Tuesday, June 21, 2022

የወለጋ ምድር

 

በንጹህ፡አማራ ደም የጨቀየችው የወለጋ ምድር

የሰውልጅ፡ ከተሰጡት ቀላልና ተራራ መብቶች ወይንም ስጦታዎች አንዱ በህይወት የመኖር መብት ነው፡፡ በበርከታ ሀገራት ፤ የእኛኝ ሀገር ጨምሮ ለበርካታ እንሰሳት ተቆርቋሪ ማህበር በስማቸው ተቋቁሞላቸው የአለም፤ የአፍሪካ እየተባለ ቀን ሳይቀር በስማቸው ተሰይሞ ይከበርላቸዋል፡ በሚደርስባቸው ጥቃት አደጋ ያንዣበበባቸው ናቸው ተብሎ፡፡ በኢትዮጲያ ሰማይ ስር ለሚኖረው አማራ ግን ፡ እንኳን መብቱ እንዲሟላለት የሚሰራ ቀርቶ ተፈጥሮ የሰጠችውን የመኖር መብት፡ የሚገፍ፤ሲገፈፍም ለማስከበር ህግን ጠቅሶ የሚሞግት፡ አካል የለም፡፡ ስሙ በችግር ጊዜ ከአፋቸው የማይጠፋው ባለስልጣነት ቀርቶ በስሙ ተወክለው ፓርላማ የገቡ አካላት አንድም ቃል አለመተንፈሳቸው ግራ ያጋባል፡፡ አማራን ወክለው ተወካዮች ምክር ቤት የተቀመጡት ጥቂት የአብን አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የገዥው ፓርቲ አባላት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ወለጋ የሞተው አማራ ጉዳይ አይገዳቸው ነበርን? ወይስ እነርሱ ይህንን ጥያቄ እንዲደግፉ ከመጡበት ሰፈር ሰው መገደል ነበረበት? ይህ ጉዳይ በርግጥ ለአማራ ተወካዮች ብቻ ሳይሆን ለአፈጉባኤው ጭምር ጉዳያቸው ሊሆን በተገባ ነበር? የህዝብ ተወካይ ነኝ ብሎ የሚያወራ አካል ከዚህ የበለጠ በህዝብ ላይ የሚደርስ ምን ችግር ይመጣል ብለው ነው፡ በችግሩ ላይ ለመነጋገር ያልደፈሩት? ብሔሩንም፤ሃይማኖቱንም የተገደለበትን ቦታ እንርሳው የሚያስማማን ሰው የተባለ ፍጡር፤(ምንም የማያውቁ ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በተከበረው የእምነት ቦታ) በአሸባሪም ይሁን በኢመደበኛ አካል ባልተገባ መልኩ ተገድሏል፡፡ ስለዚህ የህዝብ ተወካይ የሆነ ሁሉ እንዴት ይህንን ድርጊት ለመኮነን ስለአጀንዳ እና ፕሮቶኮል ይጨነቃል?

የሚገርመው የሚወጡት መረጃዎች ናቸው፡፡ “የሚደርሰበትን ምት ያልቻለው ኢመደበኛ አደረጃጀት በንጹሃን ላይ የሞት አደጋ አድርሷል” መባሉ፡፡ እንዴው ይህንን ምት ያልቻለው አካል፡ዘርና ሃይማኖትን ለይቶ ጉዳት ሲያደርስ ምቱን እንዴት ተቋቋመ? እየሸሸ ከሆነ ዘርን፤ሃይማኖትን ለመምረጥ እንዴት ቻለ? ወይስ በዚህ በኩል ሸሽ እዚያ ቦታ ላይ እነዚህ አካላት አሉልህ ተብሎ መረጃ ደረሰው? ወይስ ምት አድራሹ አካል ከሚፈልገው ቦታ ካባረረው በሁዋላ ወደ ሁዋላ ተመለሰ? በምንም መመዘኛና መስፈርት የሚወጡት መረጃዎች ውሃ የሚቋጥሩ አይመስለኝም፡፡

ይህ ድርጊት ሲፈጸም አማራን ወክሎ የተቀመጠው ተወካይና ባለስልጣን ወለጋ ወይንም ቤንሻንጉል ሄዶ እንዲዋጋ አይጠበቅበትም፡ ግን ጉዳዩን እንደሀገር በአጀንዳነት ተይዞ እልባት እንዲሰጠው ማድረግ ቀላሉ ስራው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

በአንድ ወቅት የቀደሙት፡ የሕወህት ባለስልጣናት ከሻቢያ ጋር በትግል ሜዳ እያሌ በሃሳብ ሲለያዩ ከመካከላቸው አንዱ “ዛሬ እናንተ ወደላይ ወጥታችሁዋል፡ እኛ ለጊዜው ወደታች ወርደናል፡ ግን ጊዜ ተገልብጦ እኛ ወደላይ እናንተ ወደታች ስትወርዱ መንገድ ላይ እንገናኝ ይሆናል የሚል መንፈስ ያለው ንግግር ተናገርናቸው” ሲሉ አስታወሳለሁ፡፡ እናም የዛሬ ባለጊዜዎች ይህ ጊዜ እንደነበር አይቆም፤ ሁሉም ጊዜ አለው ያኔ ታዲያ የዛሬ አልቃሾች አስለቃሾች የማይሆኑበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አይኑ እያየ ወላጆቹን ያጣ የዛሬ ህጻን፡ የሚወዳቸውሁሉ አይኑ ፊት ያጣ አባት በምን ይቅርታ ነው ልቡ የሚጽናናውና ከበቀል የሚታገሰው፡፡ ቆምና ረጋ ብለን፡ እናስብ፡፡ በዜጋቸው ላይ ግፍ ሰሩ የት ነበሩ ብለን ወደሁዋላ ዞር ብለን እንመልከት፡፡ ኢዲያሚን ዳዳ፤ አልበሽር…….ሌሎችንም፡፡ 

በክቡር የሰው፤ ልጅ ደም የጨቀየች ምድርስ የምታበቅለው እህል ምን ያክልስ ለነዋሪ ጤነኛ የሆነ አዝርዕት ተሰጥ ይሆን፡፡ ይህንን ያዩ አይኖች ወሬውን የሰሙ ጆሮዎችስ ምን ያክል ይጎዱ ይሆን፡፡ ልጆቼን ሳያቸው አዝናለሁ በለጋ እድሜያቸው ይህንን የመሰለ፡ ከባድ ነገር ሲሰሙ ምንያክል ውስጣቸው ይጎዳ ይሆን እያልኩኝ፡፡

ሰኔ 14/2014 አዳማ

No comments:

Post a Comment

                             ገበር አምባ                    ስራ ፈቶ ሲያሽ ያንች ተመልካች                       በውበት ቁንጅና ማን ነበር እንዳንች፡፡          ...