Wednesday, June 3, 2026

 

                                                             እኔና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ

 ለስራ በተመደብኩበት ወረዳ ውስጥ ከተመደብኩበት መደበኛ ስራዬ ውጭ፤ ቤተክርስቲያንን ባለችኝ አቅሜ አገለግላለሁ፤ እገለገላለሁም። ልጅ ሳለሁ በትወልድ ቦታዬ ከአዲስአበባ ለበላት እየመጣ፤ ከካህናት ጋር በቤተክርስቲያን ተገኝቶ፤ የሚያገለግል አጎ ይህንን  ፍቅር ስላሳደረብኝ፤ የእኔም የእናቴም ምኞት ትልቅ ስሆን ልክ እንደጋሸ ሸዋዬ ቤተክርስቲያንን ማገልገል ነበር ጋሸ ሸዋዬ የእናቴ አብሮ አደግ የአክስቱዋ ልጅ ሲሆን የቤተክርሰቲያን ትምህርትም ህግም በዲፕሎማ ደረጃ የተማረና በንጉሱ ጊዜ ትልቅ ቦታ ደርሶ ሀገርን ያገልግል የነበረ፤ በደርግ ስርዓትም በጥብቅና ሙያ ትልቅ ቦታ ያለው ከልብ የምንወደው አጎታችን ነበር። እናቴና ጋሸ ሸዋዬ ፍቅራቸው በጣም ጥልቅ ነው። ከአባት የሚወለዱ በርካታ ወንድሞችና የወንድም ልጆች እያሉት ከሁሉም ግን የሚመርጠው እናታችንን ነው። እናቴም ከሁሉም ዘመዶቿዋ የበለጠ ለእርሱ ያላት ፍቅር በጣም የተለየ ነው። ሁለቱም ጨዋታ አዋቂዎች ሲሆኑ አንዱ ለአንዱ ያላቸው ፍቅር እጅግ የሚያስቀና ነው። ይህ የእናታችን ጋሸ ሸዋዬን መውደድ እኛም ልጆችዋ ያለ ገድብ እርሱን እንድንወደው አድርጎናል። ስለዚህ የዘወትር የልጅነት ምኞቴ በዲፕሎማ ተመርቄ፤ ስራ ይዤ ካባ ለብሼ ካህናት መካከል ገብቼ ማገልገል ነበር። እስከማውቀው ድረስ የትምህርት ትልቁ ደረጃ ዲፕሎማ ይመስለኝ ነበር። ይህንን የልጅነት ምኞቴን ለማሳካት በልጅነቴ ሰፈር ካሉ የኔታ መሄድና መማርን ግን አልታደልኩምወደ አስኳላው ገፋሁበት። ታናሽ ወንድሜ ግን የኔታ ጋር እየሄደ ይማር ነበር። እናም ትንሽ የፊደል ገበታን ጨርሶ መልዕክተን መቁጠር ሲጀምር፤ ከእኔ በጣም ብዙ እንደሚያውቅ ይስማው ነበር። አንድ ቀን 9 ክፍል ተማሪ ሳለሁ ይህ ወንድሜ እስኪ መልዕክተ በል አለኝ፤ መልዕክተ አልኩት። ቀጥል እንጂ አለኝ በቃሌ እንድወጣው ፈልጎ፤ እንደማልችል ስነግረው፤ በጣም ነው የተገረመው፤ አንተን ብሎ 9ኛ ክፍል፤ ዝምብለን ነው የደከምነው፤ ገበሬ ብትሆን ይሻል ነበር፤ እያለ ሲገረም ዋለ። ማታ ቤት እንደገባ ለእናታችን ነበር ስሞታ ማሰማየት የጀመረው። ዝም ብለን ነው የምንደክመው ለስሙ 9ኛ ክፍል ነው ግን መልዕክተ እንኳን የማይችል እያለ ሲነግራት፤ እንዴ ይህማ አይደረግም፤ እንዴት እያለች እናቴ ከርሱ ተደርባ እኔን፤ማብሸቅ ጀመሩ። እናቴ ግን ወንድሜን ለማስደሰትና ቀልድ ለመፍጠር እንጂ ሁሉን ታውቃለች። በቃ የዚያን ዕለት ምሽት በእኔ ስነፍና ተመሸ። አመሻሹን አባታችን ገብቶ አረፍ እንዳለ፤ ታናሽ ወንድሜ ያንኑ ዜና ለአባቴ ሲነግረው እናቴ ሳቁዋን መቆጣጠር አልቻለችም፤ ቤቱ በሳቅ ተደበላለቀ። ሁኔታው ያልገባው አባቴ ነገሩን ለማጣራት ለመደገፍም ለመቃረንም አልቸኮለም ዝም አለ። ወንድሜ ግን አባቴ ድጋፉን ሰጥቶት ከትምህርት እንድቀር ለማስደረግ የሚችለውን ሁሉ አደረገ። አባቴ ቀስ ብሎ አስረዳው። ብዙ ተለፍቶበት አመነ። አሁን ትልቅ ከሆን በሁዋላም ይህ ርዕስ ከተነሳ ቤቱ በሳቅ በአንድ እግሩ ይቆማል። እናም ይህንን የወላጅ አደራና ከግቢ ጉባኤ ስመረቅ የተቀበልኩትን አደራ ለመወጣት ጭምር ከቤተክርስቲያን ብዙም አልርቅም። ልጅነት ስለሆነ ለአገልግሎት እንቅፋት የሚሆን ሚስት የለ ድስት።

1990 ዓም ኤርትራ ኢትዮጲያ ላይ ወረራ ስለፈጸመች በርካታ ወጣቶች በንዴት ጦፈው መንግስት ውትድርና ጥሪ ሲያደርግ፤ ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት፤ተመዋል። በወቅቱ፤ የማስተምራቸው የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎቼ፤ ውጤት ሳይመጣላቸው ቀርተው የነበሩት የ2ኛ ደረጃ የክፍል ጓደኞቼ ወደ ግንባር ዘምተዋል። እናም በሰኔ ወር 1990 ዓም ማህበረ ቅዱሳን በሚያሳትመው መንፈሳዊ ጋዜጣ ላይ፡ ምስጥሬን ላካፋላችው በሚለው አምድና በጋዜጣው የመጨረሻ የጀርባ ገጽ ላይ “ እውን ክርስቲያን ወታደር ይሆናልን” የሚል ጥያቄ በትልቁ ተጽፏል። እንደ ማህበረ ቅዱሳን አባልነቴ ከ10 ያልበለጡ ሐመር መጽሔትና ከ5-7 የሚደርሱ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ወስጄ በወረዳው ውስጥ ማከፋፈል ሃላፊነት አለብኝ። በዚያን ወቅት በወረዳው ያለነው የማህበረ ቅዱሳን አባላት ሁለት ነን። እኔና ሲስተር ጽዮን። በዘመኑ የጋዜጣው ዋጋ አንድ ብር ከሃምሳ ሐመር ሶስት ብር ነበሩ። ሐመር መጽሔት ይሸጣል፤ጋዜጣው ግን ላያልቅ ስለሚችል እዚያ ያለን አባላት ከራሳችን እንከፍላለን። እናም በዚያው አመት በወርሃ ሰኔ አንድ እሁድ ጠዋት ከቅዳሴ መልስ ጋዜጣውን እያዞርኩ ስሸጥ፤ጋዜጣና መጽሔት መጥቷል ግዙ ብዬ ለማስነገር ለሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢው ጋዜጣውን ሰጠሁት። ጋዜጣው ለእርሱ ስሰጠው፤ በጀርባው በኩል ስለነበር “እውን ክርስቲያን ወታደር ይሆናልን” የሚለውን ጹሑፍ ከላይ በትልቁ ስለተጻፈ  “እውን ክርስቲያን ወታደር ይሆናልን” የሚል ጋዜጣ መጥቷል ግዙ ብሎ ማስታወቂያውን ሲናገር እኔ እራሴ ግራ ገባኝ። ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣን “እውን ክርስቲያን ወታደር ይሆናልን” በሚል ማስታወቂያ የዚያን እለት ጋዜጣው፤ ወዲያውኑ ከማለቁ ባሻገር ተጨማሪ እንዳስመጣ ቀድሞው የከፈሉኝ ብዙ ሰዎች እንደነበሩ አልረሳውም። እኔና ስምዐ ጽድቅ ዝምድናችን የቆዬ ነው። በሁዋላ ግን ጋዜጣው ቁጥሩ እየበዛ፤ ለማስቀመጥ፤ ስለተቸገርኩ ልጆቼ ሰ/ትቤት ለሚማሩበት አጥቢያ ቤተክርስቲያን ቤተመጻህፍት ቤት አበረከትኩት።

No comments:

Post a Comment

                                                                እኔና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ   ለስራ በተመደብኩበት ወረዳ ውስጥ ከተመደብኩበት መደበኛ ስራዬ ውጭ፤ ቤተክርስ...