መስከረም ------ ህዳር-------
በልጅነቴ እረኛ እያለሁ፡ በዘያ ዘመን ከነበሩኝ ጓደኞቼ ጋር በአረንጓዴው ስፍራ ከብቶቻችንን
እየጠበቅን፤ የባቄላ፤ የአተር፤የሽንብራና የምስር እሸታችንን እየጠረጠርን ስንጠግብ ከምናጎራጉራቸው ዘፈኖች መካከል
መስረከም ሲጠባ ህዳር ሲታጠን
እልክልሻለሁ ልቤን በሳጥን፡፡
የምትል ያኔ ትርጉሟ እንኳ ምንድነው
ብዬ የማልጠይቃት ግጥም ከእንጉርጉሮዎቻችን መካከል አንዱዋ ነበረች፡፡ አሁንም ቢሆን ትርጉሙ ምንድነው የሚለውን ከመጠየቅ ውጭ፡ ውስጤ የሚገባኝ ነገር
ትክክል ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ብቻ ይህ አፍቃሪ ባለፉት የክረምት ወራት፡ ወንዞች ሞልተውበት ዝናብ መንቀሳቀሻ አሳጥቶት
በርቀት ያለችውን አፍቃሪውን ማየት እንደተቸገረ፡ብሶትና ፍቅሩን መግለጫ ትመስላለች፡፡ ምንም እንኳን፡ደገኛው የዝናብ ወራት ወጥቶ
የእርሱ ተከታይ የሆነውና ምድር በአረንጓዴ ያለበሳት፤ መስከረም፡ጥቅምትንና ህዳርን አስከትሎ ቢመጣም፤ አረም፡ ባቄላ ሰበራና ሌላም
ተያያዥ በርካታ ስራዎች ሊኖሩት፤ ስለሚችል እርሱ አሁንም፡ ሊያያት ባለመቻሉ እያዘነ፡ ልቤ ግን አሁን እንዳፈቀረሽ
ነው፡ ካላመንሽ በድኔን አስቀርቼ ለመልክተኛ ልቤን በሳጥን ልኬልሻለሁ፡
ጠብቂው፤ያዠው፡ መከር ሲሰበሰብ በየካቲት እመጣለሁ አይነት መልዕክት ይመስለኛል፡፡
ያ
የእረኝነት ዘመን አለፈና ትልቅ ሰው ተሆኖ፡ ህዳር ሲታጠን የሚለው ወሬ ሲወራ በወርሃ ህዳር፡ በለምለሙ መስክ ላይ የባቄላ እሸት
እየጠበስን ሆዳችንን በባቄላው፡ አየሩን ደግሞ በጭሱ የምናጠግበውና የምናጥነው፡ ትዝታ ግን አይረሳም፡፡
የሽንብራው
ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ
የትም
የትም ዞሮ ትዝ አለኝ መንደሬ፡፡ አይደል ነገሩ፡፡
በህዳር
11 ከአሁን በፊት፡ ሁለት ወሳኝ የሆኑ፡ የህይወት ሁነቶችን ከውኜባቸዋሉ፡፡ በዚህ አመትም ህዳር 11 የዋለው፤በዕለተ ሰንበት፡
ስለነበር፡ ምንም እንኳ ስራ ላይ ብሆንም በነጋታው ያለውን አመታዊውን ቅዱስ ሚካኤል በኣል በአጥቢያዬ፤ ከቤተሰቦቼ ጋር ለማክበር
አመሻሹም ላይ በልጆቻችን አነሳሽነት በጋራ መኖሪያ፡ ህንጻችን፡ ላይ በቅርብ በመሰረትነው የጋራ፤ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍና እንዲጠናከር
የራሴን አስተዋጽኦ ለማድረግ ውጥን ውስጤ ስለነበር፡ የሰኞን ጉዞ በጥበብ ወደማክሰኞ፤አሻግሬው ስለነበር፡ ውስጤ ደስተኛ ነበር፡፡
ግን ደስታዬ 24 ሰኣት ሳይሞላው፡ ይህንን ፕሮግራም የሚያፋልስ ሌላ ካለኝ ኃላፊነትና ስልጣን ውጭ የሆነ ጉዳይ ተፈጠረ፡፡ በቃ
የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡ እንዴውም ቅዱስ ሚካኤል በወላይታ ሶዶ ደብረመንክራት አቡነተክለኃይማኖት ገዳም በረከቱን እሳተፋለሁ ብዬ
ውስጤን በማሳመን፡ እሁድ ህዳር 11፡ ጉዞ ወደ ወላይታ፡ በፈጣኑ መንገድ፡፡ በዕለቱ፡አዲስ አበባ በታላቁ ሩጫ የተነሳ ጠዋት መንገዶቿ
ስለሚዘጉ፡ ረፈድ አደርግን ለመውጣት ቀጠሮ አሰርንና ወደ አራት ሰኣት ገዳማ አዲስን ለትተናት ቱዲ ፈጣን መንገድ መግቢያ ደርሰን
ረጁሙን መንገድ ተያያዝነው፡፡ አብዛኛውን የመንገዱን ክፍል በእጄ ላይ ያለውን ኦርቶጵያ የሚል መጽሀፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ ልክ 5፡30 አካባቢ፡ ሞጆን አልፈን፡ጉዞአችንን
ቀጥለናል፡፡ አልፎ አልፎ ቀና እያልኩ ግራ ቀኙን ባይም፡ ንባቤ ላይ ቸክያለሁ፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በሁዋላ ወይኔ የሚል ድምጽ
ከአሽከርካሪው ሰምቼ ቀና ስል እጀግ በርካታ የበግና የከብት መንጋ የፍጥነት መንገድ አጥሩን አቋርጦ፤ ከሁዋላ በእረኞች በጅራፍና
ዱላ እየተደበደበ አንዱና አስፋልት አቋርጦ በእኛ የመሄጃ አስፋልት ላይ ሲደረስ፡ እኛም ስንደርስ በቁጥር ከሚበዙት እንሰሳት፡ ጋር
አንድ ላይ ነበር፡፡ በተፈቀደልን የፍጥነት ገደብ ስንፈጥን ስለነበርን፡ አሽከርካሪው የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም አደጋውን ማስቀረት
አልተቻለም፡ ምናልባት ወደ ግራ ቢይዘው ከእንሰሳቱ ይልቅ እረኞቹ ላይ አደጋው ይበረታ ነበር፡፡ ከመኪናችን፡ ውጫዊ አካል ጉዳትና
ከተወሰኑ እንሰሳት መጎዳት በስተቀር ምንም አይነት አደጋ አልነበረም፡፡ መቼም ፈጣሪ ጥበቃው ብዙ ስለሆነ አደጋውን አራቀው እንጂ
ከዚህም በላይ ችግር ይፈጠር ነበር፡፡ የሚገርመው እረኞች ከብቶቻቸው ተጎድተውባቸው ከእኛ ጋር መጥተው ይጣላሉ፤ የህግ አካል እስከሚደርስ
ትንሽ እንቸገራለን፡ ብዬ ባስብም እረኞች ግን እየበረሩ አድረሻቸውን አጠፍ፡፡ ምክንያቱን ሳጣራ ለካስ ከብቶቹ አጥሩን አልፈው ከተገኙ
ቅጣት ስላለው ተይዘው መቀጣት አይፈልጉም፡፡ ምናልባት አደጋውን ያደረሱት ከብቶ ስለሆኑ ይህ ቅጣት ደግሞ ከበድ ሊል እንደሚችል
ስለሚገመት የመጥፋታቸው ሚስጢር ለካ እርሱ ነው፡፡ እንደ መንገዱ ፈጣን የሆነ አገልግሎት የሚሰጡት የፍጥነት፡ መንገዱ የሚመለከታቸው
ባለሙዎች በፍጥነት ደርሰው እኛንም፡ መኪናችንን አንስተው መንገዱ ቶሎ ለትራፊክ ከፍት አደረጉት፡፡ ከዚያ በሁዋላ እኛን እንደ ኳስ
ተቀባበሉን፡፡ እንትና ጋ ሂዱ ስንሄድ፤መጀመሪያ እንትና ጋ፡ እንትና ጋ ስንሄድ ፡ ዛሬ አይመቸኝም፡ ሁሉም ሳይሳካ ሶዶ ሊያድር
የነበረው ቡድን ምስራቅ ሸዋ ለማደር ተገደደ፡፡ በቀጣዩ ቀናት ጉዳዩን ለማፋጠን በጠዋት ተነስተን ተፍ ተፍ ማለት ብንጀምርም፡ ካሰብነው
በተቃራኒ ባላሰብነው ፍጥነት ጥፋቱ ሁሉ ወደ እኛ እየመጣ መሆኑ ገባን፡፡ አብሮን ፕላን ለማንሳት የሄደው፡ አባል
አባል፡ አደጋው ለምን ተፈጠረ፡ የሚልጥያቄ
አነሳ ሹፌር ይመልሳል፡ ፍጥነት ላይ ነበርክ፡ ሹፎር፡- በተፈቀደው
ፍጥነት ገደብ ላይ ነበርኩ፤
አባል፡-ለምን ታዲያ አላቆምክም፡
ሹፎር፡-ለማቋም እኮ ሞክሬያለሁ ግን
እንሰሳቱ ይፈጥኑ ብዙዎችና ፈጣኖች ስለነበሩ አልቻልኩም፡
አባል፡- እና ጥፋቱ የእንሰሳቱ ነው
እያልክ ነው፡
ሹፌር፡- አዎ፡፡
አባል፡-እንሳሰቱ ምን ያውቃሉ፡
ሹፌር፡- እነርሱማ ምን ያውቃሉ ያው የሚነዳቸው ሰው እንጂ፡
አባል፡- እርሱ ምንያደርግ፡
ሹፊር፡-በዚህ
በተከለከለ መንገድ ማምጣት አልነበረበትም፡፡
አባል፡-ሰው አይሰማማ፡ ቢነገረው፡፡
ሹፌር፡ እና
አባል፡- አሁን ጥፋተኛ ነህ አንተ፡፡
ከዚህ በሁዋላ ሹፎሩ መልስ መስጠት አልፈለገም፡፡ በርግጥ በእኛና በአባሉ መካከል፡የቋንቋ ችግር አለ፡፡ እንዴውም እርሱ ይሻላል፡
አማርኛ ይናገራል፡፡ እኛ ደግሞ አፋን ኦሮሞ አንችልም፡፡
ልክ
በመጨረሻ የመንግስት የስራ ሰኣት ሊበቃ ሰኣት ሲቀር ቅን ሰው አገኘንና ጉዳያችን ለጊዜው ያለቀ መሰለ፡፡ አሽከርካሪችን ግን ሌላ
ቀጠሮ ተሰጥቶት ተለያየን፡፡
አደጋው
ከተፈጠረ ከሰዓታት በሁዋላ ለባለቤቴ ስደውል ደረሳችሁ፤ በሰላም ገባችሁ ብላ ጠየቀችኝ፡ ቀስ እያልኩ እያዋዛሁ ሁኔታውን ነግሬያት
ነገ ወደ ቤት እንደምመለስ ስነግራት፡ በቃ እንኳን ተረፋችሁ፡ ቅዱስ ሚካኤል፡ በዓሉን ከእኛ ጋር አብረን እንድናሳልፍ ፈቃዱ ሆኖ
ነው፡ በሰላም ተመለስ፡፡ እንዴውም፡ የማታው ፕሮግራም ላይ የማትገኝ ስለነበር ጎረቤቶቻችንን እንዳዘኑ ነግራኝ አሁን በጣም ደስ ይላል፡ በቃ ነገ በጊዜ ና ብለን ተለያይተናል፡፡
እናም
ህዳር 12ን ቤቴ ተመልሼ በምሽቱ የሠፈር፡ ፕሮግራም ላይ ከጎረቤትና በተሰብ ጋር እጅግ ደስ የሚል ፕሮግራም አሳልፈን የህዳር
11ኑ ትዝታ ለዘመን ሰጥነው አለፍን፡፡ የቅዱሳን አምላክ የአመት ሰው ይበለን፡፡
No comments:
Post a Comment