የምወዳት ባህርዳር
የተሳፈርኩባት ጥያሪ፡ ለመነሳት የሚያስችላትን፡ ሁሉንም ቅድመ ዝግጅት ጨርሳ ልክ ከቀኑ
9.00 ሠዓት ሲሆን ወደ ባህርዳር አየሩን በአቅሟ እየቀዘፈች መብረር ጀመረች፡፡ ገና ወደ ባህርዳር እንደምሄድ ካወቅሁበት ዕለት
አንስቶ፡ ወደ ውቢቷ ባህርዳር በመጓዝ ልቤ አካሌን ቀድሞት ባህርዳር ዘንባባዎቹ አጠገብ ፊቱን ወደ ጣና አዙሮ፡ ተፈጥሮን ማድነቁን
ተያያዞታል፡፡ ኃይለማርያም ማሞ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለን ዳንኤል በሳምንት አንድ ቀን ረቡዕ ተፈጥሮ እናድንቅ ብሎ በየሳምንቱ
በዕረፍት ሰዓት፡ ፊታችንን ወደ ጎሸ ባዶና አቦ ገዳም አዙረን ከፍ ያለ ቦታ ተቀምጠን ተፈጥሮን የምናደንቀውን ጊዜ አስታውሶ፡፡ ከላይ ከሰማይ
ሆኜ ወደታች አዲስ አበባን ከላይ እያየሁዋት፡ሳለ ከጥቂት ደቂቃዎች በሁዋላ ከአይኔ ተሰወረች፡፡ ምንም እንኳ ወቅቱ ደረቅ በመሆኑ
መሬቱን ለመመልከት ብዙ የሚስብ፡ነገር ባይኖረውም፡ እይታዬን ወደ መሬቱ ከማድረግ፡ ግን አልሰነፍኩም፡፡ ይሁን እንጂ፡በጸሐይ አቅጣጫ
ስለተቀመጥኩ ብዙም መመልከት አልቻልኩም፡፡ ደግነቱ በርካታ ተጓዥ ስላልነበር አጠገቤ ባለው ክፍት ወንበር ላይ ቀይሬ ጥቂትም ቢሆን
ከጸሐይ ለመሸሽ ሞከርኩ፤ይሁን እንጂ ወደ መሬት መመልከት ስለማልችል፡የጀመርኩት መጽሐፍ ላይ አይኔን ተከልኩ፡፡ ከአንድ ቀን በፊት የገዛሁትን የሚተራሊዮን፡መጽሐፍ ቢሆንም፡ ጊዜ ስላልነበረኝ፤
እንዲሁም የደራሲውን መጽሐፍ፤አንጻራዊ በሆነ መልኩ ሰፋ ያለ ጊዜ ሳይኖር መጀመር፡ ከመጽሐፍም ከስራው መሆን ስለማይቻል፡ ከርዕሱ
በስተቀር አንዲትም፡ገጽ ማየት አልፈለግሁም፡፡ አሁን ግን ግድ ነው፡ በአንጻራዊነት፤ነጻ፡የሆነ፡ አመሻሽና ሌሊት ስላለኝ፡ ብጀምረው
ከማንበብ የሚያናጥበኝ፡ ጉዳይ ስለማይኖር እስከሚበቃኝ ማንበብ እችላለሁ ብዬ ጀመርኩት፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ ወንዞች አባይ ከጎጃምና
ጎንደር፡ የጀማ ወንዝ ከሸዋ አንድ ላይ ተገናኝተው፡ ወደ ህዳሴ ድልድድ አካባቢ ሲደርሱ ያለውን መልከአ ምድር መመልከት ስለምፈልግ፡
ሁለትና ሶስት ጊዜ ጎንበስ ቀና በማለት፡ መድረስ አለመድረሴን ቼክ አድርጊያለሁ፡፡ ምንም እንኳ ጸሐይዋ አሁንም ጨረሮችዋ ጠንካራ
ቢሆኑም ቦታውን ግን መመልከት ችያለሁ፡፡ ከሰኔ እስከ መስከረምና ጥቅምት ያለው ሃይሉ፡ሁሉ ሙሽሽ ብሎ ዙሪያ ገባው፡ባዶ ከመሆኑም
በሻገር አረንጓዴ፡ ብርድልብስ ይመስል የነበረው መሬት ተጋልጦ ድልድዩ በግልጽ ከርቀት ይታያል፡፡ ወደ ባህርዳር እየቀረብን ስንሄድ
ጢያራዋን ነፋሱ ብዙ አንገላቷት ዘወትር ለማረፍ፤ ጣናን አቋርጣ፡ ገዳማቱንና በሃይቁ ላይ ወዲያ ወዲህ የሚሉትን ጀልባዎች እያሳየችን
የምትበርበትን አቅጣጫ ቀይራ እንድታርፍ አስገድዷት 10 ሰኣት አካባቢ፡ የእለት ሙቀትዋ 31 ዲግሪ ወደ ሆነችው ባህርዳር ከተማ
በሰላም ገብተናል፡፡ ስሙ ከግንቦት፡ 20 ወደ በላይ ዘለቀ አለም
አቀፍ አየር ማረፊ የተቀየረው የአየር፡ማረፊያ ጣቢያ፡ ባለፈው ዓመት በሮኬት መመታቱን የሚያሳብቁ በርካታ ምልክቶች፡ቢታዩበትም፤
የሚሰጠውን አገልግሎት ግን ያስታጎለበት አይመስልም፡፡ በርካታ ተስተናጋጅ ያስተናግዳል፡፡ ከሰሞኑ፡በኦሮማያና አማራ ክልል አካባቢ
በተለይም በአባይ በረሃ በሚባለው ቦታ አሸባሪዎች ችግር ፈጥረው ስለለነበር የመኪናው ጉዞ ስጋት ስላላበት በርካቶች ከመሬቱ ጉዞ
ወደ ሰማዩ መቀየራቸው ጣቢያውን ከሌላ ጊዜ በተለዬ ስራ ያበዙበት ይመስላል በርከት ያሉ ወጭና ገቢዎች ይታያሉ፡፡ ባህርዳር የአየር
ማረፊያ ጣቢያዋን ብቻ ሳይሆን፡ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የሽንፈት ምልክት የሆነውን ሃውልቷን አሽቀንጥራ ጥላ፡ ቃና የማለትና
የአልሸነፍም ባይነት ሃውልቷን አቁማለች፡፡
ፎቶ፡-የሽንፈት
ምልክት የነበረው ሐውልት ወርዶ በዚህ ተተክቷል( ባህርዳር ሰማዕታት ሐውልት) የካቲት 8/2014 ለካቲት 11፣ 3 ቀናት የቀረው
ከህዳር 11 ደግሞ 3 ወር ያለፈው
ከደራሲው መጽሐፎች፡ ስሙ የማይጠፋው
ሲሳይና ባለቤቱ ጋር ሆኜ፤በሚተራሊዮን፡መጽሐፍ አማካኝነት ካነበብከትና ከሰማሁት ጋር አቀናጅቼ በጭንቅላቴ ከሳልኩዋት ቅድስት ኢየሩሳሌም
ገዳም፤ተሳልሜ፤ በብዙ መልኩ ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተቆራኘ ኑሮዋቸውን
የሚገፍትን፡ ትውልድ ሀገራችን ነው ፡ ብለው ፡ሀገራቸው ኢትዮጲያን ለቀው የሄዱ፡ ነገርግን አሁንም በሀገር ፍቅርና ናፍቆት የሚዋትቱ፤የኢትዮጲያዊ
አይሁዶችን፤የአኗኗር ዘይቤ ቃኝቼ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን የሆነው ሲሳይ ከእስልምና እምነት ተከታይ ወንድሙ
ነቢል ጋር ያደረገውን ውይይት፡ አጠገባቸው ሆኜ፤ያየሁ አስኪመስለኝ ድረስ እየተሰማኝ፡ ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ እጅግ ከሚገባው
በላይ አብሬ የኖርኩት ደስታና ሀዘኖቼን የተጋራሁትን አደም ሰይድን፤ በምናቤ እያሰብኩ፡በትዝታ ወደ ኃላ እንድነጉድ አደረገኝ፡፡
የነቢል እውቀትናየሲሳይን ታዛዥነት፤ቀናነት፤ ለእወቀትና ለጥበብ ያለውን ጥማትና ችኩልነት፡ የገዳማዊያኑን፤አባቶች፡ትህትና፤እውቀት፤ከአባቶች፤ያዩትን፡አንድም፡ሳይዛነፍ፡ለትውልድ፡እንዲደርስ
የሚያደርጉትን ትጋት ለማድነቅ እንኳን ጊዜ አጥቼ የዶ.ር አለማየሁ ዋሴን ሚተራሊዮን፡ መጽሐፍ ከእራት በፊት፡ግማሽ በላይ ሸፈንኩት፡፡
ግልብ አንባቢ ግልብ ደራሲ ይሆናል፡ የሚሉ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ጋላቢ አይደለሁ፡ ፍሬውን እየተው ከገላባው ጋር መጋለብ ልምዴ
የሆነ፡፡
ሚተራሊዮንን፡ አስቀምጭ ከእራት በፊት በጣና ሃይቅ፡ ከአብሮ ተጉዋዥ ስራ ባልደረቦቼ ጋር፡
ትንሽ ተንጎራደን ፈለገ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን፡አምላካችንን አመስግነን ወደ ፓፒረስ ሆቴል ትንሽ እግራችንን አፍታተን፡ ወደ
ሆቴላችን ተመለስን፡፡ ዶ.ር አለማየሁ ይቀጥላል በሚትራሊዮን የዋግንና የዝቋላን መልከአምድራዊ ውበት፡ በሲሳይና በኒቢል አንደበት እያስለፈለፈ፡፡ በዝቋላ ውበት
ተመስጦ የነበረው ነቢል ለእረኞች ስለሀገራቸው ውበት ሲጠይቃቸው የመለሱትን መልስ ሲሳይ ሲሰማ አንድ ሌላ ታሪክ ትዝ፡ይለዋል፡ እኔን
ጭምር ወደ፡ ደስ ወዳሰኘኝ ስሜት፡፡ ሰሜን ተራራ ላይ ጓደኛውን ገጥሞት የነገረውን፡፡ በሰሜን ተራራ ያሉ ከብርዱ ጋር በፍጹም የማይዛመድ
ልብስ ለብሰው ያያቸው የሲሳይ ወዳጅ፡ ልጆች አይበርዳችሁም ሲላቸው፡ እንዴ
ጋሼ ሀገር ይበርዳል ያሉትን መልስ፡፡ ውስጤን ምንኛ እንደነካኝ፤ እኔ ነኝ የማውቀው፡፡ ሀገር ቢበርድም፤ቢሞቅም ሀገር ሀገር
ነው አይበርድም፤ አይሞቅም፡፡ ገጣሚው፡ ገብረ ክርስቶስ
ውሸት ነው በበጋ ጸሐይ አትፋጅም
ክረምቱም፡ አይበርድም
እንዲል፡፡
No comments:
Post a Comment