Wednesday, April 15, 2026

አንጭቆረር


ወላጆቼ ሰፈር ሆኖ ከርቀት አንጭቆረርን የሚያሳይ ፎቶ
-------------
የትምህርትአጀማመር---------

የመጀመሪያው ዙር የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ በኢትዮጵያ በ1971 ዓ.ም የተካሄደ፣ መሃይምነትን ለማጥፋት እና ማንበብና መጻፍን ለማስፋፋት የተደረገ ታሪካዊ ዘመቻ ነው። ይህ ዘመቻ አዋቂዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ፣ በማንበብና በመጻፍ ችሎታቸውን እንዲያሳድጉ ያስቻለ ሰፊ እንቅስቃሴ ነበር። ይህ የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ፣ በወቅቱ በነበረው የእድገት በህብረት ዘመቻ ማዕቀፍ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበረው ይህንን እድል በለጋ እድሜያቸው ካገኙ የዚያ ዘመን ህፃናት አንዱ እኔ ነበርኩ፨ ትምህርቱ በቀን በሁለት ዙር ጠዋት ከ 12-2 ሰአት ለአዋቂ ወንዶችና ፈቃደኛ ለሆኑ ሴቶች፤ ማታ ከሆነ ሰአት ገበሬ በሬውን ፈትቶ ወደ ቤት እስከሚመለስበት ሰአት ለእናቶች ይሰጥ ነበር፨ ትምህርቱ ደግሞ ለሁለት ወራት ክረምት ነው የሚሰጠው፤ መቅረት፤ ብዙ ያስቀጣል፨ የትምህርት ፈረቃው ስራን ማዕከል ያደረገ ነበር ወንዶቹ ወደ እርሻ ስለሚሄዱ ጠዋት ይማራሉ፤ እነርሱ እዚያ ሲማሩ ስራ መፍታት የለም በሬዎቻቸው ቁርሳቸውን እየበሉ ለስራ ይዘጋጃሉ፨ እናቶች ደግሞ በማታው ክፍለ ጊዜ ይማራሉ፨ እኔና እኔን መሰል ኩታሮች፤ ከሆዳችን ውጭ ምንም እሴት የማንጨምር (ልጅ በመውለዳቸው ቤተሰብ ደስተኛ መሆናችንን፤ሳይጨምር) በሁለቱም ክፍለ ጊዜ እንድንማር እድል ክፍት ስለነበርን፤እሳት ነበርን

          ተማርልኝ ብዬ ዋሽራ ሰድጄ

          ቀለም ገባው አሉ እሳት ሆነ ለጄ፨ 

ተብሎ እንደተዘፈነላቸው፨

 መሰረተ ትምህርት መማር ለበርካታ ሰዎች እስከዚህ ዘመን፤ ድረስ ስማቸውን  በጣት ሳይሆን፤በእስኪርብቶ እንዲፈርሙ ከማድረግ ባሻገር፤ እኔን መሰሎችን ደግሞ ትምህርት እንጀራችን እንዲሆን አድርጎታል፨ እኔ በሁለቱም ፈረቃ መማሬ ጎበዝ እንድሆን ከማድረጉ ባሻገር በእናቶችና በአባቶች መካከል ያለውን የስራ ክፍፍልና ልፋት እንድገነዘበው ረድቶኛል፨ ነፍሳቸውን በቀኝ ያቁመውና የእኔ ወላጆች ግን እድሜ ለወላጆቻቸው የተማሩ ስለነበሩ፡( ኮሌጅ ግን አልበጠሱም) የዚህ መርሃ ግብር ታዳሚ አልነበሩም፨ ኣባቴ እንዴው በቀጣይ ዙሮች በቀበሌው ያሉትን እንዲያስተምር ተደርጎ እንደነበር አስታውሳለሁ፨ እናቴም ዳዊት መድገም የጀመረች ስለነበር ለመማር አትሄድም፨ በአጭሩ በዚያ ዘመን መረዳቴ የእኛ ቤት የሊቅ ቤት ነበር፨ እናቶች ከሰአት ስለሚማሩ ቶሎ ወደ ቤት ተመልሰው በስራ ሲደክም ለዋለው የትዳር አጋራቸው፤ ለእግሩ ውሃ ለአፉ ጥሬ አዘጋጅተው መጠበቅ፤ ከተቻለም እስከመንገድ ሄድ ብሎ የግብርና ዕቃውን መቀበል ስለሚጠበቅባቸው፡ ልባቸው እቤት እንጂ ትምህርቱ ላይ የለም፨ በዚያ ላይ ሁሉም እናቶች ሲገናኙ ለመጫወት መፈለግ እንጂ ትምህርት ለእነርሱ ትልቅ ዳገት ነበር፨ ምናልባት አንድ ሰአት ከተማሩ ቶሎ ወደቤት ለመሄድ ፤ በተለያዩ ዘዴዎች፤ ኧር ይብቃን ለነገ ያልቅብናልና ትልቅ ዝናብ መጥቷል፡ በተለይ በተጉለት በኩል ሰማዩ ጠቆር ካለ በቃ  አቤቱታ በየመካከሉ ይቀርባሉ፨ የሁሉም ልብ ቤታቸው ነው፤ የደከመ ባልን ከእርሻ፤ ከብት ሲጠብቅ የዋልን ልጅ ከዱር ከነከብቶቹ፤ ለመቀበልና ቀዝቀዝ ያለውን ቤት ሙቅ አድርጎ፤ ምሽቱን ደማቅ ለማድረግ፨  ሴት ነት እኮ ትልቅ ፀጋ ነው፨ ያለ ሴት ቤት በረት ነው የሚባለው በምክንያት ነው፨ በተለይ ደግሞ ሃይለኛ ባል ያላቸው እናቶች አለመረጋጋታቸው አሁንም ፊቴ አለ፨ ሲለቀቁ ሁሉም በሩጫ ነበር የሚሄዱት፨ ትምህርቱ እንዳለቀ ሁሌም ግራ እጅ ወደላይ እየተደረገ መፈክር ይባላል፨ በየቀኑ አንድ አንድ ሰው እንደመሪ ይመረጥና እርሱን ተከትሎ ሌላውም ይላል፨ በዚህ ረገድ እኔና ሌሎች፡ እናቶች፤ የኔን ፋንታ እርሱ ይበል እያሉ እድሉን ስለሚሰጡን፤ በርካታ እናቶችን ተክተን እንላለን፨ እኛ ምንቸገረን ስህተት ብርቃችን አይደል፤ በስህተታችን ሲሳቅ ደስ ብሎን እንስቃለን፨ በዚህ ረገድ ሁሌም የማልረሳው አንድ ታሪክ አለ፨

በአንደኛው ቀን መ/ሩ ሴቶች እናቶች መሪ ሆነው መፈክር ካልተፎከረ አትወጡም ብሎ ድርቅ አለ፨ ሁሉም እናቶች እንቢ አሉ፨ መ/ሩ በሩን ዘግቶ በመስኮት እያየ፤ አልከፍትም አለ፨ በዚህ ረገድ ብዙ መቆየቱ ቤት ውስጥ የሚያመው ጣጣ ያስፈራቸው እትዬ ግርድሽ     ( ነፍሳቸውን ይማር) በቃ እኔ እላላሁ ተከተሉኝ አሉና እጃቸውን አወጡ፨ የመጀመሪያው መፈክራቸው፤ ማይምነት ግቡን ይመታል ሲል ብዙዎችን ስንስቅ መ/ሩ ደንግጦ በሩን ከፍቶ ለቀቀን፨ ለካ እትዬ ግርድሽ ማለት የነበረባቸው ማሃይምነት ይወድማል ነበር፨ እሳቸው ኢሰፓኦ ይሳካል ወይ ግቡን ይመታል ማለት ነበረባቸው፨ መሰረተ ትምህርት በዚህ መልኩ ከፊደል አስተዋወቀንና በዚያ ዘመን ከምተኛበት አጎዛ  ስፋት የበለጠ የምስክር ወረቀት በመስጠት፡ የብርሃን ጎህን ቀደደልኝ፨

1972 ዓም ምናልባት ከብት ስጠብቅ ወይንም ሰፈር ሳውደለድል ከርሜ፤ በ1973 ዓም ላይ ከሰፈራችን የአንድ ሰአት ተኩል ርቀት ላይ እንጭቆረር ከተማ ውስጥ:  ዋዩ 1ኛ ደረጃ፤ ት/ቤት ውስጥ ቀደም ብለው ትምህርት የጀመሩ ፡የቀበሌያችን ልጆች ስለነበሩ፤ ከብዙ ጥያቄና ልፋት ወሩንና ቀኑን በማላውቀው ዕለት ት/ቤት ሄደኩኝ፨ ለምዝገባ ስሄድ መሰረተ ትምህርት ማጠናቀቄን የሚገልጥ ካርድ ይዣለሁ፨  ስለአንጭቆረር ሁሌም ግርም የሚለኘ ነገር አንጭቆረር ድረስ ተብሎ አንጭቆረር፡ የሀገር ቂጥ እንደሆነ ተደርጎ የሚወራው ነገር ነው፨ አንጭቆረር እጅግ በጣም ቢረዝም ከአዲስ አበባ ከ150- 200 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ነበረች፨ አሁን ግን ከተማዋ  አድጋ ተመንድጋ ሳር ቤቶችዋ ሁሉ ወደ ቆርቆሮ ተቀይረው፤ የከተማ ሽታ የሚነፍስባት ከተማ ከሆነች ውላ አድራለች፨ በአንድ ወቅት አንጭቀረር የሚለው ስም ከየት እንደመጣ ስጠይቅ ያገኝሁት ምላሽ እንደሚየዓስረዳው፡ ቀደም ባለት ዘመናት ደገኛኛ ቆለኛው ገበያያ የሚገበያይበት ቦታ ላይ የጤፍ  ሰብል የሚዘራበት ቦታ ሲሆን ጤፍ ሲታጨድ፤ በዚያ ገበሬ መሬት ላይ ሰዎች ሲገበየዓዩ አይቶ  አንች ቆረኔ የገበያ ቦታ ትሆኝ ብሎ ንዴቱን በግርምት ሲገልጽ ( ቆረን ማለት ዋናው ሰብል ታጭድ መሬቱ ላይ የሚቀረው ተረፍ ምርት ማለት ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ እዚያው ስለሚበሰብስ ለመሬቱ ለምነት የራሱ ድርሻ አለው)  እንዴት ይገበያያሉ እያለ ሲቆጣ የዚያ መገበያያ ቦታ የጤፍ ቆረን የሚለው ቀስ በቀስ አንጭ ቆረር ተብሎ፡ የገበየዓ ቦታው ሶቀየር ስሙን ይዞ መጣ ይባላል፨                 

እንግዲህ ያንን የያዝኩትን ሰርትፍኬት የተመለከተ  አንድ መ/ር አይቶ ዜሮ ክፍል ግባ ተባልኩ፨ ት/ቤቱ በሲዳ ርዳታ የተሰራ ህንፃ ሲሆን እጅግ ያማረ ወንበር የነበረው ክፍል ገባሁ፨ ወንበሩ ደብተሮቻችን፤ የምሳ መያዣ ትንሹዋን አገልግላችንን፤ ከፈለግን እኛን ጭምር ከተት ማድረግ የሚችል የውስጥ ኪስ አለው፨ አንድ ወንበር ሶስት ተማሪ ያስቀምጣል፨ የሴቶች ቁጥር ጥቂት ሲሆን ከበሩ መግቢያ ባለው ረድፍ ተቀምጠዋል፨ የመጀመሪያው ረድፍ ላይ የክፍሉ አለቃ የሆነችውና በሁዋላ እንዳወቅሁት የጥበቃው ልጅ የሆነችው፤ ምላሰ ረጂም እንስት፤ ከአንድ እህቷ ጋር ይቀመጣሉ፨ እኔ ት/ቤቱ በገባሁ በማግስቱ አንድ ተማሪ ገባ፡ ልጅ አዲስ በመሆኑ ወንበሩንም ስላላወቀው ሲገባ በሩ ስር ባለው በአለቃዋ እና በአህቷ ወንበር ተቀመጠ፨ በዚህ ጊዜ ክፍሉ በሳቅ ተቀወጠ፡ እንደፈለጋቸው እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው፤ አለቃዋና እህትዋ ከክፍሉ ወጭ ስለነበሩ ለምን ሳቃችሁ ብለው ሊቆጡን ሲገቡ ልጁ ወንበራቸው ላይ ተቀምጧል፨ ምድር ቁና ሆነች፨  አለቃዋ እና የጥበቃው ልጅ ወንበር ላይ ካለእርስዋ ፈቃድና እውቅና ሌላ ሰው ተቀመጠበት፨ ስሙ ተጠይቆ በረባሽነት ተፅፎ በደሉ ተዘርዝሮ ለጥበቃው፡ ለአለቃችን አባት ተሰጣቸው፨ የሚያውቁትን የምት አይነት ጎማ ጫማ በተጫማ እግራቸው፤ በእጃቸው፤ አልስታውስም እንጂ በጥርሳቸው ጭምር ተደበደበ፡ ያ ልጅ ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ የት/የቤቱን ደጃፍ አልረገጠም፨ ጥበቃው አቶ ተካ፤ ልጃቸው ደግሞ መርሻ ትባል ነበር፨ እኔ የገባሁ ቀን አንድ መ/ርም ሊያሰተምረን አልገባም ዘፈን ብቻ ሆኖ ዋለ፨ ይህው ድርጊት ለአንድ ሳምንት ሲቀጥል እንቢ ብዬ ቀረሁ፨ አንዲት ዘመዴ መ/ርት ስለነበረች ችግሩ ተነገራት፤በቃ ይምጣ እኔ አንደኛ ከፍል አስገባዋለሁ አለች፨  በዚህ ጥሪ መሰረት ወደ ት/ቤቱ አቅንቼ እኔ ሆዬ ማንንም ሳላማክር 1ኛ ክፍል ትማር ከነበረችው የአጎቴ ልጅ በለጡን ተከትዬ  1ኛ ክፍል ስገባ የመጀመሪያው መንፈቀ አመት ፈተና እየተሰጠ ነበር'፤ ፈተናውን ተፈተንኩ፨ መልሴ ለሁሉም አይነት ጥያቄዎች እውሸት የሚል ነበር፨ 8/100 አመጣሁ፨ ሲገባኝ የመጀመሪያዎቹ 10 ወይም 5 ጥያቄዎች እውነት ወይንም ውሸት በል የሚል ትዕዛዝ ስላላቸውን ነው መሰል፤ ከእውነት እ ን ከውሸት ደግሞ ሙሉቃሉን ወስጄ እውሸት ብዬ ለዳሽ ሙላውም፤ ለምርጫውም የመለስኩት፨ 

ይቀጥላል




1 comment:

  1. የመሰረተ ትምህርትና የአንደኛ ደረጃ ትውስታህን ወድጄዋለሁ። በዚሁ ቀጥልልን።

    ReplyDelete

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...