤታቸን የመጀመሪያ ዙር የ6ኛ ክፍልሚኒስትሪ ፈተና ተፈታኞች ቁጥራችን 21 ሲሆን ትልቁን ውጤት ያመጣው፤ከፈለኝ ሀብቴ የሚባለው ጓደኛችን ሲሆን 100 ፐርሰንት ነበር ያመጣው፤ አፈሩን ይቅለላትና ተናኘ ሃ/ጊርጎስ እና ፀጋው መኮንን 98 ፐርሰንት ሲያመጡ፤ ከታች ካርዳቸውን ያያዙት የዚያ ዘመን ጨቅላ ደግሞ ከታች ያለውን ውጤት አምጥተዋል፨ የዚያ ዘመን የክፍላችን ዝቅተኛ ውጤት የይብራለም ሞገድ ሲሆን ያመጣችው 65 ፐርሰንት ነበር፨ ይብራለም በአሁኑ ሰአት የት እንዳላች አላውቅም፨ ይብራለም፡ስልጡን የምትባል፤ ከብዙዎቻችን ቀድማ ከተማን የቀመሰች ልጅ ነበረች፨ በሸዋ ክፍለሀገርም በሩጫ ታዋቂ የነበረችውና እስከ ጀርመን ድረስ ሄዳ ሜዳሊያ ታሽነፍ የነበረችው ግርድሽ ንጉሴም የክፍላችን ተማሪ ነበረች፨ ግርድሽ ከብዙዎችን ቀድማ ሰአት ያሰረች፡ ተማሪ ነበረች፤ ሩጫ በሰጣት ትሩፋት፨ ሰአትን በተመለከተ ግርድሽና አደፍርስ ከፈለው የተለየ ገጠመኝ አላቸው፨ አደፍረስ ብዙ ጊዜ ሰአት ሲጠይቃት ሩብ ጉዳይ 20 ጉዳይ ምናምን በሚባልበት ሰአት ስለሆነ፤ በጭንቅላቱ የሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ኖሮ አንድ ጊዜ ግርድሽ ስንት ሰአት ነው፤ መቼም የአንች ሰአት ያለ ጉዳይ አያውቅ ያላት ብዙዎቻችን እስከዛሬ ድረስ ስንገናኝ የምናነሳው ትውስታቸን ነው፨                                          



No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...