ሀገሬን ጎድላ አየሁዋት
ሊነጋ ሲል በከባዱና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ማለፍ፡
ግድ እንደሚሆን ብናምንም፡ ከባዱና ድቅድቅ ጨለማው ግን ለሀገሬ በጣም ረዘመባት፡፡ በትንሽዋ እድሜ ሀገሬ ጦርነት፤ረሀብ ችግርና
እንግልት አስተናግዳለች፡፡ ከእኔ ከቀደም ያሉት የሀገሬ ዘመናትም፡ ከአሁኑ ትንሽ ይሻሉ ካልሆነ በስተቀር ችግሮች ነበሩ፡፡ በርግጥ
ችግሮች መልካቸውን ይቀይራሉ እንጅ መቼም ቢሆን ከችግሮች ነጻ መሆን አይቻልም፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ ሀገሬ የገጠማት ችግር፡ ከታሪኳና
ከእድሜዋ ልክ ሳይሆን ሲቀር አንገት ያስደፋል፤ያሳዝናልም፡፡ እንደክርስቲያን ተስፋ አልቆርጥም የማያንቀላፈው፤ ከአይን ጥቅሻ ፈጥኖ
የሚደርሰው አምላክ ፊቱን ወደ እርሷ ባዞረ ጊዜ ግን ችግሮቿ ሁሉ ከእግሯ በታች እንደሚሆኑ አምናለሁ፡፡ ያኔ ታዲያ ችግሮች ሁሉ
የተወገዱላት፤ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት፤ የሁሉም ቤት ትሆናለች ሀገሬ፡፡ ለዚህ እውን መሆን የእኔን ድርሻ ሳልዘነጋው ማለት ነው፡፡
ባለፉት ቀናት በምድረ አረብ ባልተገባ የአኗኗር
ዘዴ የሚኖሩት ወገኖቻችን ለማስወጣት መንግስት በከፍተኛ ደረጃ እየሰራበትና፡ ምናልባት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሀገር መመለስ እንደሚጀምሩና
ሀገራቸው ሲገቡም ማረፊያ ቦታዎች እንደተዘጋጁ በምስልና በድምጽ ሰምቻለሁ፡፡ መንግስት፤የወሰደው ትክክለኛ መንገድ ይመስለኛል፡፡
ሀገር እናት ናት፡፡ እናት ልጆችዋን ጠዋት ልጄ በሰላም ወጥተህ/ሽ ተመለሽ ብላ ግንባር ስማ፡ በፍቅርና በስስት አይን ትሸሻለች፡
ሲመለሱ እጆችዋን ዘርግታ፡ በእቅፋዋ፡ በዋጋ የማይተመነውን ፈገግታ ለግሳ፡ በጸሐይ የጠቆረውን ፊት አብሳ እንኳን ደህና መጣችሁ
ብላ የውጭውን መከራና ድካም በአንዴ እንደምታስረሳው፡ ሀገርም ይህንን ለዜጎችዋ ብታደርግ እሰይ ያሰኛል እንጂ ለምን አያስብልም፡፡
እናት ለሚረብሸውም፤ለጨዋውም፡ ለሰነፉም ለጎበዙም ልጅ ያላት ፍቅርን እንክብካቤ አንድ ነው፡፡ ሰነፍ ስለሆንክ ቁርስ አትበላም አትልም፡
ተገቢውን ቁጣና ምክር ትሰጣለች እንጂ፡፡ ሀገርም ይህንን ማድረግ ሲጠበቅባት በዚህ በኩል ጎድላ አይቻታለሁ፡፡
ከበርካታ ቦታዎች ህገወጥ ተብለው በተፈረጁ ቡድኖችና
በህጋዊ መዋቅር ስር ሆነው ህገወጥን ስራ በሚደግፉና በሚያበረታቱ ባለጊዜዎች የተነሳ በርካታ ሚስኪን ወገኖቻችን መከራ ደርሶባቸዋል፡፡
ከሞትም የከፍ ሞትና እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ ያለ እድሜያቸውና በማያውቁት ጉዳይ የተገደሉ፤ አካላቸው የጎደለ፤ ባልጸና እግራቸው፡
የማይደፈረውን የስደት ኑሮ የተጋፈጡ በርካታ ህጻናቶችን፡ አይተናል፡፡ እነዚህ ህጻናት አድገው ጤነኛ ዜጋ ስለመሆናቸው ማንም እርግጠኛ
መሆን አይችልም፡፡ በንጹህ ህሊናቸው ያዩት ግፍና መከራ በህሊናቸው ታትሞ ነገ ለበቀል፡እንደማይነሱ ማንም ማስረጃ መስጠት አይችልም፡፡
ይባስ ብሎ መከራን ሸሽተው ሰላም ነው ወደሚሉት አካባቢ ቢደርሱም ሰላም ያሉት፤ያስጠጋኛል ያሉት ሀገርና ወገን ግን ወደዚህ ወደዚያ
እያደረገ መከራውን ሲያበዛባቸው፡ ያሉ ዜጎቻችን፡ችግራቸው፡ በእጅጉ እንደሚገዝፍ ማንም አያውቀውም፡ብዬ ለመናገር፡ሀገሬንና የሀገሬን
ሰው አላውቀው ማለት ነው፡፡ ይህች ሀገር እኮ እንግዳ ሲመጣ አልጋውን ለቆ፡ እግር አጥቦ፤ ለእርሱ ፡ዘወትር፡የማይጠቀምበትን ቁሳቁስና
ምግብ ለእንግዳው የሚሰጥ ህዝብ ያለባት ናት፡፡ ዛሬ በዚች ሀገር በሁሉም ቦታዎች በስደተኛ ጣቢያዎቹ እየተንገላቱ ያሉ በርካታ ህዝቦች
አሉ፡፡ እነርሱን በድንኳን ተቀብላ ለማስተናገድ ቀና ያልሆነች ሀገር ከስደት ተመላሾችን ፍራሽ ዘርግታ ለመቀበል ቀናደፋ ስትል፡
ሀገሬ ሆይ እንድል አስገድዶኛል፡፡ በሀገር የተፈናቀለው፡ አምራች፤የሀገር ዋልታና ማገር የሆነው ገበሬውና ቤተሰቦቹ ናቸው፡፡ ገበሬውና
ቤተሰቦቹ ከአረብ ሀገር ካሉ ስደት ተመላሽ ዜጎች አያንሱም አይበልጡምም፡፡ እርሱም ንጹህ ፍራሽ ባይሆንም ከጸሐይ ይጠለልበት ከዝናብ
ይከለልበት ድንኳን ይሻል፤ የሚቀምሰውም ምግብ ይሻል፡ ከሁሉም በላይ ተረጋግቶ የሚያርፍበት ቦታ፡፡
መቼም የሀብት እጥረት የሚለው ጉዳይ ለገበሬው
ሲሆን ገኖ ይሰማል፡፡ ሀገሬ ሀብት አላጣችም፡፡ ግን ፍትሀዊና ቅደም ተከተላዊ የሀብት ድልድል አለማድረግይመስለኛል ችግሩ፡፡ መከራ
በበዛባት ሀገር ውስጥ በየጊዜው በሰፋፋ አዳራሾችና በመናፈሻዎች የሚደረጉ መመሰጋገኛ ፕሮግራሞች፡ የፕሮግራማቸውን ይዘት ሳይለቅ
በቅናሽ፤ ሲሆን በሻይ ቡና ብቻ አድርጎ ቀሪውን ወደ ተፈናቃዩ፡ ማድረግ፡ ሀገር ሰላም ስትሆን ሊደረስባቸው የሚችሉ ስራዎችን ማዘግየትና
ዜጋን መታደግ ግድ የሚል ይመስለኛል፡፡ ከምን አይነት ልማት የሰው ህይወት ይቀድማል፡፡
ለማንኛውም፡ በስደት አለም የነበራችሁ ወገኖቼ
እንኳን በሰላም ተመለሳችሁ ለማለት ነው፡፡