Monday, February 7, 2022

እኔና ኮቪዲ

 

 

እኔና ኮቪዲ ተገናኘን፡

ከህዳር 13/2014 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 22/2014 ዓ.ም ድረስ እጅግ ተከታታይ ስልጠናዎች፤የመስክ ጎዞዎች ቅዳሜና እህድ ጨምሮ ነበሩብኝ፡፡ ወላይታ ሶደ፤ አዳማ በተደጋጋሚ የተጓዙኩባው ቦታዎች ነበሩ፡፡

ሰኞታህሳስ 18/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ገና በቅጡ ከእንቅዋ:ሳትነቃ፡ ማልደው ወደ ቤተክርስቲያን፡ የሚሄዱ ምዕመናን፡ እንደዚሁም ወደ አትክልት ተራ የሚተሙ ተሸከርካሪዎችን፡ እያጀብን፡  ያ በቀን ውስጥ፡በአብዛኛው፤ሰዓት  ጠጠር መጣያ የሚጠፋበትን የጀርመን፡ የመብራትና ኃይሌ ጋርመንት አስፋልትን በከፍተኛ በሚባለው ፍጥነት እየነዳንና ከሹፌሬ ጋር የባጥ የቋጡን እየቀበጣጠር፡ ሸገርን በደንብ ሳትነቃ ጥለናት ወጣን፡፡ ብቸኛ በነበረው አዲስ አዳማ ፍጥነት መንገድ አድርገን በተፈቀደልን የፍጥነት መጠን፡ እያሽከረከርን፡አንድም ከተማ ሳንገባ፡አንድም ጊዜ ሳናቆም ዝዋይ ከተማ በሁለተኛው የሀገሪቱ የፍጥነት፡ መንገድ አድርገን ወጥ ቀማሽ ይመስል በጥዋት ገባን:: ጾም ስለሆነ ወጡን መቅመስ ባንችልም፡የአሳ ጥብስ ሽታ እያሸተትን መንገዳችንን ነካነው፡፡ዝዋይ የሐይቆችና ቡታጅራ፡ዋና ከተማ ነበረች፡ በመጨረሻዋቹ የደርግ ዘመን፤ ሕቀሀት መራሹ ምንገስ ሲመጣ ግን ስሟን ባቱ ብላ ቀይራለች፡ በቅርቡ አሰቃቂ የሚባል ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት የተፈጸመባት፤ ንጹሃን በማያውቁት ጉዳይ የሞት ጽዋን የተጎነጩባት፤ በርካታ የግል ቤቶች ሆቴሎች የወደሙባት፡ ከመሆኑዋ አንጻር፡ ብዙም ትልቅ ክፍተት የሚታይባት ባይመስልም እኔ ግን ዝዋይን በአይኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ካየሁዋት ግንቦት 1985 ዓ.ም ወዲህ እያነሰችብኝ ነው የሄደችው፡፡ በዝዋይ አድሪያለሁ ምሳዬን በልቻለሁ፡ አሁን ግን ዝዋይ ላይ ውሃ መጠጣትም አልመኝ፡፡ አርሲ ነገሌን፤ኩየራና ሻሸመኔ የመሳሰሉትን ከተሞች እያለፍን ልክ ምሳ ሰኣት አካባቢ ሐዋሳ ከች አልን፡፡ ትንሽ የምሳ ሰዓት እስከሚደር ድረስ ሐዋሳን ዞር ዞር ብለን አየናትና አይናችንም፤ ስሜታችንንም ሀሴት እንዲያደርጉ የበኩላችንን ጥረት አደረግን፡፡ ከገብርኤል ወደታች ወደ ሀይቁ እንደገናና ወደ አቶቴ ነዳንና ውስጥ ለውስጥ ወደ ሴንትራል ሆቴል በፈረቃ ከሚወጡና ከሚገቡ ተማሪዎች ጋር እየተጋፋን:ወደ ሐይቁ:ከሐይቁ ወደላይ ወደ ገብርኤል ተሸራሸርን፡ ጸሐይ ቢሆንም አልሞቀንም፡ አልሰለቸንም፡፡ ምሳችንን በላንና ከሁዋላ የሚመጡ የምንጠብቃቸው ጓደኞቻችን ስነበሩ እነርሱ እስከሚመጡ ድረስ የልብ ወዳጆቼ ዘንድ ጓራ አልኩ፡፡ ሠዓቱ ልጆች ት/ቤት የሚሆኑበት ሠዓት ስለሆነ: ልጆቹን ባላገኝም፡ ቤተክርስቲያንናሶዶ የሰጠችንን፡ ባለትዳር ወዳጆቼን ግን አገኘሁዋቸው፡፡ ምንም እንኳ ኮቢድ ከተስፋፋበት አዲስ አበባ በመሄዴ የተነሳ በተወሰነ መልኩ ጥንቃቄ ለማድረግ ብሞክርም፡ ካለን ቅርበት የተነሳ ፡ተቃቅፎ ሰላምታ አለመለዋወጥ በጣም ከባድ:ስለነበር ሰውረነ ከመዓቱ ብለን አምላካችንን ተስፋ አደርገን፡ኮቪዲ ሆይ እባክህ ብለን ሰላምታችንን አልተውነውም፡ተቃቀፍን፡ እንዴ ይሞታል እንዴ በናፍቆት :: ሁለቱም ወዳጆቼ ከሁለቱም ልጆቻቸው ጋር ለአንድ ሳምንት ታመው እንደነበርና ገና ዛሬ ቀና ማለታቸውን፤ባይመረመሩም፡ በሽታው ኮቪድ እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ ከእነርሱም ጋር ቢበዛ ለ 15 ደቂቃ የሚጣለውን ጥለን የሚነሳውን አንስተን፡ እንደወትሮው ብዙ መጨዋወት ባለመቻላችን እያዘንን ተለያዬን፡፡ ሀዋሳም አመታዊውን የገብርኤል በዓል ለማክበር ሽርጉድዋን ርሳ እንግዶቹዋን ከየአቅጣጫዋ መቀበል ጀምራች፡፡ እኛም ደልቦ ገብርኤልን በልባችም እያስብን ከሁዋላ የመጡትን፤ ባልደረቦቻችን ይዘን በጭኮ፤ በብላቴ አድርገን ወደ ወላይታ ሶዶአችን አቀናን፡፡ ሶዶ ገና ስናያት በፈገግታ ሀሹ ሰሮ ያዲ፡ ታ ናቶ ( ልጆቼ እንኳን ደህና መጣችሁ) አለችኝ፡፡ ሶዶ እጅግ በሚገርም ዕድገት ውስጥ ያለች፤ በቦታው ቀኑ፡እየበቀሉ ያሉ ህንጻዎች፡ የሚያምሩ አስፋልቶች፡ጌጠኛ የድንጋይ ንጣፎች፡ ለከተማዋ ልዩ ውበትን ሰጥዋታል፡፡ ይሁን እንጂ ምንም እንኩዋን በርካታ መንገዶች ያሉ ቢሆንም ከዋናዎቹ መንገዶች ባለፈ የውስጥ መንገዶች ሁሉ በሞተር፤በባጃጂናሌሎች ተሸከርካሪዎች የተሞሉ ከመሆናቸው በሻገር በእግር መጓዝን ፈታኝ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ አልፎ ከፍተኛ የሰው ቁጥር ያለ በመሆኑ በእያዳንዱዋ መንገድ በርካታ ሰዎችን፡ መመለከት አስገራሚ አይደለም፡፡

የመጣሁበት ስራ አንድ ቦታ ቁጭ የሚባልበት አይደለም፡ የመስክ ስራ አለው፡፡ መረጃ የሚሰበስቡ 16 ወጣቶችን ማግኘት፡ የሰበሰቡት መረጃ በሚፊለገው መሆን አለመሆኑን ማጣራትና ግብረ መልስ መስጠት፡ያንን መረጃ ወደ ኮምፒዩተር መገልበጥ፡ ከመንግስት አካላት ጋር ስብሰባና ምክክር ማድረግ ከወላይታ ሶዶ ሪፌራል ሆስፒታል፤ ዳይሬክተር ጋር ስብሰባ ማከናወን ይይቅ ስለነበር፡ ጠዋት የተወጣ፤ ዕረፍት የሚገኘው ማታ ወደ መኝታ ክፍል ሲገባ ብቻ ነው፡፡ መስክ በወጣንበት ዶልቦ ገብርኤልን ተሳለምን፡፡ ደልቦ ልክ እንደበፊቱ ዘመን ድምቅ ብሏል፡፡ የመጀመሪያው ግቢ በአብዛኛው፡ በምግብና መጠጥ እና በተስተናጋጆች ተጨናንቋል፡፡ ሁለተኛው ግቢ በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ጠጠር መጣያ እስኪጠፍ ድረስ፡ በምዕመናን ተሞልቷል፡፡

ታህሳስ 20 ወደ 21/2014 ዓ.ም ምሽት ግን ጥሩ ያልሆነ ስሜት ይሰማኝ ጀመር፡፡ ከአንድ ቀን በፊት እስከሌሊቱ ሰባት ሰኣት ቆይቼ ምንም የእንቅልፍና የድካም  ስሜት ያልነበረኝ በማግስቱ ግን የእንቅልፍ ባይሆንም በጣም የሚያስጠላ ድካምና የመዛል አይነት ስሜት ስለተሰማኝ፡ ገና በጊዜው አራት ሰዓት ወደ አልጋዬ አመራሁ፡፡ አንድ በጣም መጥፎ ልምዴ ከቤቴ ስወጣ እንቅልፌ: በፍጹም አይመጣም፡፡ የአልጋ አለመመቸት፡ወይንም ከማድራባቸው ሆቴሎች፡ ችግር፡ ሳይሆን፡ ከቤቴ ውጭ እንደቤቴ የምተኛው ባደግሁበት የወላጆቼ ቤት ብቻ ነው፡፡

በዚያ ቀን ምን እንኳ ወደ አልጋዬ ብገባም እንቅልፍ ባይኔ መዞር አልቻለም፡ ይልቁንም የማንቀጥቀጥና ከፍተኛ የሆነ የእራስ ምታት ስሜት፡ መግለጽ የማልችለው፡ ህመም ይሰማኛል፡፡ ምንም እንኳ ከፍተኛ ችግር ይገጥመኛል ብዬ ስጋት ውስጥ ባልገባም በተወሰነ መልኩ ግን ተረብሻለሁ፡፡ ሌሊቱን ለደቂቃዎች እንኳ እንቅልፍ ሳያሸልበኝ ነጋ፡ ጠዋት ብዙ የከፋ ህመም ባይኖርብኝም፡ ራሴን ዝግጁ አድርጌ ለስራ ተነሳሁ፡ ማስታገሻ: ውጬ ወደ 20 ኪሜ ርቀት ላይ ለስራ ወጣን፡፡ ስሜቴ: ግን ጥሩ አልነበረም፡ ቢሆንም ግን ስራዬን ስሰራ ዋልኩ፡፡ ቀጣዩ ቀናት አርብ ሲሆን ወደ አዲስ፡ አበባ መመለስ ስነበረብኝ በአስቸጋሪው የአላባ ሻሸመኔ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ፡ የህመሙ ስሜት እንዳለ ቢሆንም ጥርስ የማያስከድነው የተረኛው ሹፌሬ፡ ዳኛቸው ሳቅና ጨዋታ ግን ህመሜን ሳላስበው እንድጓዝ አድርጎኝ ነበር፡፡ ቅዳሜን በትንሽ የህመም ስሜት አሳልፌ እሁድ ለስብሰባ ቢሮ መግባት ስለነበረብኝ፡ ቀኑን ሙሉ፤ተወጥሬ ነበር የዋልኩት፡፡ የዚያን ቀን ከስብሰባ መልስ ትክክለኛው ህመምን ማስተናገድ ጀመርኩ፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ ያሉት ቀናት በዚህ መልኩ አልፈው ለገና በዓል በግ መግዛት ስለነበረብኝ እጅግ ጥንቃቄ አድርጌ ገበያ ሄጄ ስመለስ ግን ከፍተኛ ሳል ጀምሮኝ በከባድ የህመም ስሜት ውስጥ ስላስገባኝ፡ የክርስቶስን ልደት በዋዛሜው፡ ከቤተክርስቲያን  ቀርቼ ቤቴ እንዳሳልፍ አድርጎኛል፡፡ ኮቪድ እንኳ ሆኖ;ልደትን  ከቤተክርስቲያን ያልቀረሁት ዘንድሮ ግን አልቻልኩም፡፡ ላለፉት ሃያ ምናምን አመታት ልደትን፡ሌሊት  ቤተክርስቲያን አሳልፌያለሁ፤ከዚያም በላይ ትዳሬን የመሰረትኩት በዕለተ ገና ስለነበር፡ ገና ለእኔ ልዩ በዓል ነው፡፡ ግና ምን፡ያደርጋል ዘንድሮ ከርቀት የሚሰማውን ቀሳውስቱን ድምጽ እየሰማሁ፡ አልጋዬ ላይ ተኝቼ አሳለፍኩት፡፡

በበዓሉ ባሉት ቀጣይ ቀናትም፡ ለተወሰኑ ቀናት ትንሽ ጠንካራ የህመም ስሜት ቢኖረኝም በቀጣዮቹ ቀናት ግን ህመሙ ቀንሶ፤ የድካም፡ ስሜቶች፤ በቀላት ሊገለጹ የማይችሉ፡ተለዋዋጭ የስሜት ህመሞችን፡ ቀዝቀዝ ያሉ ምግቦችንም ሆነ ውሃ ስጠጣ፤ ስልክም ለደቂቃዎች ሳናግሬ፡  የማሳል፡ በተወሰነ መልኩ የመታፈን  ስሜቶች፡ ይሰሙኝ ነበረኝ እንጂ፡ ከባድ አልነበሩም፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው፡ ስበድለውም፡ ሳሳዝነውም፡ ተጨማሪ ቀናትን በጨመረልኝ አምላኬ መልካም ፈቃድ እንደሆነ አምናለሁ፡፡የጠንካራዋ ባለቤቴ፤ ትጋትና እንክብካቤ፤የልጆቼም እንዳይጨንቀኝ የሚያደርጉትና ትጋት የራሳቸው ትልቅ ቦታ ነበራቸው፡፡

እጅግ የሚገርመው ኮቪድ በጣም እፈራው የነበረው፡ ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ እስከአሁኑ ድረስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ፡ ወርሃዊ የቤታችን ወጭ በዝንጅብል፡ ግዥ የተነሳ አሻቅቦ ነበር፡፡ መ/ቤቴን ምስጋና ይድረሰውና ማስክና ሳኒታይዘር ግን ወጭ አልነበረብኝም፡፡ ጥንቃቄም ቢሆን እጅግ፡ከፍተኛ ደረጃ፡ሊባል የሚችል ከቤቴ በረንዳ ስወጣ እንስቶ ማስክ የማይለየኝ ነበር፡፡ ይህ ጥንቃቄ ከመጀመሪያቱ ዕለት አንስቶ ቢሆንም ኮቪድ፡ ግን ይዞኛል፡፡ የሚገርመው እንዴት እንዳገኘኝ፡ማወቅ አለመቻሌና ለወደፊት ልምድ ሳልወስድበት ማለፉ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ጥንቃቄ አለማድረግን እያበረታታሁ ሳይሆን፡ ጥንቃቄ እያደረግን እንደዚህ ከያዘን፡ ጥንቃቄ አለማድረግ የመያዝ መጠኑንና ዕድሉን ስለሚያሰፋ አሁንም ጥንቃቄ እንድረግ መልዕክቴ ነው፡፡




የካቲት 1/2014

አአ

1 comment:

  1. ቆንጆ የጉዞ ማስታወሻ ነው ወግደረስ! አዝናኝና አስተማሪም ነው፡፡ እንኳንም ከኮቪድ ተረፍክ፡፡ የምጠይቅህ ጥያቄ ቢኖር መኪና መንዳት መቻል አለመቻክን ነው፡፡ ምክንያቱም ሹፌራችን የሚል ስላነበብኩ፡፡ በተረፈ ይህ ብሎግ ታዋቂ እንዲሆን ሊንኮቹን ለወዳጅ ዘመድ አጋራቸው፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን ጽሑፎችህንም በፎቶ አሸብርቃቸው፡፡ ምክንያቱም ፎቶው ሰው ስለሚስብ ነው፡፡ የጽሑፍ ችሎታህ ተዳፍኖ እንዳይቀር በብሎግ መምጣትህ ትልቅ ነገር ስለሆነ በዚሁ ቀጥልበት፡፡ የፌስቡኮቹንም ወደዚህ ብታመጣቸው ጥሩ መሰነጃ መንገድ ይሆንልሃል፡፡

    ReplyDelete

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...