Saturday, July 5, 2025

 

                                          አ-ፈ-ወ-ር-ቅ

ምንም፤እንኳ ነሰነሰችው ተብሎ ከሚወራላቸው እንስቶች መካከል ባትመደብም ፤ጥቁር ሆኖ ከትከሻዋ ለመውረድ እየሞከረ ያለውን ጸጉሯን ለመንከባከብ፤ቦዝና አታወቅም፡፡ ልጄ የሴት ልጅ ውበቷ ጸጉሯ፤ ነው ጸጉርሽን በደንብ ተንከባከቢው አንች ምግብ እንደምትመርጭው ሁሉ ጸጉርሽም ቅባት ይመርጣል፡ የሚስማማውን መምረጥ ግዴታሽ ነው፡፡ እኔ እናትሽ፤ አለኝ ብዬ የምኮራበት አንጡራ ሀብቴና ውበቴ ጸጉሬነው፤ የሚለው የአክስቷ ንግግር ትክክል መሆኑን መረዳት፤የጀመረችው የሁለተኛ ደረጃ /ቤት በራፍ እንደረገጠች ነበር፡፡ አክስቷ ባሳለፉት ዘመናት ሁሉ ጸጉራቸውን ምንያክል ይንባከቡት እንደነበር አሁን ያለውን የጸጉራቸውን ሁኔታ በመመልከት ማንም መገመት ይችላል፡፡ አንዳንዶች በወጣትነት ዘመናቸው ምን ዓይነት ይሆኑ እያለ፤ የመነጋገሪያ ርዕስ ያደርጋቸዋል፡፡ ሰብለ ከቤቷ፤ ተነስታ ወደ ምትማርበት የግል ኮሌጅ እስከምትደርስ ድረስ ቢያን 5-10 የሚደርሱ ጸጉሯን የሚያደንቁ ሰዎች አታጣም፡፡ አንዳንዴ አድናቆቱ የሚመጣው ከሴቶችና በዕድሜ ገፋ ካሉ አካላት ጭምር በመሆኑ የለከፋ እንዳልሆነ ከገባት ሰነባብቷል፡፡ ይህንንም ሰፊ አድናቆት በማግኘቷ በውስጥዋ የሚሰማት ደስታ ወደር የለውም፡፡ ዕለት ዕለት በራስ መተማመንና አልሸነፍም ባይነትንም እየጨመረላት ስለሄድም በትምህርቷ ጎበዝ ብለው ከሚጠሩት ተርታ ተመድባለች፡፡ ምንም እንኳ ያሉዋት የክፍል ጓደኞቿ እርሷን የመሰሉ ቀለሜዎች ባይሆኑም የእርሷን ጓደኝነት ስለሚፈልጉት በእርሷ ፕሮግራም መመራት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ ይህንን ማድረግ በመቻሉዋ ደግሞ መምህራቿ ጭምር ደስተኛ ሆነዋል፡፡ ቱሪዝም በኢትዮጲያ የሚለውን ኮርስ የሚሰጠው ወጣቱ / አፈወርቅ በዚህ ተግቧሯ ከሚያደንቁዋት /ራን መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ / አፈወርቅ፤ ከተመረቀበት ሙያ በሻገር በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ትምህርት ሰፋ ያለ እውቀት እንዳለው የኢትዮጲያ የመስህብ ቦታዎች ሲገልጽ ከሚጠቀማቸው አገላለጾችና ለዛዎች ውስጥ ብዙዎች ቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያን ይሸታሉ፡፡ ምንም እንኳ የሀገራችን ታሪክ ከቤተክርስቲን ታሪክ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሆኖ በተለያየ መልክ ብንማረውም የመምህር አፈወርቅን ለዛና ቋንቋ ተጠቅሞ ግን ለማስተማር የቤተክርስቲኒቱን የውሰጥ ሚስጢር ማወቅ የሚጠይቅ ይመስላታል፡፡ ሰብለ ምንም እንኳ በሁሉም ትምህርቶች ጎበዝና ሁሉንም በእኩል የምታይ ቢሆንም በመ/ አፈወርቅ ትምህርት ግን በጣም ትመሰጣለች፡፡ ትምህርቱን ተምሮ ትልቁን ውጤት ከማስመዝገብ ባለፈ፤ እኔ ማነኝ የሚለውን ጥያቄ ሁሌም እንድታስብ ያደርጋታል፡፡ ኢትዮጲያ እንደሀገር ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የገዘፈ ምን ታሪክ አላት፤ ቤተክርስቲንን ከኢትዮጲያ ብንለይ ኢትዮጲያ ሚለው ስም ለዚች ሀገር ይሰፋታል፡፡ ታሪኬ ነው ብላ ለዓለም የምታወራውና የምትሳየው ሁሉ የቤተክርስቲያን ነው፡፡ በርግጥ ኢትዮጲያም የቤተክርስቲያን ነች ቤተክርስቲያንም እንደዚያው፡፡ ሰብለ የመ/ አፈወርቅን ኮርስ ከመከታተል ባለፈ ኢትዮጲያ ስለምትባለው ሀገር ለማወቅ ሊረዳት የሚችል መሆኑ ስለገባት አንድ ቀን ጊዜ ወስዳ ልታናግረው ወስና የድፍረት አቅም እያሰባሰበች ትገኛለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህንን መሰል ባህሪዎቿ ፤በዚህ ዘመን ካሉ ደፋር ሴት ተማሪዎች ለየት ያደርጋታል፡፡ ምንም እንኳ፤የፍርሃት ስሜቶች በውስጧ ባይኖሩም ለመምህራኖቿ ያላት ከበሬታ ግን ወደር የለውም፡፡ መምህር የቀለም አባት ነው፡ እኛ ወለድንሽ / ግን የምታይበትን አይንሽ አበራልሽ፤ነገ እንድታይ አደረገሽ…… ሰብለ ይላሉ ወላጆቿ፡፡
 
አየሽ ሰብለ በቤተሰባችን ውስጥ በተለይም በእናቴ ወገን በክርስትናው በኩል ጠንከር ያለ ይዞታ ነበር ልልሽ እችላለሁ፡፡ ቅድመ አያቴ ሰባት ወልደው ያደገላቸው እናቴ አባት ብቻ ነው፡ እርሱም እናቴን ብቻ እንደወለደ 36 ዓመቱ ይህችንን ምድር ተሰናበታት፡፡ ሰባት ወልደው የልጅ መና የሆኑት ቅድመ አያቴም በጉዳዩ አእምሮዋቸው ስለተነካ ለሰባት ዓመታት ቀውሰው ይህችን ምድር ተሰናበቷት፡፡ የወንድ ቅድመ አያቴ ወንበር ዘርግተው ኢትዮጲያዊው ትምህርትን ከመላው ኢትዮጲያ፤ለሚመጡ ተማሪዎች በዓመት ሃምሳ ብር እየተከፈላቸው ሲያስተምሩ የነበረ ሲሆን የነበረቻቸውን ብቸኛ የልጅ ልጅ እናቴንም እስከ ዳዊት ድረስ እንድትማር አድርገዋት ረዳት መምህራቸውን እስከመሆን አድርሰዋት ነበር፡፡ ወንዱ ቅድመ አያቴ ትምህርታቸውና እምነታቸው ላቅ ያለ ስለነበር የሚደርስባቸውን ፈተና ሁሉ ለአምላክ አሳልፈው እየሰጡ፤ በጸሎት ጭምር በመትጋት ኖረው፤ የሚወዷቸው ባለቤታቸው ከሞቱ አምስት አመታት በኋላ እርሳቸው ይህችን ምድር ተሰናበቷት፡፡ ቅድም አያቴ በጣም ጥልቅ የሆነ ሃይማኖታዌ፤ ሰው ስለነበሩ አንዳንዶች ሲያወሩ እንደሰማሁት ሊደርስባቸው ያለውን ነገር ቀድመው ስለሚያውቁት ነገሩ ሲደርስ ብዙም እንግዳ አይሆንባቸው ነበር ይላሉ፤ ስለማላውቃቸው ብልሁ ቅድም አያቴ የምሰማቸው ወሬዎች፡፡ ቅድም አያቴ ዘወትር የሚጨነቁት እውቀታቸውን ተቀብሎ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የሚችል ወንድ ልጅ ስላልነበራቸው እንጅ በሌላ በምንም ጉዳይ አልነበሩም አሉ፡፡ ይህንን ጭንቀታቸውን ለመቅረፍ ይመስላል ብቸኛ የሆነቸውን የልጅ ልጃቸውን ብዙ ያስተማሩዋት፡፡ ይሁን እንጂ ከትልቅ ዘር መወለዱዋ፤ ለጋብቻ የሚፈልጓትና ዘወትር ደጅ የሚጠኑ አካላት ስላሉ፤ ልትገፋበት እንደማትችል ይገምታሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ዘር የማስቀጠሉ ኃላፊነትም ለዚችው ብቸኛ እናቴ የሚሰጥ ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ሊኖር የሚችለው አማራጭ መማርና ማስተማር ግብሩ ሆኖ በወንበራቸው ተቀምጦ ማስተማር የሚችል ባል መፈለግ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአመታ በፊት በውስጣቸው ያጩት፤ ወደ ቅስና በማምራት ላይ ያለውና ፈጣንና ድምጸ መረዋ የሆነው አባቴን ነው፡፡ አለቃ ወልደ አብርሃም ሁሉም ተማሪዎቻቸውን በእኩል አይን የሚመለከቱ ቢሆንም በዚያን ዘመን የእርሳቸው ተማሪዎች የነበሩ ሲያወሩ እንደሰማሁት ለአባቴ ግን የነበራቸው ክብር ከሁሉም ይልቃል ይላሉ፡፡ ይህም ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን በአባቴ ጎበዝ መሆንና ለመቀደስና በድምጽና በዜማ ለሚባሉ ትምህርቶች እጅግ የተገራ ድምጽ ስለነበረው ነው፡፡ አባቴ ከድምጽ ባሻገር መልክና ቁመናው ካለው መልካም ስነምግባር ጋር ተዳምሮ፤ ማንም ሰው ሊመርጠውና ሊወደው የሚችል ነው፡፡ መቼም ለአባትህ አዳለህ እንማትይኝ እርግጠኛ ነኝ አለ፤ እቀዘቀዘ ያለውን ማኪያቴ ፉት እያለ አፈወርቅ፡፡ ሰብለ በምትሰማው ነገር በጣም ተመስጣለች፡፡ የአፈወርቅ ንግግር ለዛው የአተራረክ ብቃቱ ቃላት አመራረጡ በጣም መስጧታል፡፡ እንዴ ልጃቸው እንደዚህ የሆነ ብዙ የሚወራላቸው አባትም ምን ያክል ውብና ብስል ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመትም አልከበዳትም፡፡ እናልሽ አንድ እሁድ ቀን ቅድመ አያቴ ወላጅ አባቴን ወደ እርሳቸው የጸሎት ክፍል ይጠሩና አንድ ትልቅ ሚስጢር ያዋዩታል፡፡ አባቴም በሰማው ነገር በጣም ግራ ይገባና፤ እግራቸው ስር ወድቆ በለቅሶ ይለምናቸዋል፡፡ ልጄ ገብረመስቀል/ በክርስትና ስሙ እየጠሩት/ ይህ ኃሳብ ነው፤ እግዚአብሔር ከፈቀደና ከወደደው ይሆናል፡፡ እርሱ ፈቃድ ካልሆነ ግን በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ እርሱ የማይሆነን አይሰጠንም፡፡ ሊሰጠን ሲያስብ ደግሞ ባልጠበቅነውና ባለሰብነው መንገድ ነው፡፡ ልጄ ኃሳብክን አከብራለሁ፤ ከቃልህም አልወጣም አንተም በነገርኩህ ሃሳብ ሳትደናገጥ፤ለማንም ሳትተነፍስ እስኪ ሱባዔ ያዝበት፤ ፈጣሪ ምን ይላል የሚለውን ስማበትና ለአስተርዮ ተገናኝተን እንወያያለን፡፡ በል እግዚአብሔር ይባርክህ ይጠብቅህ፤ሃሳብክንም ይሙላል ብለው ጸሎት አድርገው ባርከው ይሸኙታል፡፡ ይህንን ያጫወተኝ ወላጅ አባቴ እኔ ማግባት እንዳለብኝ ሲመክረኝ ነበር አለና አሁንም ማኪያቶውን ፉት ማለት ጀመረ፡፡ ሰብለ ግን እርግጠኛ ነሽ ምንም ነገር አላስነካሽኝም፤ አላት ሰብለ በንግግሩ ግራ ተጋብታ ማለት ምን አረ እኔ እያለች አንዴ እጇን አንድ ጊዜ ደግሞ እግሯንና መላ አካልዋን መመልከት ጀመረች፡፡ አፈወርቅ እየሳቀ ማለቴ እንደዚህ አይነት ጉዳዮችን የማወራው በጣም ቅርብ ለሆኑ ሰዎች ነበር ዛሬ ግን ነገሩ ስላልገባኝ ነው፤ አላት፡፡ ውይ ቲቸር እኔ ምንም አላስነካሁህም ምንም ነገርም አላውቅም ግን እንደዚህ ብለህ ታሪኩን ላለማንገርና በዚህ ለማቆም ፈልገህ ከሆነ ግን በጣምነው የማዝነው፤እጅግ የሚመስጥ ታሪክ ነው፤ እባክህ ጨርስልኝ በማለት ልመና ገባች፡፡ ኖኖ በፍጹም አላደርገውም ተልዕኮሽ ምን እንደሆነ ሳላውቅ ከዚህ በኋላ አንዲትም ቃል አልናገርም፡፡ ምንድነው ከእኔ የምትፈልጊው ማነው የላከሽ፤ እንዴትስ ነው በቀጠርሽ ቦታና ሰዓት ልገኝ የቻልኩት፡፡ ተማሪዎቼን አከብራለሁ፤ ፍላጎታቸውን አውቄ ለማሟላት እጥራለሁ ግን ይህ ተለየብኝ፤ ያለነው እኮ አንች ወላጆች ቤት ነው፡፡ እያለ መናደድ ጀመረ፡፡ ሰብለ ግራ ገባት አጇ ላብ በላብ ሆነ መልአክ የነበረው አፈወርቅ ወደ ሰይጣን ለመቀየር ብዙ አልፈጀበትም፡፡አረ በማርያም፤ በእግዚአብሔር ቲቸር እኔ ማንም አላከኝም፤ምንም ኃሳብም የለኝም፤ ሰብዕና በጣም ስለማረከኝኛና ሞዴል አድርጌ ስለማይህ ጭምር ነው እንጂ ለሌላ ለምንም አላማም አይደለም፡፡ እባክህ ተረዳኝ፤ እያለች ቆማ ለመነቸው፡፡ መርበትበቷን ያየው አፈወርቅ በሳቅ ሊፈነዳ ምንም አልቀረውም፤ አንች እንደዚህ ፈሪ ነሽ እንዴ ምንድነው፤ እንደዚህ የሚያደርግሽ፤ በጣም ጠንካራ ትመስይኝ ነበር፤ በይ ቁጭ በይ እኔ ስቀልድሽነው፡ ብሎ እንድትቀመጥ ወደ ሶፋው ሲጋብዛት ጠረኑዋ በአፍንጫው ገባ፡፡ ሰብለ እንባዋቿ መንታ መንታ እየሆኑ መውረድ ሲጀምሩ አፈወርቅ ብርክ ያዘው ወትሮም የሴትን ልጅ እንባ ማየት የማይወደው፤ሰውዬ በሰው ቤት መጥቶ የሰው ልጅ ማስለቀሱ ግራ ስለገባው በተራው ልመና ገባ፡፡ እባክሽ ሰብለ እኔ ውሸቴን ነው፡፡ ለቀልድ ነው አንች ቀልድ አታውቂም እንዴ እያለ አጠገብዋ ተቀምጦ ትከሻዋን ሲዳብሰው፤ ሰብለ የበለጠ መንሰቅስቅ፤ጀመረች፡፡ አፈወርቅ ቀስ እያለ ትከሻዋን፤ እየመታታ ከለቅሶ ልትወጣ በሚያደርገው ጥረት ሰብለ ሳታስበው አፈወርቅ ደረት ላይ ተለጥፋ ቀረች፡፡ የትንፏሻ ሙቀት ወደ ውስጡ ሲገባ ግራ ተጋባዋ አፈወርቅ መቀመጫ ሊቀይር ሲያሰሰብ ከውስጠኛው ክፍል ሰብልዬ ትቻችሁ ጠፋሁ አይደል የሚል ሰብለ እናት ድምጽ ተሰማ፡፡
                           ተሰማ፤ ተሰማ የእማማ ድምጽ ተሰማ
                                 ሰብልዬ እያለ እየተጣራ፡፡
                                 to be continued....

 

 

No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...