ትዝታ ዘ ፋሲካ
የ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ መካነ አእምሮ ከገባሁበት አመት አንስቶ ላለፉት
በርካታ አመታት፡ ፋሲካንና ቀጣዮቹን የትንሳኤ ሳምንታት በተወለድከቡት አካባቢ፤ የማሰለፍ አጋጣሚውን አግኝቼ አላውቅም ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ፋሲካን ተከትሎ፡የሚመጣው የሩር(ቅሌ)፡ ወይንም የገና ጨዋታ፤ አክፍይ ተይዞ ከቦታ ቦታ የነበረው፤ እንቅስቃሴ፡ በቅርቡ
የተጋቡ ባለትዳሮች ብቻቸውን ወይንም የመጀመሪያ ልጃቸውን አስከትለው ወደ ሴቷ ወላጆች ዘንድ ለበአሉ የሚያደርጉት ጉዞ፤በፈረስ የሚደረጉ
ሰርጎችና መሰል የበኣል ክዋኔዎች ግን ያደኩበትን ቦታ ሳስብ ከውስጤ አይጠፍም፡፡ ዘንድሮም ወደ ተወለድኩበት ቦታ ሳቀና እነዚያን
ክዋኔዎች ለማየት ጉጉቴ ከባድ ነበር፡፡ ግን ምንም እንኳ ብዙዎቹ እንዳሉ ቢሆንም የተወሰኑት ግን ተለውጠዋል፡፡
በእኔ ዘመን ወጣቶች ሜዳ ወርደው ሜዳና እርሻ ውስጥ የሚጫወቱት የቅሌ ጨዋታ ቀርቶ በእግር ኳስ ጨዋታ ተተክቷል፡፡ ከባህል አንጻር ቅሌ መጥፋቱ የሚገድ ቢሆንም በእግር ኳስ መተካቱ ግን ጥሩ ይመስለኛል፡፡ በቅሌ ጨዋታ ወቅቱ፡ ብዙ ድብድቦች፡ ቅሌው፡ ከሮ ሲመታ አይን ላይ ወይንም ሌላ አካል ላይ ካረፈ የሚሰከትለው ጉዳት፡ አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ለበአል የተዘጋጀውን መጠጥ ቀማምሰው በመምጣት አግባባዊ ባልሆነ መልኩ ሲጫወቱ ከሚያደርሱት ጉዳት፡ አንጻር መቅረቱን ወድጀዋለሁ፡፡ ይህ ጨዋታ ህግ ተሰርቶለት ከባህላዊ ጨዋታ ተርታ ተመድቦ የገና ጨዋታ ተብሎ ስለታቀፈ ጨዋታዋ የመጥፋት እድሉ አነስተኛ ነው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ለመልስና ለአክፋይ የሚሄዱ ሰዎችን ግን አልተመለከትኩም፡፡ ምናልባት በመጀመሪያ ሳምንት በርካታ ሰርጎች በመኖራቸው የተነሳ፡ ወደ ቀጣይ ሳምንታት የተሻገረ ይመስለኛል፡፡ በታደምኩበት የሰርግ ስነስርዓት ላይ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ አብረውኝ የተማሩ በርካታ አቶዎችንና ወ/ሮዎችን፤ በስም ብቻ የማውቃቸው ዘመዶቼን፡ ማግኘት በመቻሌና የልጅነትና የት/ቤት ትዝታዎቻችንን አንስተን መጫወታችን እጅግ ደስተኛ እንድሆን አድርገውኛል፡፡ ምንም እንኳ እኔ በታደምኩበት የሰርግ ስነስርዓት ላይ ተኩስ ያልነበረ ቢሆንም ማታ ግን ከተለያዬ አቅጣጫ በርካታ ተኩሶች ይሰሙ ነበር፡፡ ሁሉም ግን የደስታና ከሰርግ ስነስርዓቱ ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ በጎጅነቱ ላይ፡ ከጥቂት ሰዎች ጋር ስናወራ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ እጅግ በጣም የሚገርመው አንድ ጥይት( ተተኳሽ) ዋጋው ከመቶ ብር በላይ ሆኖ እንኳ መተኮስ ጨመረ እንጅ አልቀነስም፡፡ ይህ እጅግ ሊወገዝና ሊቆም የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ከጥይት ተኩስ ጋር በተያያዘ ስራ በያዝኩበት አመት አንድ የዚያ ዘመን ቅርብ ተመራቂ የነበረና ከጎጃም አካባቢ የመጣ የስራ ባልደረባ ስለምርቃት ትዝታዎቻችን ስናወራ፡ አጎቱ ለእርሱ ምርቃት ከመደሰታቸው የተነሳ 9 ጊዜ እንደተኮሱለት ሁለቱን እርሱን እንዳስተኮሱትና እኛን አጎቱን ትልቅ ውለታ እንደዋሉት በኩራት ሲነግረኝ የሳቁትን ሳቅ ዛሬም አልረሳውም፡፡ይሁን እንጂ አላስፈላጊ በሆነ መልኩ ጥይት በመተኮስ ሰላምን ከማደፍረስ ባለፈ በኢኮኖሚ ላይ ጫና የሚፈጥረውን ተኳሽን ግን አስተምረንም ካልሆነ ህግ ፊት አቅርበን እንዲማር ካላደረግነው ጉዳቱ የጋራ ነው፡፡
በቆይታዬ፤ ድሮ ልጅ እያለሁ ለሆሳዕና ገበያ ወደ እነዋሪ ገበያ ከዋዜማው ጀምሮ በሰፈራችን ስለሚጓጓዙት ቅልብ በሬዎችም አንስተን አውርተናል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ስንጋ በሬዎችን በእግር ማጓጓዝ ቀርቶ በመኪና እንደሆነ ስምቻለሁ፡፡ ስለጅሩ በሬ ስናወጋ ዋጋውን ከፍተኛ መሆን አንስቼ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ በነበረን ውይይት፡ ገበሬው ድካሙን ሳይቆጥር፡ በሬወን ለማድለብ የሚያወጣው ወጭ፡ በሬው የተገዛበት ውጭ ሲደመር፡ ድካሙን ሳይጨመር አሁን የሚሸጥበት ዋጋ ኪሳራ ነው፡፡ ከዚያ አልፎ አደልቦ በሬ የሸጠ ሰው መልሶ የእርሻ በሬ ስለሚገዛ ኢኮኖሚያው ጥቅሙ በደንብ ሲሰላ ገበሬው አትራፊ አይደለም፡፡ ይህንንም በርካታ ሰዎች የተረዱት ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ አመታት፡ እንደከዚህ ቀደሙ በእህልን የደለቡ በሬዎችን ላናይ እንችላለን፡፡ የየወረዳዎች ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤቶችን ዋጋ ከመዘገብ ባለፈ የገበያያ ትስስር የመፍጠር፤ ወጭ ቆጣቢ የሆነ የከብት ማድለብ ልምድ ለገበሬው ሊያጋሩ ይገባል፡፡
ከደብረብርሃን ጅሁር፡ለበርካታ አመታት ይሰራል እየተባለ ሳይሰራ የቆየው የአስፓልት መንገድ
በታሰበውና መሆን ባለበት ፍጥነት፡ እየተሰራ ባይሆንም ከዞኑ ርዕሰ ከተማ እስከ 42 ኪ.ሜ ድረስ የጥርጊያውና የቆረጣ ስራው ተጠናቅቋል፡፡
መሬቱ ሜዳ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ግን ፕሮጀክቱ ስራ ከተጀመረበት አንስቶ 50 ፐርሰንቱ እንኳ አለመሰራቱና በቀጣይ ደግሞ በክረምቱ፡
ምክንያት ስለሚቋረጥ አሁንም መንገዱ ቶሎ እንደማይጠናቀቅ መረዳት ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ትልቁ የጫጫ ወንዝ አሮጌው ድልድይ
መነካካቱና እርሱን የሚተካው አዲስ ድልድይም ስራ አለመጀመሩ፤ ድንገት አሮጌው ድልድይ ችግር ቢገጥመው ምንም የአፈር ማዳበሪያ ያላገኘው
የጅሩ ገበሬ በቀጣይ ሌላ ፍዳ እንዳይገጥመው ስጋቴ ከፍተኛ ነው፡፡
ከደነባ በታች ያለው መንገድም በቅርቡ ከክረምት መግባት ጋር ተያይዞና አፈሩ ጥቁር ሆኖ ስራውን ከባድ ከማድረጉ አንጻር፡ከሚቀጥለው አመት ከጥቅምት ወር በፊት ያኔም በመንገዱ ግራና ቀኝ የሚኖረው አዝመራ ካላስቸገረ ይጀመራል ተብሎ አታሰብም፡፡
ከመንገዱ አለመመቸት፤ ከበኣል ጋር በተያያዘ፤የሰዎች እንቅስቃሴ በመበራከቱ የፍስክ ወር ከመሆኑ አንጻር፤በርካታ የሰርግ ስነስረአቶች በመኖራቸው፡ በፈለጉ ሰዓት ቀርቶ ቀኑን መሉ መኪና ማግኘት እጅግ ከባድ ነው፡፡ በከተሞቹ መናኸሪያዎች በርካታ ተሸከርከርካሪዎች ቢኖረም ብዙዎቹ ዲኮር ተደርገው የሰርግና ባህላዊ ዘፈኖቻቸውን ከፍተው፡ ሰርገኞችን ብቻ ይዞ ለመሄድ እንጅ ለመንገደኛ ተደራሾች አይደሉም፡፡ በስምሪት ላይ ያሉ ባለሙያዎችም ችግሩን ለመፍታት ፍላጎቱና አቅሙ እንዳልነበራቸው ማንም መገመት ይችላል፡፡
ለማንኛው ለበርካታ አመታት ተለይቸው የነበረውን የፋሲካ በዓል፤ሰርግና መሰል ተግባራትን በዚህ
አመት መሳተፍ በመቻሌ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡
No comments:
Post a Comment