Saturday, February 5, 2022

"Beauty of the commons"

 

በሚገርም አጋጣሚ ከተገናኙ ጥር 10/2012 ሰባተኛ ዓመታቸው ካለፈ ወደ ሶስት ወር ገዳማ ሆኖታል ዘንድሮ፡፡ ከሁለት አመት በፊት ሊጋቡ ወስነው ተፍ ተፍ ሲሉ ድንገት ስኮላርሺፕ አገኘና ወደ ቻይና አቀና፡፡ ሁኔታዎች እንደዚያ መሆናቸው በተፊሪም ሆነ በረቂቅ ዘንድ በተወሰነ መልኩ ቅሬታን ቢፈጥርም “እርሱዋ ሁለተኛ ዲግሪ እርሱ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ሆነው መጋባታቸው፤ ለበርካታ ሰዎች እርሷ እኮ ከእርሱ በላይ የተማረች ናት” የሚለውን አጉል አመለካካት አፍ ማስደፈኛ ስለሚሆናቸው ብዙም የተከፉም አልነበረም፡፡በረቂቅ  ታናሽ እህቷ ዘንድ ግን ይህ ጉዳይ ትልቅ አሉታዊ ተጽእኖ አለው፡፡ጓደኛ ይዛ ከቤተሰብ ለማስተዋወቅ የእርሷ የታላቁን ጉዳይን ብቻ ነበር የምትጠብቀው፡፡ አሁን ለሌላ ሁለተኛ አመት መራዘሙና ለታናሽ እህቷም ሌላ ችግር ይዞ መምጣቱን ስታስበው፤ እጅግ በሚጣፍጡና ልመናን ባዘሉ ቃላት አይን አይኗ እያየች “ሪ ዬ እባክሽ ፈጠን አድርጊው እኔ እኮ በቃ ማግባት እፈልጋለሁ ጓደኛዬም እንጋባ እያለ እያስጨነቀኝ ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ አልበላም አልጠጣም ብዬ አስከአሁን የለፋሁበትን የሴትነት ክብሬን/ ጎልዴን/ እንድሰጠው ይፈልጋል፤ እርሱ ደግሞ ሊሆን እንደማይችል አንችም ታውቂያለሽ” የሚለው ልመናዋ ትዝ አላትና የሆነ ነገር ውስጧ ገባ፡፡በቃ እንግዴህ  ምንም ማድረግ አልችልም፡ በዚህ አመት ላገባ እንደሆነ  ብስራት ልነግራት ስሰናዳ ይህ መጣ፤ የሚያስደስት ግን ደግሞ የሚያሳዝን፤ ግራ የሚያጋባ፤ ምን አይነት ነገር ነው አለችና ውስነገር ገብቶት ለደቂቃዎች ያክል አንድ ቦታ ፍዝዝ ብላ ቆመች፡፡ ወዲያው ደግሞ ግን ሁሉም ነገር ለበጎ ማለት ነው ፡አምላክ የፈቀደው ይሁን፤ምን ይደረጋል አለችና ራስዋን በራስዋ አጽናንታ በተፈሪ ልቦና ውስጥም የባሰ ገር እንዳይገባ አግኝታው ሊወያዩ ልትደውልለት ስልኳን አወጣች፡፡

ረቂቅና ተፈሪ የተዋወቁት ከሰባት አመት በፊት በአንድ የጥምቀት በዓል ላይ ነው፡፡ እርሱ ቅዱስ ማርቆስ ሰ/ትቤት ዘማሪ እርሷ ደግሞ የቀጨኔ መድኃኔ አለም ዘማሪ ሆነው የየአጥቢያቸውን ታቦታት አጅበው ጃንሜዳ የከተራው ዕለት መጥተዋል፡፡ ታቦታቱን ካስገቡ በኋላ ሁለቱም ሰ/ትቤቶች ዘማሪያኑን ነገ የሚገናኙበትን ሰኣት ለአባላቶቻቸው አሳውቀው የከተራው ፕሮግራም ያበቃ ቢሆንም፤ ረቂቅ ግን ሁሌም እንደተለመደው ከወላጅ አባቷ፤ጋር የምታድረው ጃን ሜዳ ነው፡፡ አባቷ አቶ ዝናው ”እንዴ ታቦት ከመቅደሱ ወጥቶ ሜዳ እያደረ እኔ  ቤቴ አድራለሁ፡” የሚፈልግ ልጅ ከእኔ ጋር መሄድ ይችላል፤ ”አንች ግን ስለሚያምሽ ከቤት እደሪ አምላክ ያውቃል” እያሉ ብዙም ጤነኛ ያልሆኑትን የትዳር አጋራቸውን ቤት እንዲቆዩ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ እና በሌላው ባህሪያቸው ከልጆቻቸው ሁሉ አብልጣ የምትወዳቸው ረቂቅ፡በየአመቱ ከአባቱዋ ጋር አዳርዋ ጃንሜዳ ነው፡፡ ብርዱ አጥንት ዘልቆ ውስጥ ድረስ ቢሰማም እርሷ ግን ምንም ሳይበግራት ለበርካታ አመታት ጃን ሜዳ አድራለች፡፡ አባትዋ አብዛኛውን የሌሊቱን ክፍል የተለያዩ የጸሎት፡መጻህፍትን ሲደግሙ፤ አንዳንዴም ከቀሳውስቱ ጋር አምላካቸውን ሲያመሰግኑያድራሉ፡፡አብራቸው የሄደችውን ልጃቸው ረቂቅን፡ ”ልጄ እንደሚመችሽ ሁኝ ጸሎትሽን ከጨረስሽ፤ከሚዘምሩት ጋር ዘምሪ ካልሆነም እዚሁ አጠገቤ ተኝ ”ይሏትና እርሳቸው ወደ ግል ጸሎታቸው ይገባሉ፡፡ ረቂቅም እንደሚመቻት ልቦናዋ ወደ ፈቀደው ትሆንና እንቅልፍ ሲጥላታ አባቷ አጠገብ ትተኛለች፡፡ ልክ እንደሁሌውም ከሰባት አመት በፊት ሰብሰብ ብለው ወደሚዘምሩ ወጣቶች ጋር ሄዳ መዘመር እንደጀመረች አጠገባቸው ያለው መብራት ሲጠፋ ወጣቶቹ እርስ በርሳቸው፤ ሲገፋፉ አንዱ በአንዱ ላይ ወዳደቀና ጥቂት ልጆች ተጎዱ ከእነዚህ አንዷ ረቂቅ ነበረች፡፡ በዚያ በጨለማ ማን እንደወደቀ ማን እንደተጎዳ ብዙም ሳይታወቅ መብራቱ ወዲያው መጣ ረቂቅ ግን ከወደቀችበት መነሳት አቅቷት ስትንፏቀቅ አንድ ወጣት አይቷት ወደ እርሷ ተጠግቶ ምነው እህቴ ምንሆንሽ?ረገጡሽ እንዴ? አለና ጠየቃት እንቧዋ መንታ መንታ ሆኖ እየወረደ ወገቧን እንደተጎዳችና መነሳት እንዳቃታት አባትዋን እንዲጠራላት በተማጽኖ ለመነችው፡፡ አንጀቱ ስፍስፍ ያለው ወጣት “አይዞሽ” ብሎ ቀስ ብሎ አነሳትና ወደ አንድ ጥግ ወስዶ ቀስ እያለ ሁለመናዋን እያሻሸ፤ በተወሰነ መልኩ ህመሙዋን፤ቀነስ እንዲሊላት በኋላ እንደምንም ብላ ተነስታ ቆመች፡፡ ልትራመድ ስትሞክር፡ አልቻለችም፡፡ወጣቱን ደግፎ አባቷ፤ዘንድ እንዲያደርሳት፡ለመነችውና ወደ አባቷ ዘንድ እየወሰዳት እያለ በዚህ መልኩ አባትዋ ቢያዩዋት ሊደነግጡ ስለሚችሉ ”ቆይ ትንሽ አሳርፈኝና እራሴ ልሞክር” አለችው፡፡ እንዳረፈችም፤እግሯን ጀርባዋን ትከሻን እያሸላት ህመምዋ እየተሻላት ስለሄደ ተነስታ መራመድ ቻለች፡፡ ህመሙ ግን አልለቀቃትም፡፡ ወደ አባቷ እየቀረበች ስትሄድ ያንን መልካም ወጣት ”በቃ ፋዘር ያው ደርሻለሁ እመብርሃን ትስጥልኝ ውለታህን ለመክፈል ያብቃኝ አንተ ባትደርስልኝ እኮ ማንም ዞር ብሎ አያየኝም ነበር፡ረቂቅ እባላለሁ የቀጨኔ መድኃኔ አለም ሰ/ትቤት አገልጋይ ነኝ አንተን ማን ልበል” አለችው ተፈሪ እባላለሁ እኔም የቅዱስ ማርቆስ ሰ/ት/ቤት አባልና አገልጋይ ነኝ ሲላት እንደገና በፍጹም ወንድማዊ ሰላምታ እቅፍ አድርጋ ትከውን ሳመችው እርሱም እንደዚያው፡፡ ”ወይ ለካ ሁለታችንም የአንድ ቤት ልጆች ነን ማለት ነው” ብላ እና ”ነገ አታገለግልም እንዴ ?” አለችው ”አረ አገለግላሁ ዛሬም እኮ ታቦት አስገብተን ወደ ቤት ከሄድን በኋላ እኔ እዚህ ለማደር ስለት ስላለብኝ መጣሁ እንጂ” አላት፡፡ አንችስ ?እኔም እንደዚያው ነው፤በየአመቱ ታቦታቱ ወደ የማረፊያቸው ከገቡ በኋላ ከአባቴ ጋር እዚሁ፤ነውየማድረው አለችውና ልክ ረጂም ጊዜ እንደሚተዋወቅ ሰው ወሬያቸውን ቀጠሉ፡፡ ወይ “ከሰው ጋር ካልሆንክ፤ ለምን ፋዘር ጋር ሄደን እዚያ ቁጭ ብለን ወይ እናወራለን ካልሆነም እንዘምራለን” አለችው፡፡ ፈቃደኛ ሆኖ ሰው ሳይረግጡ ቀስ እያሉ አለፍና አቶ ዝናው አጠገብ ደርሰው ቁጭ አሉ፡፡ ልጃቸው ከሌላ ሰው ጋር መምጣትዋን ያወቁት አቶ ዝናው ምንም ሳይመስላቸው ቦታ እንዲበቃቸው እርሳቸው ወደ ጫፍ ወጥተው ለሁለቱ ምንጣፍን እንዲጠቀሙ አደረጉ፡፡ ረቂቅና ተፈሪም ስለየሰ/ትቤቶቻቸው አገልግሎት፤ ስለአባላት ጥንካሬና ድክመት ስለወቅታዊ የቤተክርስቲያን ፈተናዎች ሲወያዩ ረጂም ሰኣት ቆዩ፡፡ በመካከል አቶ ዝናው ”ልጄ ነገ ዘማሪ አይደለሽ እንቅልፍ ይጥልሻል ትንሽ አረፍ አትይም” ሲሉዋት እሺ አባዬ እርሱም እኮ ዘማሪ ነው አለችና ያለምንም ህፍረት ስለተፈሪ ነገረቻቸው፡፡ አሰይ ”ጎበዝ በጉብዝና ወራት ፈጣሪ ማመስገን ለዚው በዝማሬ እጅግ ድንቅ ነው በርታ ልጄ” በሉ አረፍ በሉ ይበቃችኃል አይደል አሉ፡፡ ተፈሪ እፍረት እየተሰማው ”አረ ይበቃል”፤ እሺ እናርፋለን ሲል አቶ ዝናው ከያዙት ትርፍ ልብስ አንዱን ጋቢ ለተፈሪ ሰጥተው አንች እርሱን ልበሽ አሉዋት ወደ ብርድ ልብሱ እያሰዩዋት፡፡ ሁለቱ ወጣቶች ንግግራቸውን በዚሁ ገታ አድርገው ሰላም ለኪ እንኳ ብለን እንረፍ አለና ተፈሪ በለሆሳስ ለራሱ ሲጸልይ ረቂቅም በግልዋ ጸልያ አረፍ አሉ፡፡

 

ጥምቀት ባለፈ በሳምንቱ ረቂቅ ከመነን በጉልት በኩል አድርጎ ወደ ቀጨኔ አቅጣጫ በግምት ወደ ግማሽ ኪሎ ሜትር፤ ያክል ከተጓዙ በኃላ በስተግራ በኩል ታጥፎ ወደ ውስጥ ትንሽ ገባ ብሎ ከሚገኘው የወላጆችዋ መኖሪያ ቤት አባትዋ በቅርቡ ለጥምቀት የገዙላትን የሀገር ልብስ ለብሳ እምር ድምቅ ብላ፤ አመታዊውን የስባረ አጽሙ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ለማክበር በእግረኛ መንገድ ወደ አስፋልቱ እየወጣች ነው፡፡ ዕለቱ ቅዳሜ ሰዓቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ከአጥቢዋ ውጭ ላሉ በዓላት ለአገልግሎት ስለማትመደብ በእነዚህ በዓላት ዕለት ብቻዋን ሆኖ በተረጋጋ መንፈስ በዓሉን ማክበር በጣም ትወዳለች፡፡ ከቤተሰብም ጋር እንኳ በአጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር አብራ አትወጣም፡፡ በተለይም ከእህቷ ጋር ከሆነ ደከመኝ ልቀመጥ ራበኝ የሆነ ነገር እንግዛና እንብላ: አየሽ :አየሻት: አታምርም: አያምርም የሚለው ንዝንዟ ስለማይመቻት ከልቧ የምትወዳትን እህቷን እንኳ ቢሆን በእነዚህ ቀናት ማስከተል አትወድም፡፡ አጋጣሚ ሆኖ በቅርብ የሰፈርዋ ልጅ የሆነ ከእርሷ ጋር ሰ/ት/ቤት አገልጋይ ስለሌለ ብቻዋን እንድትሆን እርሷም፡ ሁኔታዎችም የፈቀዱላት ይመስላል፡፡ ትንሽ ራመድ እንዳለች: የያዘችያት ስልክ፤ ያክብርዋ ለሰንበት መላዕክት እያለች በመዝሙር ዜማ የጥሪ ድምጽ አሰማች፡፡ስትመለከተው የተፈሪ ጥሪ ነበር፡፡ ባለፈው የጥምቀት ዕለት ለመጨረሻ ሲለያዩ ስልክ ከተለዋወጡ ወዲህ ተደዋውለው አያውቁም፡፡ ዛሬ እርሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደውል፡፡

ስሙን በስልኳ ላይ ስታየው ፈገግ እያለች “ወይ አንተ ልትጠይቀኝ ነው እንዴ የደወልከው ምንው ግን አንደዚህ አስቸኮለህ ግን ደህና ነህ” አለችው ፍጹም ወንድማዊ በሆነ ፍቅር፡፡ ተፈሪ፤ድምፅዋን፤ እንደሰማ የሆነ ነገር ውስጡ ድው ድው አለበት በዚያ ላይ ደግሞ በወቀሳ መጀመርዋ ውስጡ ራደበት፤ ወይኔ አለና የጸጸት ስሜት ተሰምቶት ዝም አለ፡፡ “ሄሎ” አለች ረቂቅ ዝም ሲልባት “ሄሌ” እየሰማሁ ነው አላት፡፡

“ምን መሰለሽ ረቂቅ ስላልደወልኩልሽ ይቅርታ፡ ግን አንድ ቀን ስልክሽን ስሞክር ዝግ ነበር ከዚያ በኋላ አልሞከርኩም፤አጥፋቻለሁ፡ይቅር በይኝ አላት፡፡” “አረ ለቀልድ ነው፤ ተሸሎኛል፡፡ በርግጥ ስልኬን ብዙም አልከፍተውም፡ ስፈልግ፤የረፍትና በዓል ጊዜ ካልሆነ በስተቀር አለችው፡፡” “ነው እንዴ እና ስልክሽን ዘግተሸ እኔን ትወቅሻለችሽ እንዴ ባይገርምሽ በጣም ብዙ ሞከሪያለሁ በተለያየ ስልክ” አለናወይ ይቅር በለኝ፡፡ “አንች ወደ ቤተክርስቲያን እየሄድኩም ታስዋሽኛለሽ” አላት፡፡ ውይ “የትነው እየሄድክ ያለው እኔም እኮ ወደ ጊዮርጊስ እየሄድኩ ነው አለችው፡፡ “አራዳ ጊዮርጊስ ነው” አላት አዎ እኔም ወደ እዚያ ነው፤ አሁን በቃ ልደርስ ነው አዲስ አበባ ሬስቶራንትን አልፌ ታክሲ ተራ ጋር ደርሻለሁ፡፡ በቃ እንደገባሽ የመጀመሪያው ግቢ ወደ  በስተግራ በኩል፤ጥግ ላይ እጠብቅሻለሁ እንገናኝ አላት፡፡ እሺ ተፌ ታክሲ ያለ አይመስልም ከአፍንጮ በር በእግሬ ስለሚሆን ትንሽ እቆያለሁ፡፡ ወይ መኪና አልያዝሽም እንዴ፤ መጥቼ ልውሰድሽ አላት ለቀልድ ያክል አዎ በናትህ መኪናዬ ጋራዥ ገብታ ዛሬ ከሰዓት ነው የምትወጣው፤ እኔ ደግሞ የሰው መኪና ስማይመቸኝ፤ እንጂ ብትወስደኝ አሪፍ ነበር፡፡ ግን በጣም አመሰግናለሁ አለችው እርሷም በተራዋ፤ በቀልድ ሁለቱም ፍርፍር ብለው ሳቁና በይ እሺ ስልኩን፡ዝጊው ትራፊክ አየኝ እንዳይቀጣኝ እየነዳሁ ስልክ ሳወራ፡ሲላት፡ ወይ ወደታችም እያየህ የጉልትዋን ሴትዮ፤ ዕቃ እንዳትረግጥባቸው፡ አለችውና እየሳቀች ስልኳን ዘጋች፡፡ከስልክ ልውውጣቸው በኃላም ተፈሪ ብቻውን በሳቅ ፈረሰ፡፡

የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፡ በርካታ ገድላትን ከፈጸመ በኋላ የሀገሩ ሰዎች ለጣኦታቸው አልሰግድም ስላላቸው ገድለው ካቃጠሉት በኋላ አመዱን በደብረ ይድራስ ተራራ ላይ ያዘሩበትና ታላቁ ሰማዕት ከፈጣሪው የክብር አክሊል ለማግኘት ታላቅ ተጋድሎን የፈጸመበት  በዓል እጅግ በደመቀ ሁኔታ ታቦቱ በሚገኝበት በመላው ኢትዪጲያ ጥር 18 ቀን ስባረ አጽሙ ተብሎ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ረቂቅና ተፈሪም፡ታቦቱን አክብረው ፡ታቦቱ ወደ መቅደሱ ገብቶ ታቦት በውስቴታ የሚለውን የመጨረሻ መዝሙር ከዘመሩ በኃላ፤የማትቸኩይ ከሆነ ሻይ ቡና ብንልስ አላት ተፈሪ፡፡ እቸኩል ነበር ግን ሰው ማስቀየም ስለማልፈልግ እሺ አለችው፡፡ ተፈሪ ከልቡ ሳቀ ምነው ምን ያስቅሃል ስትለው አረ ባክሽ፡ አለና ያዝ አደረጋት፡፡ አይ የሰ/ት/ቤት ተማሪዎች ባህሪ በበዙ መልኩ መቀራረቡ ነው፡ የኛም ሰ/ትቤት፡ልጆች እንደዚህ ስትያቸው ወይ በጣም ብዙ ስራ አለብኝ ግን መታዘዝ ደግሞ ብለው፡ በነካ ይሉሻ፡፡ ለቀልድ አፍሽ አምልጦሽ ያወራሽውን ሻይ ቡና እንበል እውነት አድርገው መጋበዝ ይሞክራሉ፡፡ እና ያንን ባህሪ ቀጨኔም ማየቴ ገርሞኝ ነው አላት፡፡ ረቂቅ ሲበዛ ነጻ ናት፡፡ እንዴ ልክ ነዋ መታዘዝ ለዚያው የሰ/ት/ቤት ወንድም ሲጠይቅ እንቢ አይባልም አለችው፡ ጋብቻ እኮ አይደለም፤ ሲላት አንተ ሞዛዛ ብላ ቁንጥጥ አረገችው፡፡ ቆይ እሺ እንደዚህ ነው እኔ ሞቻለሁ ለሰ/ትቤት አመራሮችህ ባልናገር ስትል ስልኩን ጎርጎር አድርጎ ይኸው ስልኩ አላት ግራ፡ገባት የማን ስትለው፤የግብረገብ ክፍል ኃላፊ ንገሪው ብዬ ነው ሲላት ቁጭ ብላ እንባዋን እኪፈስ በሳቅ ፍርፍር አለች፡፡አንተ ምን ዓይነት አድክም ነክ በዚህ አይነት በሳቅ ስለምትገልኝ ሻይ ቡናው ይቅርብኝ አለችው፡፡ ይሻላል እሺ ይቅር ሲላት አይ ባይሆን እኔ እጋብዝሃለሁ፡ እንጂ እርሱማ አይቀርም አለችው፡ የያዘችውን መቶ ብር እያሳየችው፡፡ በድንጋጤ በሚመስል ስሜት  ብሩን እያየ አንች፤ይኸ ነገር ሰላም ነው በዚህ እድሜሽ እንዴት እሺ አለና አንች ጋር ተቀመጠ፤ ትተዋወቃላችሁ ወይስ እንግዳ ነው አላት ደንገጥ ብላ ምኑ፡ስትለው ቮልት ነዋ አላት፡፡ እ ወዲዚህ ስመጣ ሲኖሮጥ ድንገት ተገናኘኝና እባክሽ ቤተክርስቲያን አሳልሚኝ ሲለኝ ነው ይዤው የመጣሁት፡፡ አንዳንዴ በሩቅ አየዋለሁ፡እንጂ ብዙ ትውውቅ የለንም፡ እያለችው ግቢው ለቀው ወጡና ቁልቁል ወደ ፒያሳ ወርደው ሲኒማ አምፒር አጠገብ ካለ አንድ ኬክ ቤት ገቡ፡፡ ሻይ ከሚበሉት ኬክ ጋር አዘዙና ተፈሪ አጠር ያለጸሎት አድርጎ መጠቀም ጀመሩ፡፡ የባጥ የቆጡን እያወሩ ከቆዩ በኃላ ፡ረቂቅ በዚህ አመት 12ኛክፍል እንደምትፈተን፤ተፈሪ ደግሞ በተግባረዕድ ኮሌጂ የ2ኛ ዓመት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ተማሪ እንደሆነና ከወላጂ እናቱ እና ከአንዲት እህቱ ጋር ስድስት ኪሎ ከገነዘብ ሚኒስቴር ጀርባ ከሚገኘው የቀበሌ ቤት ውስጥ እንደሚኖር ነገራት፡፡ በተፈሪና በረቂቅ መካከል ምንም አይነት እፍረትና ይሉኝታ ሳይኖር በነጻነት ሁሉን ተጫወቱ፡፡ እንደዚህ በነጻናት እንዲያወሩ፤ ነጻም ሆነው ያለፍረሃት ሃሳባቸውን እንዲገልጹ፤ያደረጋቸው፤ በሰ/ትቤት የሚሰጠው ጾታዊ ትምህርት ነው፡፡ ይህ ትምህርት የብዙ ወጣቶችን ችግር የፈታ ለበርካታ፤መንፈሳዊ ጋብቻዎች፤እህታዊና ወንድማዊ ግንኑነቶች መሰረት የጣለና በወንድሞችና በእህቶች መካከል በምክንያት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖርና እንዲፈጠር ትልቅ ምክንያት ነው፡፡ ይህ በቤተክርስቲያን፡አጋጣሚ፤በሚመስል ነገር መገናኘታቸው፡ የበለጠ ትውውቅን ፈጠረላቸው፡፡ አንዳንዴ ተፈሪ እንኳን የዚን ዕለት ወደቀችና ተጎዳች ያ ባይሆን እኮ መቼም ልንተዋወቅ አንችልም፡፡ የፈጣሪ ስራ አኮ ድንቅ ነው፤ይላል፡፡

ረቂቅና ተፈሪ እየተደዋወሉ በተወሰነም ቀን በአካል እየተገናኙ፤ወክ እያደረጉ ግንኑነታቸው ከፍ እያለ መሄድ ከጀመረ ስድስት ወራት እያለፉት ነው፡፡ በተለይ ረቂቅ የ12ኛ ክፍል ፈተናዋን ከተፈተነች በኃላ ጊዜ ስላላት ሁለቱ ወጣቶች አዘውትረው ይገናኛሉ፡፡ አንድ ቀን አመሻሹ ላይ፡ድባብ መናፈሻ ቁጭ ብለው ሳለ ድንገት ረቂቅ ሳታስበው፤  እስኪ ስለወደፊትሽ ንገሪኝ አላት፡ ተፈሪ የሆነ ድንብር ብር ስትል ታየው፡ ማለት አለችው፡ ግራ እንደተጋባች አይኑዋን ከእርሱ እያሸሸች፡ ማለትማ ምን መሆን ትፈልጋለሽ፤ ወደ ጋብቻስ፤የመግባት እቅድሽ እንዴት ነው፡ ጓደኛ እንደሌላት ቢያወቅም እርግጠኛ መሆን ስለፈለገ እርሱን ጭምር ጠየቃት፡፡ ተፌ አለችው ፊቷን ወደ እርሱ መልሳ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ አስቤበት አላውቅም፤ ያው ውጤት ከመጣልኝ ዩነቨርሰቲ እገባለሁ፤ ከተወሰነ አመት በኃላ ደግሞ ማግባቴ አይቀርም፡፡ ሰ/ትቤት ያስተማረችን ህይወታችን ግልጽነትን፡አይደል፡፡ ወይ ታገባለህ ወይ ትመነኩሳለህ፡፡ እንደምታውቀው ደግሞ መመንኮስ ለተፈቀደላቸው እንጂ ለእኛ አይናችን የፈለገውን ለሚያየው ጆሮዋችን የፈለገውን ለሚሰማው፤ልቦናችንም በሃጢያት ለሚጋልበው ምንኩስና ቅድስና ስለሆነ አይፈቀደልንም፡፡ እና የረከሰው ጋብቻ ብቻ ነው የሚፈቀድልን ማለት ነው ሲላት አይደለም፤ ጋብቻ እርኩስ ነው ማለቴ አይደለም ጋባቻ ቅዱስ ነው፡ ቅዱሳን እኮ የቅዱስ ጋብቻ ውጤቶች ናቸው፡፡ ልል የፈለግሁት ምንኩስና ፈተናና ጾሩ ብዙ ነው ለማለት፡ነው፡፡

ከአፏ ቀበል አለና ተፈሪ በርግጥ ልክ ነሽ፤ለእንደኔና አንች አይነት ወጣት ምንኩስናና ማሰብ ከባድ ነው፡፡ የምናው የምንሰማው የምንማረው ሁሉ በአለም ተወስነን እንድንኖር እንጂ የከበረውን ምንኩና እንድናስብ አይደለም፡፡ አንድ ሰው አልመነኮሰም ማለት ግን ህገ እግዚአብሔርን አላከበረም ማለት አይደለም፡፡ ራሱን አርሞ ትክክለኛ የግራ አጥንቱን አግኝቶ በትዳር ተወስኖ መኖርም ትልቅ ሃላፊነት ያለበት ቅድስና ህይወት ነው፡፡ እኔ አንዳንዴ ሳስበው በዓለም ውስጥ እየኖሩ ከአለም ግብር ተለይቶ መንፈሳዊነትን ጠብቆ መኖር በራሱ ትልቅ ሰማዕትነት ስለሆነ ክብሩ ከምንኩስና ይበልጥብኛል፤ ግን ሁሉም ለሚቻለው ቅድስና ስለሆነ በአምላክ ስራ አልገባም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም እኮ ያለው ቢቻላችሁስ እንደ እኔ ሁኑ ካልሆነ ግን አንድ ወንድ አንዲት ሴት ትኑረው አይደል ያለው አለና ክንዶቿ አካባቢ አሸት አደረጋት፡፡ ረቂቅ የሆነ ፈዘዝ የማለትና የመደናገጥ ስሜት አሳየች፡፡ ተፈሪ በውስጡ ነጥብ ያስቆጠረ ስለመሰለው ከዚህ ጨዋታ ሳይወጡ እንዲቀጥሉበት ፈልጓል፡፡

ትምህርት ምን ማጥናት ነው የምትፈልጊው መቼም የሀገራችን፤ትምህርት፤የምንፈልገውን እንድንማር ባይፈቅድም፡አለና መለስ ብላ ሰስታየው ማብራሪያ ቀጠለ ህክምና ለማጥናት ትልቅ ተስፋ ውስጡ ያለውን ወጣት ግብርና እንዲያጠና፤ ምህንድስና ለማጥናት የሚቋምጠውን ኦኮኖሚክስ፡ አካውንታት ለማጥናት አቅዶ ህግ እንዲማር እያደረገ ፍላጎትና ትምህርት ሳይገኛኙ ይቀሩና፤ ተማሪው ከተመረቀ በኋላ ስራውን በፍቅር እንዳይሰራ ስልቹ እንዲሆን የሚፈልገውን ትምህርት እንደገና ከፍሎ እንዲማር ያደርገዋል፡፡ የአኔ አይነት እድለ ቢሱንም ውጤቱን ቆምጦ ይጥልና እንዳይነሳ ያደርገዋል አላት በምሬት፡፡ አዎ ልክ ነህ ግን አንተ እንዴት ዩኒቨርስቲ አልገባህም አለችው፡፡ እኔም አላውቅ ሰነፍ ነበርኩ እንዳልልሽ ከእኔ የኮረጁት እኔ የማስረዳቸው፤ከእኔ የሚያንሱት ዩኒቨርስቲ ገብተዋል፡፡በኋላ ግን ቀስ ብዬ እንደተረዳሁት ገንዘብ ሚኒስቴር ከጀርባችን ስለሆነ ሌሊት ሳጠና መብራቱ ዘበኛውን እንዳይተኛ ስለረበሸው እርሱ ከሶኝ ነው ነጥቤ የተቆረጠው አሉ፡፡ ከዚህ ውጭም ምንም ምክንያት፤አላገኘሁም አላት፡፡ ረቂቅ ፍርሃት ገብቶበት ከነበረው ኃሳብዋ ነቃ ብላ መሳቅ ጀመረች፡፡ አይዞህ እኔም ከሁለት ወር በኋላ ቁርጤን አውቃለሁ፡፡ ደግ፤ ቤተሰብህ አጠገብ ሆነህ አሪፍ የትምህርት መስክ አይደል እያጠናህ ያለኸው አለችው፡፡ እርሱስ አረፊ ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርን ልታዘበው ብየ እንጂ እኔ እንደሁ ከአዲስ አበባ ውጭ ቢልኩኝ አልሄዳትም ነበር፡፡ለምን ስትለው አረ ባክሽን ክልላዊ አስተሳሰብ እያራመደ፤ስለክልሉ እያወራ እንዴት ነው ዩኒቨርሳል የሆነ እውቀት የሚሰጠኝ፡ ብዙዎቹ መ/ራን ከእድሜ ከእኔ ያልበለጡ ሱሪያቸውን ከመቀመጫቸው ዝቅ አድረገው የውስጡ ሱሪያቸውን እያሳዩ  የሚለብሱ ጸጉራቸውን ክፍል ውስጥ ሳይቀር የሚጎነጉኑ ምን ጥሩ ነገር አገኛለሁ ብዬ ከእናቴ ተለይቼ፡ እርሷን፤ለወጭና ለጭንቀትስ የምዳርጋት፤ እዚሁ አዱ ገነቴ ትሻለኛለች አላት፡፡ እርሱማ ልክ ነህ የሚገርምህ እኔም ውጤት ቢመጣልኝኛ ከአዲስ አበባ ውጭ ቢደርሰኝ እቀይራለሁ ካልሆነም አቋርጣለሁ እንጂ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከፍለሀገር ሄጄ አልማርም፡፡ ምናልባት አዋሳ፤ ደብረብርሃን ካልሆነ አላደርገውም አለች፡፡አይ አንች እንኳን ከአዲስ አበባ ውጭ አትሄጅም አላት፤ በምን አወቅህ ወይ አምላኬ ባደረገው አለች፡፡ እንዴ ትምህርት ሚኒስቴር በእኔ ላይ ሁለተኛ በደል እማ አያደርስብኝም፡፡ እኔ ነጥብ ከለከለኝ ውሃ አጣጭዬን ደግሞ ከእኔ ያርቃት እንዴ ሲል እንዳልሰማ ሆና ዝም አለችው፡፡ በጉዳዩ ላይ እንዲቀጥል የሚገፋፋ ነገር ስላጣ፤ቆፍጠን ብሎ በግልጽ መናገር ጀመረ፡፡

ረቂቅ አላት ኮስተር እያለ ላለፉት ስድስት፤ወራት እኛ በማናውቀው አምላክ ግን ባወቀው በአጋጣሚ ተገናኝተን፡ብዙ ነገራችንን በግልጽ አውርተን ተዋውቀናል፡፡ ደጋግሜ አምላኬን በጸሎትም ጭምር ጠይቄዋለሁ፡ውስጤም ፍጹም ደስተኛ ነው፡ እና ፈቃድሽ ከሆነ ወደፊት ዘመናችንን በአምላክ ፈቃድ በአንድ ጎጆ ውስጥ እንድንኖር የእኔ ፈቃድ ነው፡፡ይህንን አይነት ጥያቄ ፈተናሽን ከመፈተንሽ በፊት አንስቼ ውስጥሽን መረበሽ ስላልፈለግሁ አልጠየቅሁሽም፡፡ ጥያቄዬም ድንገት የመጣ ሳይሆን ብዙ አውጥቼ አውርጄ ጊዜ ወስጄ የወሰንኩት ነው፡፡ አሁን በዚህ ሰዓት ከአንች እሺ ወይንም እንቢ የሚለውን መልስ መስማት አልፈልግም ጊዜ ወስደሽ አስቢበትና ውሳኔሽን አሳውቂኝ፡ ውሳኔሽ በፍጹም ቅንነትና መንፈሳዊነት ላይ መሰረት ተደርጎ ከተወሰነ ለውሳኔሽ ተገዥ ሆኜ በፍጹም ወንድምነትና እህትነት ግንኙነታችን ይቀጥላል፡ አለና የውስጡን ፡ሁሉ፡ዝርግፍ አድርጎ ተገላገለ፡፡ ማለት ስትል ኖኖ አሁን ምንም ማለት አይጠበቅብሽም፤አትገደጂምም አላት፡፡ አውቃለሁ ግን በዚህ ወቅት ሆነን የምንወስናቸው ውሳኔዎች የልጅነት፤ሆነው ኃላ ዋጋ እንዳንከፍልባቸው፤ አምላካችንንም እንዳናሳዝንባቸው ብዬ እንጂ መልስ ልሰጥህ ፈልጌ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሳላመሰግንህ የማላልፈው፤ ውስጤን ተረድተህ ከትምህርቴ ጋር ጫና እንዳይፈጠርብኝ አስበህ፤ እስከአሁን ድረስ ፍጹም በሆነ እህትነትና ወንድምነት ስለቀረብከኝ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡ ምንም እንኳ ሰ/ትቤቴም ሆነ ቤተሰቦቼ ከማንም ጋር እንዳልገናኛኝ ገደብ ባይጥሉብኝ እኔ በደንብ ቀርቤ የማውቀው ወንድ አንተ ብቻ ነህ፡፡ግን ሳውቅህ መልካም ወንድምነትህን፤እንደታላቅ ወንድም ምክሮችህንና ቀልዶችህን እንጂ እንደ ሌላ ወንድ አስቤህ አላውቅም ብዬ ልዋሽህ አልፈልግም፡፡ አልፎ አልፎ የሆነ ስሜት ሲሰማኝ እራሴን እወቅስና አከስ ነበር፡፡ምንም እንኳ ግልጽ መሆን በሁሉ ተገቢ ቢሆንም ያደግንበት ባህልና ሴትነት በውስጤ ስላለ ይህንን ስሜቴን ነግሬህ አላውቅም፡፡ አሁን ያ የሚሰማኝ ስሜት እውነት ነው ወይስ መልካም ያልሆነ መንፈስ ነው የሚለውን ልረዳ፤አምላኬንም ላማክረውና መልሴን አነግርሃለሁ፡፡ ግን ደስ የሚለው በሁለቱም መልሶቼ አንተ ከእኔ አትርቅም፡፡ አየህ ምንም እንኳ አንድ ወንድም ቢኖረኝም እርሱ በትዳር ስለተወሰነ ጊዜውን ሰጥቶ አብረን ብዙ ጊዚ አናሳልፍ፤በዚህም የተነሳ የወንድም ጣዕሙና ፍቅሩን በብዙ አላውቀውም፡፡ ስለዚህ አንተን በወንድምነት ማግኘት እጅግ መልካም ነው፡፡

ነሐሴ 13/2004 ዓ.ም፤ ጌታ ምስጢረ መለኮቱን ለዓለም የገለጠበት ዕለትና ቤተክርሰቲያን የጌታ አበይት በዓላት ብላ ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ ነው፡፡ ረቂቅ በጠዋት ቤተክርስቲያን ደርሳ፤ ውጤት ዛሬ ይገለጻል ስተባለች ወደ ት/ቤቷ ምስኪሃዙናን፤ት/ቤት ትሄዳለች፡፡ሌሊቱ አልነጋ ብሏት ስትገላበጥ ነው ያደረችው፡፡ ተፈሪም በጠዋት ቤተክርስቲየን እናቱን ይዞ በመሄድ ለማስቀደስ ስላሰበ እራቱን በጊዜ በልቶ ተኝቷል፡፡ድንገት ሌሊት ከእንቅልፉ ብንን ብሎ ሰዓት ሲመለከት 9.05 ነው ሰዓቱ፡፡ ስልኩ ላይ አንድ አዲስ ሜሴጅ ገባ እና ሲያነበው፡፡ ተፌ ይቅርታበጊዜ ጀምሬ ስልክህን ስሞክረው እንቢ አለኝ፡ ነገ ውጤት ይገለጻል፡፡ውስጤ በጣም እየፈራነው፡ እባክህ ጸልይልኝ ይላል፡፡ የረቂቅ መልዕክት ነው፡፡ ወዲያውኑ ፈጠን ብሎ አይዞሽ አትጨነቂ አምላክ ያለው ይሆናል፤ ያንንም የሚያስችል ሃይል እርሱ ይሰጥሻል፡፡ ደግሞ እርግጠኛ ነኝ በቂ ውጤት ታመጫለሽ አለና ላከላት፡፡ ነቅታ ስለነበር ወዲያውኑ መልዕክቱን አንብባ አመሰግናለሁ እንደአፍህ ያደርገው አለችና ላከችለት፡፡ እንዴ ይህች ልጅ አልተኛችም ማለት ነው አለና፤ቢደውል ምንም ችግር እንደሌለው ስለሚያውቅ ደወለላት ወዲው አነሳቸው ይቅርታ እሺ እኔ እንቅልፍ አጥቼ እረብሽኩህ አይደል አለች፡ ከአጠገብዋ የተኛችውን እህቷን እንዳትቀሰቅሳት ድምጥዋን ቀንሳ አይ ችግር የለውም አንች ግን ምን ሆነሽነው አሁንም ምን ይመጣል ብለሽ ነው፡የምትጨነቂው ውጤቱ ይመጣል ግን የሚደርስሽ መዳወላቡ ዩኒቨርስቲ ስለሆነ ተዘጋጂ አላት፤ መዳወላቡ እርሱ ደግሞ የት ነው አለችው ስሙን እንኳ ሰምታ የማታውቀው ዩኒቨርስቲ ሲጠራላት፡፡ እዚህ ቅርቡ ነው በሻሸመኔ በኩል ሁለት ቀን በአውቶቡስ ተጎዙ የሚደረስበት አላት፡፡ አንተ ቆይ ቀልድ ሁለት ቀን በመኪና ተጉዞ ቅርብ ነው፤ ይባላል፡፡ ምንቸገረኝ እኔ እሄዳሁ አንተ ግን ብቻህን ስትለው አረ እኔ ስቀልድ ነው፤ በቀደም ቅዱስ ማርቆስ ተንበርክኬ ማመልከቻ አስገብቻለሁ፡አላት፡፡ ምን ብለህ ውሃ አጣጬን የትም አትውሰዳት እዚሁ ካጠገቤ ኮሜርስ መድባትና አብረን ጠዋትና ማታ እንድንሄድ አድርግ ብየዋለሁ፡፡ እመብርሃንንም፤ እማማ እንድትነግራት ነግሬያታለሁ፡፡ እንዴ ለእርሳቸው ደግሞ ምን ብለህ ነገርካቸው አለች ቆጣ ብላ፡፡ እንዴ ያው እውነቱን ነግሬነዋ አንድ የማልወዳት ልጅ አለች ውጤት መጥቶላት ከመነን ሜክኪኮ እንድትመላለስ ጸሎት አድርጊ ብየ አላት፡፡ ወይ ተፍዬ አንተን እኮ በዚያ በጥምቀት ምሽት የሰጠኝ አምላኬን ሁሌም ነው፡ የማመሰግነው፡፡ አለችውም፡፡ ግራ ተጋባና ዝም አለ፡፡ ተፌ አለችው ቀስ ብላ ዝም አላት ስልኩን አለመዘጋቱን ከጆሮዋ አንስታ አየች በኋላ በድንጋጤ ሳይስበው፤አቤት አቤት ሲል እናቱ ሰምተው አቤት ተፈሪ ጠራኸኝ ልነሳ ሰዓት፤ደረሰ አሉት አይ እማዬ ሰዓት ገና ነው አልደረሰም ትንሽ ይቀራል ተኝ አላቸው ድምጹ ለረቂቅም እንዲሰማ አድርጎ፡፡ ወይኔ ሰው ረበሽን አለች ቀስ ብላ፡፡ አይ ምንም አይደል ቤተክርስቲያን ለመሄድ ስለተነጋገርን ሰዓት የደረሰ መስሏት ነው ሲላት በል በል ቻው አመሰግናለሁ ይቅርታ ብላ ስልኩን ዘጋችው፡፡ ተፊሪ ወይ ተፍዬ አንተን እኮ በዚያ በጥምቀት ምሽት የሰጠኝ አምላኬን ሁሌም ነው፡ የማመሰግነው የምትለውን የረቂቅ ንግግር ደጋግማ ጆሮው ላይ ቅጭል ስትልበት እንቅልፍ በአይኑ ሳይዞር 11 ሠዓት ላይ እናቱን ይዞ ለቅዳሴ ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ ተነሳ፡፡ካህናቱ ኪዳን ሳይጀምሩ የእመቤታችንን ተዓምር ሲያኑቡ ደረሱና ወደ መቅደሱ ሁለቱም በራሳቸው መግቢያ በር፤ገብተው የቅዳሴውን፡በረከት ተካፍለው፤ ስርዎተ ህዝብ ሲደረግ ተፈሪ የቆረቡ እናቱን ይዞ ወደ ቤቱ አቀና፡፡

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የረቂቅ ውጤትም በጣም ጥሩ ሆኖ፤ ተፈሪ ሲመኝ እንደነበረውም ረቂቅ በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ የንግድ ስራ ትምህርትቤት ተመድባ በሰፕላይ ማኔጅመንት ትምህርት ከጀመረች ወደ አንድ ወር ገደማ ሆኖዋታል፡፡ በዚህ፡ወራት ጊዜያት ውስጥ ግን ከተፈሪ፤ጋር ለተወሰኑ ቀናት ተገናኝተው፤እዚያው ሜክሲኮ አካባቢ ምሳ ቢበሉም አብረው ግን መጥተውም ሆነ ሄደውም አያውቁም፡፡ ሰፊ ጊዜም ወስደው ተጫውተው አያውቁም፡፡ሁለቱም ግን ሁኔታዎች እንደሚያስቧቸው እንደዚህ በመሆናቸው እጅግ ደስተኞች ሆነው አምላካቸውን ከልብ አመስግነዋል፡፡

በህዳር ወር አንድ ቅዳሜ ቀን ጠዋት፤ረቂቅ ለተፈሪ ደውላ ተፍዬ ዛሬ የት ነው የምትውለው፤ አለችው ለጊዜው ምንም የተለየ ፕሮግራም የለኝም የሆነ አሳይመንት ስላለኝ እርሱን አሰራለሁ፤ ከዚያ፤ ውጭ የያዝኩት ፕሮግራም የለኝም አላት፡፡ እኔ ደግሞ ሰኞ የሚሰጥ የግል ስራ አለኝ ዩኒቨርስቲ ቤተመጻሀፍት እገባለሁ፤እዚሁ፤ስድስት ኪሎ ግቢ እስከምሳ ሰዓት ድረስ የምጨርስ ይመስለኛል፤ከዚያ በኋላ ግን ነጻ፤ነኝ፡፡ ትያትር ይዞኝ የሚገባ ሰው ባገኝ ደስይለኝ ነበር አለችው፡፡ ቲያትር ታዲያ ምን ችግር አለ ስፓንሰር ካገኘሁ እኔ አለሁ አይደል አላት፡፡ እውነት ተፌ፤ ማለት የቲያትሩን ከፍለሽ ተጨማሪ ክፍያ ከከፈልሽኝ ችግር የለውም አላት፡፡ ታድዬ ለክፍያውም ምንም ችግር የለውም የኪስ ገንዘብ ስለወጣ የፈለግከውን ያክል ይከፈልሃል አለችው፡፡ በብር ሳይሆን በዶላር አላት፤ ምንም ችግር የለም ላንተ እንኳን በዶላር ለምን በሌላም አይሆንም አለችና ልክ ስደስት ተኩል አካባቢ አንበሳ ግቢ በር ላይ ለመገናኘት ተቀጣጠሩ፡፡

በቀጠሮው መሰረት ከተገናኙ በኋላ ቁልቁል ወደ አራት ኪሎ እየወረዱ ግን አንች ቲያትር እንይ ስትይ ትንሽ አይከብድሽም ይኸ ሁላ ህዝብ በእውነተኛው መድረክ ላይ ሲተውን እያየሽ ቲያተር አላት፡፡ እንጃ በቃ አለ አይደል በጣም ስለተጠፋፋን አብረን እንሁን ጭምር ብዬ ነው አለችው፡፡ እና ቲያትር ቤት ነው እንዴ የምንሆነው ይልቅስ ምሳችንን እንብላና አንድ ሰጥ ያለ ቤተክርስቲያን ሄደን እንቀመጥ አላት ወይ አሪፍ ነበር ግን ነጠላ አልያዝኩም አለችው፡፡ ችግር የለም ቤተመቅደስ ከርቀት ተሳልመን አንድ ጥግ ቁጭ እንላለን አላትና ምሳቸውን በልተው በቅርብ ወደላችው የቤተመንግስቱ አጎራባች ቤተክርሰቲያን ወደ በዓታ ለማርያም፤ገዳም አቀኑ፡፡ የየግል ጸሎታቸውን አድርሰው ለምን ሙዚየም አንጎበኝም እኔ ህጻናት፤ክፍል እያለሁ ነው የጎበኘሁት ሲላት፤ እኔም ልጅ ሆኜ ሰ/ት/ቤታችን ባዘጋጀው ጉብኝት ነው የገበኘሁት አለችውና አንዴውም አሪፍ ሃሳብ ነው ያመጣኸው ብላ ሁለቱም ተነስተው ወደ ሙዚየሙ አቀኑ፡፡

ጉብኝታቸውን ጨርሰው ጥቂት እንደተቀመጡ ረቂቅ በአንድ ወቅት አንድ ጥያቄ ጠይቄሽ እስከአሁን መልሱን አልነገርሽም፡፡ በርግጥ ብዙም የተረጋጋ ጊዜ ስላልነበረሽ ነው ዝም ያልኩሽ አሁን ግን በቅድስት ቤተክርስቲያን ፊት ሆኜ ልጠይቅሽ መልስሽን ንገሪኝ አላት፡፡ ትንሽ ዝም አለችና ቀስ ብላ እጇን ጀርባው ላይ ጣል አደረገች፡፡ ተፈሪ የምትለውን ለመስማት ጓጉቶ ዝም ብሎ ይጠብቃታል፡፡ አሁንም ትንሽ ዝም አለችና ድምፅዋን ሳልሳል አድርጋ ተፈሪ በዚህ ጥያቄ ከሁሉም በላይ ደስተኛ የምሆነው አንተ ሳትሆን እኔ ነኝ፡፡ በዚህ ዘመን፤ እውነተኛ ሰውን አግኝቶ፤ማንነቱን አጣርቶ የትዳር አጋር ማድረግ እጅግ የሚያስደስት ነው፡፡እኔና አንተ ደግሞ ይህንን ነገር ሳናስብ በደንብ ተዋውቀናል፡፡ ማወቅ የሚገባኝን መረታዊ ነገሮች ያወቅሁ ይመስለኛል፡፡ ግን ስትል ከመቀመጫው ነቅነቅ አለ፡ግን አፍራሽ መሆኑን ስለሚገባው፡፡ ግን እንደተማርነው ትዳር ትልቅ ጉዳይ ነው አንዳንድ መምህራን እንዴውም ትዳር የትልቁ ቤተክርስቲያን  ምሳሌ ስለሆነ ትንሷ ቤተክርስቲያን ብለው ይጠሩዋታል፡፡ እና ይህንን ትልቅ ተቋም ለመምራት እጅግ ብዙ እውቀትና ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ ያንን እውቀትና ጥበብ ደግሞ በተወሰኑ ጊዜያት አሟልቶ፤መገኘት አይቻልም፡፡ ጉድለት በጊዜ ሂደት እየሞላ የሚሄድ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በቃ ምን ልበል አለችና ወደጆሮው ጠጋ አለች፡፡ የፈለግሽኝውን ማለት መብትሽ ነው አላት፡፡ ለምንድነው ፊትህን ከፊቴ ያነሳኸው ፊቴን እያየህ ላወራህ እፈልጋለሁ አለችው፡፡ እሺ አለና ፊቱን ወደፊቷ አዞሮ ቤተክርስቲያን ግን በመሆናቸው በመካከላቸው ያለውን ተገቢ ርቀት ጠብቀው ተቀመጡና እየተያዩ ማውራት ጀመሩ፡፡ ተፈሪ ፊት አይን አይኗን ሲያት ፈርታ አቀረቀረች ረቂቅ፤ ብዙም ሊያስጨንቃት አልፈለገም፡፡ እሺ የመጨረሻ ውሳኔሽን እኮ አልነገርሽም አላት፡፡ አውቃለሁ፡ ተፍዬ እንዴው ልትጫወትብኝ ፈልገህ ካልሆነ በስተቀር እንደወደድኩህ፤ ካንተ ውጭ የማንም መሆን እንደማልችል ታውቃለህ፡፡ ባዕድ ይቅርና ዘመድ እንኳን ወንድ ቀርቶ ሴት እንዳንተ ቀርቤ የልቤንም አውርቸው አላውቅም፤ከምወዳት ታናሽ እህቴ በስተቀር፡፡ ስለዚህ ለጠየክኝ ጥያቄ መልሴ እመብርሃን ቃሌን አክብሬ ክብሬን ጠብቄ ታኑረኝና የጀመርኩትን ትምህርት ታስጨርሰኝ እንጂ፤ በቀሪው እድሜ በሙሉ ካንተ ውጭ ሌላ ወንድ ላላይ ያንተ መሆኔን ጥያቄህንም በአክብሮት የተቀበልኩ መሆኔን በሰማይ አምሳያ በሆነችው ቅደስት ቤተክርሰቲያን ውስጥ ሆኜ ፈቃደኛነቴን፡ ጊዜው ሲደርስም አግብቸህ ለመኖር ፈቃደኛ መሆኔን ቃል እገባልሃለሁ፡አለችው፡፡ ረቂቅ ንግግሯና ቃላቶቹ እንዲሁም ከውስጡዋ ያለው ድምጸትና እርጋታዋ የበለጠ ልዬ ሆናበት እንደገና አፈቀራት፡፡ ተፈሪ ረቂቅን በተቀመጠችበት ትቷት ወደ ቤተመቅደሱ ሄደና መሬት ላይ ተንበርክኮ አምላኩን አመሰግኖ ተመልሶ መጣና ረቂቅን እቅፍ አድርጎ ትከሻዋ ከሳማት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ግንባሯንም ደጋግሞ ሳማት፡፡ እርሱ መቅደሱ አጠገብ፤ተንበርክኮ ሲጸልይ በነበረ ወቅት ረቂቅም የራሷን ጸሎት በተቀመጠችበት አድርሳ ጨርሳለች፡፡ ከዚያ በኃላ፤ሁለቱም በደስታ ሆነው አምላካቸውን በጋራ አመሰግነው ተያይዘው ወጡ፡፡ ቀስ እያሉ መንገዳቸውን እያቀኑ፡ እንግዲህ ለሚቀጥሉት ሶስት አመታት በትምህርት ላይ ትቆያለሽ እኔ ደግሞ ለሚቀጥለው አመት ትምህርቴን አጠናቅቃለሁ፡ ትምህርትሽን ጨርሰሽ ሁለት አመት ከሰራሽ በኋላ የአምላክ ፈቃድ ከሆነ ከአምስት አመት በኋላ ማለት ነው እንጋባለን፤ተባብለው ቃል እየተግባቡ፤መጪን ጊዜም በቅርበት በመወያትና በመካከር ሊኖሩ ተነጋግረው የቀን ውሎዋቸውን አጠናቀቁ፡፡ ተፈሪ ዛሬ ልቦናው በተለየ የኩራት ስሜት ነው፡፡ የሚረግጠውን ምድር፤በቁጥጥሩ ስር እንዳደረጋት ይሰማዋል፡፡ ከአራት ኪሎ ያንን ዳገት በምን ያክል ፍጥነት እንደወጡት አልታወቃቸውም፤ እነ ረቂቅ ሰፈር ቶሎ የደረሱ መሰላቸውና መለያየታቸውን ሲያስቡ ውስጣቸው ተከፋ፡፡ ወደ ሰፈር እየቀረቡ ሲሄዱ በመካከላቸው ያለው ቅርርብ የተለየ ትርጉም እንዳያሰጥ አድርገው ከጉልት ወደ ታች ያለውን መንገድ ስለሰፈራቸው እያወሩ ወደ ውስጥ አቀኑና ወግና ስርዓት ባለው መንፈሳዊ ሰላምታ ተሰጣጥተው ሞቅ ካለ የእጅ፤ሰላምታ መጨባበጥ ተደምሮበት ተለያዩ፡፡

 

ተፊረ ትምህርቱን አጠናቆ በአንድ ትልቅ የግል ፕሮጀክት ውስጥ በደህና ክፍያ፤ተቀጥሮ እየሰራ የእርሱ እና የቤተሰቡ ህይወት ተለውጧል፡፡ ረቂቅም ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በአንድ የመንግስት መ/ቤት ውስጥ ተቀጥራ መስራት ከጀመረች ሁለተኛ አመት እየሆናት ነው፡፡ከስራዋ ጎን ለጎንም በማታው ክፍለ ጊዜ ሁለተኛ ዲግሪዋን እየተማረች፡በዚህ አመት ትጨርሳለች፡፡ ባለፉት አመታት በተለይም ተፈሪ ስራ ከጀመረ በሁዋላ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ነገር ቀስ በስ እያሟሉ፤ሲሆን ተፈሪ ረቂቅን ከእናቱ እና ከእህቱ ጋር አስተዋዉቋታል፡፡ ረቂቅም፤ይፋዊ በሆነ መንገድ ባይሆንም እህቱዋና እናቱዋ አውቃል፡፡ ሁለቱ ወጣቶች መልካም የእጮኝነት ጊዜያቸውን አጠናቀው፤ቀደም ባለው ዘመን ቃል በገቡት መሰረት ዘንድሮ ለጋብቻ ተፍ ተፍ እያሉ ሲሆን ንሰሃ አባታቸውም ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡ የሚቀረው ሽማግሌ መላክ እና የሰርጉን ዕለት መወሰን ነው፡፡ ምናልባት በወርሃ ሚያዚያ ከፋሲካ ቀጥሎ ካሉት እሁዶች በአንዱ ይሆናል፤ ብለው ወስነው፤ሁለቱም ይፋዊ በሆነ መል ከቤተሰብ ጋር ትውውቅ ለማድረግ ቀጠሮ ይዘው፡ሳለ፡፡ አንድ ቀን ለተፈሪ እንኳን ደስ አለህ የሚል የኢሜል መልዕክት መጣለት ዝርዝሩን ሲያነበው በአጋጣሚ በአንድ ወቅት ቻይና ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ዩኒቨርስቲ ለሁለተኛ ዲግሪ ያመለከተው ስኮላር ሽፕ ተቀባይነት እንዳገኘና በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ መጥቶ ትምህርቱን መጀመር እንዳለበት የሚገልጽ ኢሜል መልዕክት ነበር፡፡ መልዕክቱ፤ የውሸት አለመሆኑን ደጋግሞ ካጣራ በሁዋላ ወደ ረቂቅ ዘንድ ስልኩን አነሳና ደወለ፡፡ ብዙ ሳይቆይ አነሳችውና ወይ ፍቅር እያሰብኩህ ነበር የደወልከው አለችው፡፡ አመሰግናለሁ ፍቅር ምሳ ተገናኝተን አብረን ብንበላስ አላት፤ይገርምሃል እኔም ለስራ ከቢሮ ወጥቼ ወደ አንተ ቢሮ አካባቢ ስደርስ እኮ ነው ልደውል አልደውል እያል ሳመነታ የደወልከው አለችው፡፡ ወይ ደስ ይላል በቃ መጣሁ የቱጋር ነሽ አለና እርሷ ወዳለችበት ቦታ የስራ ልብሱን ቀይሮ ወጣ፡፡

እንደደረሰ በተለየ ሁኔታ ሰላም ካላት በሁዋላ፤ ትንሽ ራመድ ራመድ አሉና ወደ አንድ ቀለል ወዳለ ሬስቶራንት ገቡ፡፡ ምሳቸውን እየተጎራረሱ ከበሉ በሁዋላ ወደ ሌላ ካፌ ሄደው ማኪያቶ እየጠጡ፤ ፕሪንት ያደረገውን የኢሜል ደብዳቤ ሰጣት፡ ምንድነው ብላ አንብባ እንደጨረሰች ዋው ኮንግራ ብላ ተነስታ ተጠመጠመችበት፡፡አጸፋውን መለሰላት፡፡ ከሞቀው ደስታ በኋላ ግን፤ፍቅር ይህ ነገር ፕሮግራማችንን ይረብሻል፡፡ ፕሮግራማችንን እናድርግው እንኳ ብንል ከተጋባን ወር ባልሞላ ጊዜው ውስጥ እንለያያለን አላት፡፡ እናራዝመው ካልን ደግሞ ተጨማሪ ሁለት አመት እንቆያለን አላት፡፡ ትንሽ አሰብ አደረገችበት እና ተወው ፍቅር አሁን ይህ ደስታነው እንዴት እናድርግ፡ የሚለውን እናስብበታለን፤ለአባታችንም እናማክራቸው ከሁሉም በላይ ደግሞ ተስፋችን እርሱ አይደል የሚለንን እናደርጋል አለችና አይኑዋን ወደ ፈጣሪ አነሳች፡፡ እሺ የኔማር አላትና ደስታ የተሞላበት አጭር ጊዜ አሳልፈው ከስራ ሰዓት በሁዋላም ሊገናኙ ተቀጣጥረው ተለያዩ፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚያደርጉት ስድስት ኪሎ ዩነቨርስቲ  ከዋናው በር ፊት ለፊት ከሚገኘው፡ድባብ መናፈሻ ተገኛኑና እስከምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ብዙ አወሩበትና ተጋብቶ ከአንድ ወር ላነሰ ጊዜ ቆይቶ ከመለያየት ትምህርቱን ጨርሶ ከመጣ በኋላ፤ መጋባት በሚለው ኃሳብ ተስማምተው፤  ይህንን ሃሳብ ለንሰሃ አባታቸውም ሊያማክሩዋቸው፡ እርሱ ደግሞ ከመሄዱ በፊት ከወላጆቹዋ ጋር ልታስተዋዉቀው እንደሚገባ ስምምነት ላይ ደረሱና በኮንትራት ታክሲ ቤትዋ አድርሶዋት፡ተለያዩ፡፡ ሁለት ሰዓት አሳልፋ፤ ስትገባ ሳሎን የነበሩት አባትዋ ነዋር አለሜ ምነው መሸብሽ ስራ በዛ ብለው ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ግንባርዋን ስመው ቦርሳዋን ተቀበሉዋት፡፡ አረ አይደለም  አባዬ አንድ የግል ጉዳይ ነበረኝ፤ ከቢሮ ውጭ ለዚያ ነው ቆየሁት፤ ያልደወልኩት እስከዚህ እቆያለሁ ብዬ አስቤ ስላልነበር ነው፡ አለቻቸው፡፡ አለሜ ታወቂያለሽ እኔ እንኳን ዛሬ ትልቅ ሰው ሆነሽ ዱሮም አንችን አልቆጣጠር፤ አንች እኮ አለሜነሽ፤ ክብርሽን የምትጠብቂ አሉዋት፡፡ አውቃለሁ አባዬ አለችና ጠጋ ብላ እቅፍ አደረገቻቸው፡፡ ደረታቸው ላይ ተለጥፋ ትንሽ ሰትቆይ የሚሰማት ደስታ ልዩ ነው፡፡ በይ ግቢ ልብስሽን ቀይሪና ነይ ብለው አሰናበትዋት፡፡ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ሁሉም የቤተሰብ አባል ባለበት ሆኖ እንዲሰማት ሰላምታ አቀረበች፡፡ ፍቅርዋን በለከፋ የምትገልጽላት ታናሽ እህቷ ጎረምሳው መጣህ፤ እሰይ ግባ ዛሬ ደግሞ ምነው በጊዜ መጣህ አለቻት፡አባት በሁለቱ ልጆቻቸው ፍቅር በጣም ደስተኛ ናቸው፡፡ አንችማነሽ ትንሷ አስቲ ተነሽና እህትሽን እግርዋን እጠቢያት አሉ የምትለውን መስማት ፈልገው፡፡ እሺ አባትየው ውሃ ትንሽ ሞቅ ይበል ብዬ ነው አጥባታለሁ፡ ስትል ቤተሰቡ በያለበት ሆኖ ይስቃል፡፡ በዚህ መሰረት የእነረቂቅ ቤት የማታ ድምቀቱ ይጀምርና ሁሉም ሲተኛ ረቂቅና አቶ ዝናው ግን ትንሽ ቆይተው የልብ ልባቸውን ካወሩ በሁዋላ ነው የሚተኙት፡፡ ረቂቅ ዛሬ ቤት ከገባች ጀምሮ በውስጣ ሲብሰለሰል የነበረውን ሃሳብ ለአባቷ ልታማክራቸው ወስናለች፡ምንም እንደማይሉዋት እርግጠኛ ነች፡፡ ምክራቸው፤ለውሳኔ ይረዳታል፡፡

ዛሬ ወደ መኝታ ክፍላቸው  በመጨረሻ የሄዱት፤ ወላጅ እናቱዋ ሲሆኑ በሉ እናንተ ዘበኞች ስትተኙ መብራት ማጥፋትና ሶኬት መንቀላችሁ አትርሱ ብለው ሲገቡ አባት ብድግ አሉና እሺ እመቴ እንዳሉ አሉና ሚስታቸውን፤አስቀው ወደ መኝታ ክፈላቸው ላኩ፡፡ ትንሽ ዝም ብለው ከቆዩ በኃላ በህግ ሙያ የተሰማሩ አባትዋን፤ረቂቅ ፈራ ተባ እያለች አባ አንድ ነገር ላማክርህ ነበር አለቻው፡፡ ወይ ምን ገዶኝ ልጄ፤ አማክሪኛ አሉዋት፡፡ እርሷም አንድም ሳታስቀር ከተፌ ጋር ያላትን ግንኙነት አስረድታቸው አሁን ግን ለሰርግ ሲዘጋጁ የገጠማቸውን ሁኔታ ትንሽ እንደከበዳቸው እና በዚህ ረገድ ምክር እንዲለግሱዋት ጠየቀቻቸው፡፡አቶ ዝናው ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው በቤታቸው፡በምስራቁ በኩል ወደ ተሰቀለው የመድኃኔአለም ስዕል ሄዱና ተመስገን አምላኬ ብለው አምላካቸውን ካመሰገኑ በኋላ ተመልሰው፤ልጃቸውን ረጂም፤ሰዓት እቅፍ አድርገው መረቁዋት፡፡ ልጄ ባንች እንደምኮራ ሁሌም ልቤ ይነግረኛል፡ አሁንም ኩራቴ ነሽ፡፡ የነገርሽኝን ነገር፤የመጨረሻ፤ ውሳኔ ሰጭ አንችና አጋራሽ ብትሆኑም እኔ ግን ሁለት አመት ብዙ ሩቅ ስላልሆነ ያገኘውን ዕድል ቢጠቀምበት ሁለታችም ደስተኛ ትሆናላችሁ፡ብዬ አስባለሁ፡፡ ለትዳሩ ብሎ ግን ይህንን ዕድል ቢጨናግፈው፤ ለሰርግ ብዬ እያለ ይጸጽተና አንችንም ሊያሳዝንሽ ይችላል፡ እና አንች እኮ ልጅ ነሽ ሁለት አመት ብትታገሽው ምን ችግር አለው አሉዋት በጥያቄ መልክ፡፡ ምንም አባዬ መልካም ከመሆኑ የተነሳ እንኳን ሁለት አመት10 አመትም እታገሰዋለሁ አለቻቸው፡፡ አሰይ ልጄ አድግ ብለሽልኛል አሉዋት፡፡ እንዴው የእርሱስ ኃሳብ አሉዋት፡፡ እርሱም በዚህ ሃሳብ ይስማማል፤ ዛሬ እኮ የቆየሁት በዚሁ ጉዳይ ስንወያይ ነበር አለቻቸው፡፡እሰይ ባይሆን ከመሄዱ በፊት አስተዋውቂን፤ቤተሰቡንም እንወቃቸው አሉዋት፡፡ መልካም አባዬ በጣም ነው የማመሰግነው አለቻቸው፡፡ ማንን እኔ ይህ እኮ ግዴታዬ ነው፡፡ መውለድ ብቻ ሳይሆን አሳድጎ አስተምሮ ልጅን በክብር ድሮ ለወግ ለማዕረግ ማድረስን የመሰለ ምን መልካም ነገር አለ፡፡ ወላጅ እኮ እድሜው የሚገፋው፤ ደስም የሚለው በልጆቹ አለም ነው፡፡ እያሉ ብዙ ምክር መከርዋት፡፡ በዚህም ልቧ እርፍ ብሎ ቆንጆ እንቅልፍ ወሰዳት፡፡

ተፈሪም ለእህቱና ለእናቱ ያለውን ሁሉ የዚያኑ ዕለት ማታ ነግሩዋቸው እነርሱም በእርሱ ኃሳብ ተስማሙ፡ እናቱ ግን ልጄ መቼም ጊዜ የማይለውጠው የለምና ከመጥፎ ፈተና ለመጠበቅም ለምን ከመሄድህ በፊት ሽማግሌ ልከህ ቀለበት አታደርግላትም አሉት፡፡ ይህ ኃሳብ ከማንም ያልመጣ በመሆኑ ተፈሪ በጣም ገረመው፡፡ አዎ ይቻላል ምን ችግር አለው፡፡ በቃ ይህንኑ ጉዳዩ ከ ሪ ም ሆነ ከንሰሃ አባቴ ጋር እነጋገርበታለሁ አለ፡፡ በቀጣይ ቀን በምሳ ሰዓት ተፈሪ የኮንትራት ታክሲ ይዞ ወደ ረቂቅ መ/ቤት አካባቢ መጥቶ ምሳ አብረው እንደሚበሉ፤ጠዋት በስልክ ደውሎ ነገራትና በምሳ ሰዓት ሁለቱም ማታ ከወላጆቻቸው ጋር የተወያዩትን እናየደረሱበትን ድምዳሜ ተወያዩ፡፡ በመጨረሻም ሽማግሌ መላክና ቀለበት ማድረግ አዲስ ሃሳብ ሆኖ ይህንንም ዛሬ ማታ ለንሰሃ አባታቸው ሊያማክሩዋቸው ተስማምተው ተለያዩና፤ ማታ ወደ አባ ክፍለ ማርያም አቀኑ፡፡ የቀረበውን ሃሳብ ከሰሙ በኃላ፤ አባ ይህ ከቤተክርስቲያን አስተምሮ ፤አንጻር ችግር እንደሌለው ይልቁንም ከፈተና ሁለቱንም እንደሚጠብቃቸው ነግረዋቸው ሽማግሌ መላክ በሚለው ሃሳብ ተስማሙ፡፡ ይህ ሃሳብ በረቂቅ ወላጆችም ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ የሽማግሌ መረጣና ቀን ቆረጣ ተወሰነ፡፡

በመጨረሻም ተፈሪና ረቂቂ አንድ ላይ ሆነው አስተርእዮ ማርያምን በአዳዲ ማርያም ቤተክርስቲያን ለመጨረሻ ጊዜ አክብረው በሚቀጥለው እሁድ ሽማግሌ ተልኮ የተፊ በረራም የካቲት 1 ሊሆን ተወስነ፡፡ በአባ ክፍለማርያም መሪነትም የተመረጡ አምስት ሽግሌዎች ወደ እነረቂቅ ቤት ሊሄዱና በዚያው ቀን አባ ጸሎት ያደረጉበት ቀለበት ከቀኑ አስር ሰዓት ሁለቱ እጮኛሞች የሁለቱም ወላጆች ባሉበት በእነ ረቂቅ ቤት ቀለበት ለማድረግ ቀን ተወስኖ እጅግ አጭር ግን ደግሞ ደስ በሚል ስነስርዓተ ተከናወነ፡፡ ይህ ስርዓት ሲጠናቀቅ ቀን ተቆጥሮ ከሁለት አመት በሁዋላ ጥር 16/2020 ቀን የጋብቻቸው ፕሮግራም በምስኪያህዝኑና ገዳም በስርዓተ ተክሊል፡እንዲከናወን፤የሁለቱም ሙሽሮች ቤተሰብ በጋራ በሆቴል በሚያዘጋጁት የምሳ ግብዣ እንደሚኖር ተወስኖ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ ተፈሪ ከሌሎች አምስት ኢትዮጲየን ተማሪዎች ጋር ሆኖ በኢትዮጲያ አየር መንገድ ወደ ሀገረ ቻይና ሁዋን ግዛት ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱ አቀና፡፡

ረቂቅ ሳታቋርጥ የተፈሪን እናትና እህት እየሄደች በመጠየቅ በወር አንድ ጊዜም ላቭ ቶፕዋን ይዛ በመሄዴ ተፈሪን ከእናቱእና ከእህቱ ጋር በስካይፕ እየተያዩ እንዲያወሩ ተፈሪ የጣለባትን አደራ በሚገባ ተወጥታለች፡፡ እርሱዋና እርሱም  በሚቻለው መገናኛ ሁሉ እየተገናኙ ሁለቱን አመት ምንም ሳይመስላቸው ሊያጠናቅቁና ተፈሪ ለመጨረሻው ዙር ፈተና እያጠና እያለ ባለበት ሰዓት የቻይና ግዛት ውስጥ በትንፋሽ የሚተላፍ በሽታ ስለመግባቱ ፡ለረቂቅ ነገሩዋት ብዙም ኣሳሰቢ እንዳልሆነ ይልቁንም የሽብር ወሬ ነው ተብሎ ይህንን ያወራው ዶ.ር እንደታሰረ ነገራት፡፡ ይሁን እንጂ በበሽታው የሚይዙ ሰዎች፤ቁጥር ዕለት ከዕለት እየጨመረ ይልቁንም አለም አቀፋዊ አጀንዳ መሆን ሲጀምር በሁሉም ዘንድ ከባድ የሀዘን ድባብ ፈጠረ፡፡ ተፈሪና ረቂቅ በሰዓታት ልዩነት ይደዋወላሉ፤ ቴክስት ይደራረጋሉ ግን ስጋቱ በውስጣቸው እያየለ ይሄዳል እንጂ ብዙም ጠብ የሚል መልካም ነገር የለም፡፡ ይባስ ብሎ ተፈሪ ወደ ሀገሩ ሊመጣ አንድ ወር ሲቀረው፤የቻይና ውሃን ግዛት ለሶስት ወር ዝግ ተደረገ፡፡ በሁለቱም ላይ ምድር ተደፋችባቸው፡ በጥር ወር ሰርግ ስለሚበዛ ቀደም ብላ በጥቅምት ወር ለሆቴልና ለአዳራሽ ቅድመ ክፍያ፤ከፍላለች፡የምትሰረግበትን ልብስ መርጣ አሰፍታለች፡፡ የተክሊል ልብስም ቀድማ መርጣ ክፍያ ፈጽማች፡ የጥሪ ካርድ ሊታተም ወደማተሚያ ቤት መሄድ ብቻ ነው የቀረው፡፡ አቶ ዝናው፤ቤት ለሚመጣ ጎረቤትና ዘመድ ተገቢውን ዝግጅት አጠናቀዋል፡፡ይህ የሶስት ወር ዝግ አዋጅ ሲታወጂ እንደ ሁኔታውም ወደፊት ሊራዘም እንደሚችል ሲገለጽ ሃዘናቸው፤ከባድ ሆነ፡፡ ወደ ተፈሪ ወላጅ ቤት እንደወትሮው ብትሄድም እናቱን አጽናኝ መሆንዋ ቀርቶ እርሷ ሆደባሻ ሆና ጉልበታቸው ላይ ደገፍ እንዳለች እንቅልፍ ወስዷት ጸጉሩዋን እንደህጻን እያሻሹ ሲያባብሉዋት፤ የምትገኝበት ሁኔታ እየጨመረ መጣ፡፡ ወላጅ እናቱ ከወለዱት ልጃቸው ይልቅ እዚህ በቅርበት የሚያዩት ወደፊት የልጃቸው ባለቤት ጉስቁልናና ጭንቅ ልባቸውን በጣም ይረብሸዋል፡፡

ተፈሪ በሚችለው ሁሉ እራሱን ይጠብቃል፤ አምላኩን ይማጸናል፡ያለበትን ሁኔታም ሀገር ቤት ላሉ ሁሉ፤መረጃ ይሰጣል፡፡ ይልቅስ ከሃዘን በጸሎት እንዲያስቡት ይማጸናል፤አንዳንድ ጊዜ እርሱ ከረቂቅ ተሸሎ እርሷን ይቆጣል፡፡ በቻይና ያለው ሁኔታ ዕለት ዕለት እየባሰ ሲሄድና ተስፋው ሲጨልም ቀድመው የተያዙት ፕሮግራሞች ሁሉ እንዲሰረዙ ተደረገ፡፡ አንዳንዶች ሁኔታውን ተረድተው የተከፈላቸውን ክፍያ ሙሉ ሲመልሱ ጥቂቶች ግን በንግድ ቋንቋ ስላዩት መቀጫ እየቆረጡ መለሱ፡፡ ረቂቅ ሁሉም ምንም ቁም ነገር አልሰጣትም፡፡ እርሷ ሁሌም የሚያሳስባት የተፈሪ ህይወት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ጋብቻቸው በተዋወቁ ሰባተኛ አመታቸውም ተግባራዊ እንዳይሆን ኮሮና /ሳንባ ቆልፍ በሽታ/ እንዳይሳካ አደረገው፡፡ የቻይና ሁኔታ እስከመጋቢት ወር መጀመሪያ ድረስ፤ምንም ለውጥ ሳይመጣ ሁሉም ዝግ እንደሆነ ቀጠለ፡፡ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ግን ትልቅ ተስፋ መሰማት ጀመረ፡፡ በሽታውን ቻይናዊያን ተቆጣጠሩት፤ ተፈሪም እስከዚች ቀን ድረስ ምንም ሳይሆን ቀረውን ትምህርቱንም በ ኦን ላይ ተከታትሎ ፈተና ብቻ ይቀረዋል፡፡ እርሱም በወርሃ መጋቢት አጋማሽ እንደሚወስድ ተነግሮታል፡፡ ይህንን መረጃ ግን ለረቂቅም ሆነ ሀገር ቤት ላለ ማንኛውም አካል አልተናገረም፤ ይህንን የሚያጨልም ሌላ ነገር ቢፈጠር፤ሰቀቀን ላለመፍጠር አስቦ፡፡ እንደተባለው ዩኒቨርሰቲው ፈተናው ሰጥቶ የትምህርት ማስረጃዎቹን በሙሉ በአንድ ሳምንት ጊዜውስጥ አጠናቆ ወደ ሀገሩ ለመሄድ ተነሳ፡፡ እጅግ አስቸጋሪው ግን በርካታ አየር መንገዶች በረራ ስላቁዋረጡ፤ ቀጥታ በረራ የለም፡፡ ለው ብቸኛ በረራ፤ከቻይና ግብጽ ከዚም 14 ቀን ማግለያ ተቀምጦ ቫይረሱ ካልተገኘበት፤ወደ ሀገሩ መግባት እንደሚችል አረጋገጠና፤ይህንኑ አማራጭ ለመጠቀም ከሌሎች አብረው ካሉ፤ ኢትዮጲያዊያንተማሪዎች ጋር ወደ ግብጽ ለመብረር ወስነው በረሩ፡፡ ግብጽም ማግለያ፤ጣቢያ ገቡ፡፡ በዚህ መሀል ወደ ሀገርቤት እየተመለሰ ስለመሆኑ የባሰ ከመጣ ብሎ ለአንድ ጓደኛው ብቻ ነግሮታል እንጂ ለማንም ትንፍሽ አላለም፡፡ ካይሮ እያለም እንደበፊቱ ቶሎ ቶሎ ሳይሆን አልፎ አልፎ ብቻ ለረቂቅ በፊስቡክ ያወራታል፡ ምክንያቱን ስትጠይቀው ፈተና ስለሆነ በጣም ተጨናንቄያለሁ በዚያም ላይ ኔትወርክ እንደበፊቱ አይደለም እያለ ይነግራታል፡፡ ምክንያቱ አሳማኝ እንዳልሆነ፤ ውስጧ ቢገባውም የባሰ እንደይመጣ በማለት ሁሉን በውስጧ ችላ ዝም ብላለች፡፡ አምላክዋን ግን ሁሌም በጸሎት ትጨቀጭቀዋለች፡፡ ተፈሪ 14ኛ ቀኑን ከቫይረሱ ነጻ መሆኑን ስለተረጋገጠ ፤ በሄደበት የሀገሩ አውሮፕላን በሀበሻ አብራሪና አስተናጋጅ፤ከካይሮ አዲስ አበባ ገባ፡፡ ገና በአውሮፕላን ላይ እያለ በሀገሩ ምድር መግባቱን ሲያረጋግጥ ከተቀመጠበት ተነስቶ አምላኩን አመሰገነ፡፡አዲስ አበባም የገጠመው ይኸው ነው ወደ ለይቶ ማቆያ፡፡በለይቶ ማቆያ ለመቆየት ከቀረቡለት አማራጮች በነጻ ወደ ዩኒቨርስቲ ካልሆነም ወደ ሆቴል መሄድ እንደሚችል ሲነገረው፡ ምንም ሳያንገራግር ወደ አየር መንገዱ ባለ አምስት ኮኮብ ስካይ ላይት ሆቴል ለመሄድ ወስኖ ወደዚው አቀና፡፡ ወደ ሆቴሉ የወሰደውን አሽከርካሪ ወንድሜ የፈለግከውን ዋጋ፤እከፍልሃለሁ ሲም ካርድህን ስጠኝ አለው፡፡ ትንሽ ከተነጋገሩ በሁዋላ ገጥሞት የነበረውን ችግር ሲነግረው፤አሽከርካሪው፤አንጀቱ ሊጨክን አልቻለም ትርፍን ሲም ካርድ አውጥቶ ሰጠውና ሰው ሲደውል ይኸኛውን ቁጥሬን ስጣቸው ብሎት ቁጥሩን ሰጠው፡፡ ተፈሪ ያገሬ ልጅ ወንድሜ ስላደረክልኝ ውለታ ደስታዬን እቅፍ አድርጌ ብገልጽልህ ምንኛ ደስባለኝ ግን አየህ ይህ የማይረባ በሽታ በፍቅራችን ገባ እና አራራቀን እንደነገርኩህ ላለፍት ሁለት አመታት ከሀገሬ ርቄ በዚህ በተረገመ በሽታ የተነሳ ሰርጌ ካለፈ ከሁለት ወር በሁዋላ ግብጽ 14 ቀን ኮራንታየን ገብቼ ለሌላ 14 ቀን እዚህ ልገባ ነው፡፡ ሀገሬ እንኳ ገብቼ የቤተክርሲያንን ደጅ እንዳልስም እጣኑን እንዳላሸት አቅመ ደካማ እናቴን አይኗን እንዳላይ፤በጉጉት ስትጠብቀኝ የነበረችውን የሰባት አመት ፍቅረኛዬን ፍቅሬን ከልቤ እንዳልገልጽት እያደረገኝ ነው አለና ሳያሰበው እንባውን በቁሙ ሲለቀው ወጣቱ አሽከርካሪም እንባውን መቆጣጠር አቅቶት እርሱም እያለቀሰ ወደ ታክሲው ተመልሶ ገባ፡፡ ተፈሪ አልጋ ክፍሉ ከመግባቱ በፊት ማድረግ ስለሚጋበው ጥንቃቄ፤ ገለጻና ማብራሪያ ቅድመ ምርመራና ምዝገባ ተከናውኖለት በ ስልኩ ላይ የ200. 00 ብር ካርድ ሞልቶ ገባ አምስተኛ ፎቅ አልጋ ቁጥር 510 የገባው ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፤ረቂቅ በዚህ ሰኣት ቢሮ መሆንዋ ገመተና ቆይ ቤት ትግባ አሁን ድንገት ደውዬ አላስደነግጣትም አለና፡፡ ሻውር ወስዶ የናፈቃትን አዲስ አበባን፤አልጋ ክፍሉ በረንዳ ላይ ወጥቶ ንጹህ አየርዋን ወደ ውስጡ እየማገ በስሰት አያት፡፡መንገዶችዋ እንደበፊቱ የተጨናነቁ አይደሉም በሽታው እዚህም ስለገባ፤በተወሰነ መልኩ ክልከላዎችም ስላሉ መንገድ ላይ ያለው መጨናነቅ ቀንስዋል፡፡

ረቂቅ 11 ሰዓት ከቢሮዋ ወጥታ ፍራፍሬና የተወሰኑ እቃዎች ገዝታ ወደ ተፈሪ እናት ቤት ገብታ ሰላምታ ሰጥታቸው አረፍ እንደላች ስልኳ ጮኸ፡፡ ከቦርሳዋ አውጥታ ስታየው ስም የለውም ግን የኢትዮጲያ፤ ቁጥር ነው፤በትሩ ኮለርም ስም አልወጣም፡ ማን ይሆን ብላ ስልኩን አነሳችና ሄሎ አለች ከዚኛው ወገን ግን ምንም አይነት ድምጽ የለም ከርቀት የሚሰማ ኢትዮጲ ታበጽህ እደዊሃ የሚል መዝሙር ብቻ ይሰማታል፡፡ ተፈሪ ሄሌ ያላላት ያለችበትን ቦታ ለመገመት እንዲያስችለው በማሰብ ነበር፡፡ ደጋግማ ሄሎ ብትልም ምን ድምጽ ስላልሰማች ማነው ብላ መልሳ ዘጋችው፡፡ ተፈሪ ያለችበትን ቦታ፤መገመት አልቻለም፡ግን ጸጥ ያለቦታ እንደሆነ ገምቷል፡፡ የት ትሆን ቤተክርስቲን እንዳትሆን ወደ ቤተክርስቲን መግባት ተከልክሏል የሚል መረጃ ነግራዋለች፡፡ ስራም እየጋባች፤ እንደሆነ ነግራዋለች፤እና ቤት ወይስ ማዘር ጋ ሄዳ ነው አለና ውሳኔላይ ሳይደርስ መልሶ ደወለው፡፡ ወይ ማዘር ይህ ስልክ መልሶ ተደወለ አለችና ስታነሳው ልጄ ይሆናል ብለው ሲያወሩ የእናቱ፤ ድምጽ ጆሮው ላይ ጥልቅ አለ፡፡ ሄሌ አለችው በትህትና ሄሌ አላት መልሶ አቤት ማን ልበል አለችው፤ ፍቅርን በዚህ ስልክ ማግኘት እችል ይሆን አላት ድምጹ ትንሽ ቀየር አድረጎታል ወይ ይቅርታ ተሳስተዋል የፍቅር ስልክ አይደለም አለችው፡፡ አልተሳሳትኩም፤ረቂቅ የእኔ ፍቅር አይደለሽም ብሎ በእውነተኛ ድምጽ፤ ሲያናራት ወይኔ ማዘር ብላ ወደ ተፈሪ እናት ስልኩን ወረወረችውና ወደ ጓዳ ሮጠች፡፡ የተፈሪ እናት ስልኩን ከወደቀበት አነሱና ሄሌ ማን ልበል ምንድነው ልጄን ያስደነገጥካት አሉ፡ተፈሪ የዕናቱን ድምጽ ሲሰማና ረቂቅ መደንገጥዋን ሲያወቅ መናገር አቅቶት ዝም አለ፡፡ ሄሌ አሉ እናቱ በድጋሚ አረ ሄሌ ሲሉ ትንሽ የተረጋጋችው ረቂቅ  ከተፈሪ እናት ስልኩን ወሰደችና ሄሌ ተፌ አለች ወይ ፍቅር አላት አንተ ይህ እኮ የኢትዮጲ ቁጥር ነው የትሆነህ ነው አለችው፡፡ ሀገሬ ኢትዮጲያ አዲስ አበባ አላት፡በሳግ ድምጽ፡፡ ተፍዬ በማዘር አትቀልድ የት ነው ያለኸው ስትል የተፈሪ እናት ተነስተው ጆሮዋ ላይ ተለጥፉባት፡፡ ፍቅር እውነቴን ነው አዲስ አበባ ከአንድ ሰዓት በፊት ገብቼ አሁን ስካይ ላይት ሆቴል ነው ያለሁት እንደምታውቂው ቀጥታ ከሰው ጋር መገናኘት ስለማይቻል፤ወደ ለይቶ ማቆያ ገብቻለሁ፤ አምላከ ቅዱሳን ይክበር ይመስገንና ለሀገሬ ምድር በቅቻለሁ ሲላት ቤቱን በእልልታ አጥለቀለቀችው፡፡ ጉዳዩ ለመልካም መሆኑ የገባቸው የተፈሪ እናትም ተንበርክከው በስዕለ ማርያም ፊት እየሰገዱ እልልታውን አቀለጡት፡፡ሪ ማሚምን አረጋጊያትና መልሼ ልደውል ብሎ ስልኩን ዘጋው፡፡ ስልኩን ዘግቶ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ ብሶቱ ከውስጡ በእንባ ታጥቦ ሊወጣለት አልቻለም፡፡ ረጂም ሰዓት ባለቀሰ በወደደ ግን ከጥቂት ቆይታ በኃላ ስልኩ ጮኸ፡፡ የረቂቅ አልነበረም ሲም የሰጠው ያ ትሁት አሽከርካሪ ነበር፤ ስለደህንነቱና ዘመዶቹን ስለማግኘቱ ሊጠይቀው፡፡ የእርሱን ዘግቶ ትንሽ ጎርደድ እንዳለ፤ረቂቅ ደወለች፡፡ ስማ ተፌ ግን ደህና ነህ አለችው ፍቅር እኔ እጅግ በጣም ደህና ነኝ የእናንተ ፍቅርና ናፍቆት ውስጤን ከሚረብሼኝ በስተቀር፡፡ ዛሬ ከቻይና ተነስተህ ነው አለችው፡፡ ፍቅር እርሱ ታሪኩ ረጂም ነው ሌላ ጊዜ እነግርሻሁ፡፡ አሁን ሀገሬ ገብቼ አጠገቤ እንደሆንሽ እያሰብኩ መደሰትና ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመውን ሰርጋችንን መች እንደሚሆን ብቻ ማሰብ ነው የምፈልገው አላት፡፡ እኔም፤የእኔ ፍቅር አለችውና ተረጋግታ ማናገር ስላልቻለች እማ ተፌን አናግሩት ብላ ስልኩን ሰጠቻቸው ልጄ ደክሞሀል ድምጽህን ብቻ አሰማኝ አሉት፤ማሚ እንዴት ነሽ፤ ምንድነው አካኪ ዘራፍ የምትይው እግዚአብሔርን አመስግኝ እንጂ በሰላም ሀገሬ ገብቻለሁ አላቸውና አረጋቶ መልሶ እንደሚደውል ከነገራቸው በሁዋላ እታባስ አለ፤ እታባ ከስራ አልገባችም ስትገባ ትደውልሃለች አለችውና በቃ እረፍ ብላ ስልኩን ዘጋችና የተፈሪን እናትና የደስታ እልልታውን ሰምተው የመጡትን ሰዎች፤ ግማሹን በማቀፍ ግማሹን ደግሞ ከአንገትዋ እጅግ ጎንበስ እያለች፤ የደስታዋ ተጋሪ መሆናቸውን እያመሰገኘች ሸኘቻቸው፡፡፤ኮሮና አሁንም ማቀፍን መከልከሉ የደስታዋ እንቅፋት እንደሆነባት፤በምሬት ረግማዋለች፡፡ ነገሮች በዚህ መልኩ ከተረጋግጉ፤በሁዋላ ረቂቅ በደስታ ሲቃ እየተፍነከነከች የወላጆቿቤት የእንጦጦ ተራራን ያክል ርቆባት በግድ  ደረሰች፡፡ እንደደረሰች አባትና እናትዋ ሳሎን ቁጭ ብለው ሲያወጉ ደረሰችና ከፊታቸው ቆም አለች፡፡ አለሜ አሉና አባትየው ብድግ ሲሉ አባ አትነሳ እዚው ሁን ብላ በራ እግራቸው ስር ተደፋች፡፡ አባት ልጃቸው በደረሰባት ከባድ ፈተና ውስጣቸው በጣም ያዝናል፡፡ እንዴው ልጄ፡ሁለት አመት ሙሉ ተስፋ ስታደርግ ቆይታ ይኽ መጥፎ በሽታ ሰርጓን፤አስታጎሎ ምናለ ጓደኛዋን፤እንኳ በሰላም ቢመልስላት እያሉ ዘወትር ጠዋትና ማታ በልባቸው እህህ እንዳሉ ነው፡፡  ልጄ ምንድነው አሉ አባትና እናት ግራ ተጋብተው፡፡ አይ ዛሬ ትልቅ የደስታዬ ቀን ነው ቁጭ ብሉ ብላ ሁለቱንም ፈጥና አስቀመጠቻቸው፡፡ ቁጭ እንዳሉም ተፈሪ መጣ ብላ የደስታውን ብስራት አበሰረቻቸውና ደስታዋን መቆጣጠር አቅቷት ሁለቱምን እቅፍ አደረገቻቸው፡፡ እህ ምን አልሽ አሉ አባት ጆሮዋቸውን ተጠራጥረው፡፡ ተፈሪ መጣ እኮ ነው የምልህ አባዬ አለቻቸው አባትዋ በደስታ እቅፍ አድርገዋት ተመስገን አምላኬ እያሉ እንባቸውን እርሳቸውም አፈሰሱ፡፡የአቶ ዝናው ቤት በደስታ ሞልቶ አመሸ፡፡ ስልኩ እንዴ ወደ ተፈሪ ሌላ ጊዜ ወደ ተፈሪ ወላጆች ሲደወል ለዘመድ ሁሉ ዜናው ሲበሰር አደረ፡፡ ረቂቅ በዚህ ሁሉ መሃል ምን እየተፈጠረ እንደሆነ አይገባትም ከሚቆመው ጋር ትቆማለች፤ሲቀመጡ ትቀመጣለች፡ትስቃለች በቃ ደስታ ፍንክንክ አድርጉት፤ ታናሽ እህትዋን አስሬ እያቀፈች ትስማታለች፡፡ ማቀፍና መሳሙ የበዛባት ታናሽ እህትዋ ቀስ ብላ በጆሮዋ ጠጋ ብላ ቀስ በይ ጨምቀሽ ገደልሽ፤ተፈሪ መስየሽም አሳሳምሽ ወደ ከንፈሬ ጠጋ እያለ ነው አለቻትና ከጉያዋ ስትወጣ እየሳቀች ተከትላት ወደ መኝታ ክፍላቸው ገቡ፡፡ ወይ ሪ፤ እንደዚህ ደስብሎሽ አይቸሽ አላውቅም በተለይ ደግሞ በላፍት ሁለት ወራት የነበረሽን ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ ስመለከት ምንኛ አሳዝነሽኝ እንደነበር ልነግርሽ አልችልም፡፡ እኔ እኮ ጎበዝ ትመስይኝ ነበር፡ ተፈሪ በጣም ነው የገባልሽ አለችና አዛኝ ንግግሯን ወደ ቀልድ ወስዳ እንደገና እህቷን ለጸብ እንድትጋበዝ አደረገቻት፡፡ ግን ሪ አሁን መች ነው ሰርጋችሁ ስትላት ትቀልጃለሽ እንዴ በወጣ በማግስቱ ነዋ፤ከዚህ በሁዋላማ አንድም ቀን አላድርም፤ ቤተሰብ ሲፈልግ ድግሱን እኛ ከተጋባን በሁዋላ ያደርግ ከዚህ በሁዋላ ከተፌ ጋር ለአንድ ቀንም መለየት አልፈልግም፡፡ እቅፍ ውስጥ መግባት ናፍቆኛል፡ ስትላት አንች ሚጢር አወጣሽ ለካ ከመሄዱ በፊት እቅፍ ውስጥ ገብተሸ እ…. ምናምን ስትላት፤ለማናደድ መሆኑ ስለገባት አንች አፈር ብይ ጥላት ሄደችና ተመልሳ መጥታ ደግሞ ስሚ እኔ ዛሬ በስልክ ከእርሱ ጋር ሳወራ ስለማድር ሁሉም ከተኙ በኃላ ሳሎን ሶፋ ላይ እንደምታድሪ እወቂ ስትላት ካልከፈልሽ አልወጣም፡፡ አለቻት የፈለግሽውን ጠይቂኝ እከፍልሻለሁ ስትላት ወይ የእኔ ማር ላንች ላንድ ለእናቴ ልጅ ምን ያክል እንተጎዳሽ ስለማውቅ አይደለም ሳሎን በረንዳ እደሪ ብትይኝ እንኳን አድራለሁ፡፡ አየሽ ጉዳትሽ እኮ ጉዳቴ ነው፡ እኔ እንኳ በሳምንት ሶስት ቀን ከንፈሬ እሰከሚቀላ እየተሳምኩ በናፍቆት እቃጠላለሁ እንችማ ምን እንደምትሆኝ ሳስበው ታሳዝኝኛለሽሽ፡ ይልቅስ ሳሎን ያለውን ቤተሰብ ልበጥብጥና ቶሎ ላስተኛሽ አንችም ገባ በይና ተካኩለሽ አውሪው እንዴውም በስካይፕ ቪዲዮ ኮል አድርጊናየተጨነቀልቡን ኣሰሪፍ አለቻት፡፡

ይህ በሆነ በ14ኛው ቀን ተፈሪ ምርመራ ተደርጎለት ረቂቅ ብቻ መጥታ ተቀብላው ወደ ቤቱ አመርቶ ሰርጋቸው ያለምንም ውጣ ውረድ እና መንዛዛት የዳግማ ትንሳኤ ሳምንት እንዲሆን ተወስኖ፤ ለሰርግ ዝግጅቱን ከሁለት ቀናት ዕረፍት በሁዋላ አብረው ተፍ ተፍ ማለት ጀምረዋል፡፡

 

ተፈጸመ

 

 ሚያዚያ 15/2012

ሌሊት 12.33 ሠዓት

       

 

                       

 

 

 

No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...