Saturday, March 26, 2022

የ2014 የ12 ከፍል ብሔራዊ ፈተና

                          የ2014 የ12 ከፍል ብሔራዊ ፈተና ገመና

በሀገር ውስጥ በነበረው ግጭትና በኮሮና ምክንያት መደበኛ የፈተና ጊዜውን ሳያከብር በሁለት ዙር የተሰጠው የ 12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ከተገለጸበት ከጥቂት ቀናት በሁዋላ ወደ ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጄንሲ፡ እና ወደ አንጋፋው የትምህርት ሚኒስቴር  ህንጻ በየቀኑ ሊባል በሚቻል ደረጃ ተመላልሻለሁ፡፡ ሐገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጂንሲ ህንጻው በእድሳት ላይ ያለ በመሆኑንና ከፈተና ጋር በተያያዘ ወደ ውስጥ መግባት እጅግ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ለተወሰኑ ቀናት ለታክሲ፤ለዳቦ፤ለዘይት እንደሚደረገው ሰልፍ ተሰልፎ መግባትም ተጀምሮ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ከውስጥ ያሉት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በአቅማቸው ባለጉዳይን እና ቅሬታን ለመቀበል ጥረት ቢያደርጉም ስህተት ለማረም ግን ያላቸው ተነሳሽነት እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ምን ያክል ጥንቃቄ ተደርጎ እንደተሰራ ያስረዳሉ እንጅ በጥንቃቄ ውስጥ እንኳ፡ሊፈጸም የሚችል ስህተት ስትነግሩዋቸው መስሚያቸው ጥጥ፤ ፊታቸው የነሐሴን ደመና ይመስላል፡፡ ባለጉዳይን ከመሰልቸታቸው የተነሳ፡ ወደ ትምህርት ሚኒስቴር መሔድ የሌለበትን ጉዳይ ከራሳቸው ላይ አዙረው ተገልጋይን በተለይም ክልል አቋርጠው የመጡ ወላጆችን ይልቁንም አካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች ፡ ሲያጉላሉ ለተመለከተ ህዝብን ማገልገል ምንያክል ውሃ እንደበላው ማሳያ መንገድ ነው፡፡ ባለግርማ ሞገሱ ትምህርት ሚኒስቴር ህንጻ ውስጥ ያሉት ባለስልጣናትና በስራቸው ያሉ ከፍተኛ ባለሙያዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ባለጉዳይን ሊያስተናግዱ ቀርቶ በስራ ሰዓት ቢሮዋቸው ውስጥ አለመገኘታቸው፡ በስንት ሰኣት እንደሚገቡ እንኳ መረጃ አለመተዋቸው ህሊናን የሚጎዳ ከመሆኑ ባለፈ ችግርን ለመፍታት ያላቸው ተነሳሽነት ተገልጋይ በማማረር ወደ ዚህ ግቢ እንዳይገባ አድርጉ ተብለው ገለጻ የተሰጣቸው ይመስላል፡፡ ከላይ ያሉትን ሁለቱን ዋና ባለስልጣናት ለማግኘት ቀርቶ ደብዳቤ ወደ ሚመለከተው መመራቱን እንኳን ከሁለት ሶስት ቀናት በሁዋላ በስልክ ነው የሚነገረው፡፡፡

ለዘመናት የገዘፈ ህንጻውን እያየሁ የማደንቀው እናት መ/ቤቴ ትምህርት ሚኒስቴር የደንበኛ አገልግሎትን በዚህ መሰል መንገድ ሲያስተናግድ ማየቴ እጅግ በጣም አሳፍሮኛል፡፡ ከደንበኛ አገልግሎት አሰጣጥ ባለፈ፤ ተማሪዎች በመከራና በጭንቅ ውስጥ ሆነው የተፈተኑትን የፈተና ውጤትን በተገቢው መንገድ አለማረምና ተገቢውን ውጤት አለመስጠት ግን የሚኒስቴር መ/ቤቱ ትልቁ የታሪኩ ጥቁር ነጥብ ሆኖ መመዝገቡ፡ እጅግ ያሳፍራል፡፡ ሁሉንም አይነስውራን ተማሪዎች ኖርማል ብሎ ጉዳታቸውን በይፋ መካድና  በማይገባቸው ነጥብ መገምገም፡ይህንንም ስህተት ለመቀበል ያለው አንባጓሮ እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ጦርነቶች ቢኖሩም በተወሰኑ ቦታዎች ያለው አንጸራዊ ሰላም ለተወሰኑ ተማሪዎች አንጻራዊ የሆነ ጠቀሜታ ስላለው በተለያየ ሜዳ የተጫወቱ ተጫዋቾችን በተመሳሳይ ዳኛ መዳኘት ግን ተገቢ አይደለም፡፡  የዚህ አመት የትምህር ሚኒስቴር ስህተት ስህተቱን መስራቱ ብቻ ሳይሆን ስህተቱን ተቀብሎ አለማስተናገዱ፡ ስህቱን ለመቀበልም ዝግጁ የሆኑ ባለሙያዎችና አመራሮች አለመኖራቸው ነው፡፡



No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...